በአዲስ አበባ በተከሰቱ የቦምብ ፍንዳታ ሙከራዎች ጉዳት መድረሱ ተገለፀ

በትናንትናው ዕለት በአዲስ አበባ ከተማ በተሞከሩ የቦምብ ፍንዳታዎች የሰው ህይወት መጥፋቱን እንዲሁም በርካቶች መቁሰላቸውን የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጄነራል እንደሻው ጣሰው ገልፀዋል።

የድምፃዊ ሃጫሉ ሁንዴሳን መኪና ውስጥ መገደል ተከትሎ በተነሳው ተቃውሞ ላይ የተሞከሩት ቦምብ ፍንዳታዎች ሦስት ቦታዎች ላይ መሆናቸውንም ኮሚሽነሩ የአርቲስቱን አሟሟት በተመለከተ ለአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን በትናንትናው ዕለት በሰጡት መግለጫ አስረድተዋል።

"የሚያፈነዱት ጭምር ቆስለዋል፣ የሚያፈነዱት ሰዎች ጭምር ሞተዋል፤ ሃሳባቸውን ለመግለፅ የወጡ ንፁሃን ዜጎችም የዚህ ጉዳት ሰለባ ሆነዋል" ያሉት ኮሚሽነሩ ምን ያህል ሰው እንደሞተ እንዲሁም የቆሰሉ ሰዎችን ቁጥርም አልጠቀሱም።

የት አካባቢ የቦምብ ፍንዳታዎቹም እንደተሞከሩ ኮሚሽነሩ ባይጠቅሱም በከተማዋ ከዚህ ቀደም በተደረገ ጥናት "ከተማዋን ለማተራመስ የታጠቁ ኃይሎች ከውጭም ከውስጥም የተለያዩ ሥራዎች ለመስራት ሞክረዋል" ብለዋል።

አክለውም "እንግዲህ ጥይት ሲተኮስ፣ ቦምብ ሲፈነዳ እከሌ ወዳጄ ነው እከሌ ጠላቴ ነው ብሎ አይለይም። ሰላም ሁሉንም ለመጠቅለል አቅም አለው። ችግር ግን ሁሉንም አይጠቀልልም፤ ችግሩ ባለበት ብቻ ያሉ ሰዎች ላይ ጉዳት አድርሶ ያልፋል" በማለት አስረድተዋል።

የፌደራል ፖሊስ አዛዡ የአርቲስቱን ሞት ተከትሎ በተነሱ ተቃውሞዎች የተለያዩ ጉዳቶች እንዲሁም የንብረት መውደሞች መድረሳቸውንም ተናግረዋል።

ጉዳት የደረሰባቸው አካባቢዎችን በተመለከተ የተጠናቀረ መረጃ ባይኖርም በአዳማ፣ ሐረር፣ ዝዋይ፣ ቡልቡላ፣ ሻሸመኔ የመሳሰሉት አካባቢዎች ከፊሎቹ ናቸው ብለዋል።

የጉዳት መጠንም በአሁኑ ሰዓት ለመግለፅ አስቸጋሪ እንደሆነ የገለፁት ኮሚሽነሩ ሆቴሎችና ፋብሪካ የሚመስሉ ተቋማት እንደተቃጠሉም ለጋዜጠኞች አስረድተዋል።

በአዲስ አበባም ሆነ በክልሎች ላይ ስለደረሱ የጉዳት መጠኖች መረጃው እንደተጠናቀረ ለኅብረተሰቡ የሚያደርሱ መሆናቸውን የገለፁት ኮሚሽነሩ ሕዝብ በፍራቻ ተሸብቦ የሚኖርበት ሁኔታ መፈጠር እንደሌለበትም አፅንኦት ሰጥተዋል።

"እንዲህ ትልልቅ ከተሞች ላይ ግለሰቦች ቦምብ ይዘው ሲንቀሳቀሱ ሌሎች ደግሞ እየፈሩ የሚሄዱበት ነገር እንዲፈጠር መፍቀድ የለብንም" ያሉት ኮሚሽነር እንዳሻው ኅብረተሰቡ እጅና ጓንት ሆኖ ነገሮችን እየመረመረ በማረጋጋቱ ሥራ ላይ ከመንግሥት ጎን እንዲቆምም ጥሪ አቅርበዋል።

ከዚህም በተጨማሪ ለሕዝቡ በተለይም ለአገር ሽማግሌዎች ጥሪ ያቀረቡት ኮሚሽነር እንዳሻው አሁን የተፈጠረው ችግር በአጭር ጊዜ እንዲቋጭ የራሳቸውን ሚናም እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።