ሲፒጄ የሃጫሉ ግድያን ተከትሎ ኢንተርኔት መቋረጡንና ጋዜጠኞች መታሰራቸውን አወገዘ

በፖለቲካ ግጥሞቹ የሚታወቀውን የሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ ተከትሎ በሃገሪቱ ኢንተርኔት መቋረጡን እንዲሁም የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትወርክ ጋዜጠኞችን እስር በመቃወም የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ድርጅቱ ሲፒጄ ባወጣው መግለጫ አውግዞታል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ቀውስ በተፈጠረ ወቅት ምላሹ የተለመደው "መረጃን ማፈን" እንደሆነ የጠቀሰው ድርጅት ህዝቡ ወቅታዊ ዜናና መረጃ በሚፈልግበት ወቅት ኢንተርኔትን ማቋረጥ "የሚያሳዝን ነው" በማለት ከሰሃራ በታች ባሉ ሃገራት የድርጅቱ ተወካይ ሙቶኪ ሙሞ ተናግረዋል።

"የመንግሥት ባለስልጣናት በአስቸኳይ ኢንተርኔቱን እንዲመልሱት እንዲሁም በስራ ላይ በቁጥጥር ስር የዋሉት የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትወርክ ጋዜጠኞች መለቀቅ አለባቸው። በተጨማሪም ጋዜጠኞች በአሁኑ ሰዓት ያሉ ተቃውሞዎችን ለደህንነታቸው ሳይሰጉ እንዲሁም ነፃነታችንን እንነጠቃለን ብለው ሳይፈሩ እንዲዘግቡ መንግሥት ዋስትና ሊሰጥ ይገባል" ብለዋል

በትናንትናው ዕለት የፌደራል ፖሊስ አዲስ አበባ የሚገኘውን የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትወርክ ስቱዲዮ "ሰብሮ በመግባት" በርካታ ጋዜጠኞችን በቁጥጥር ስር ማዋሉንም ሲፒጄ በአሜሪካ የሚገኘውን የኔትወርኩን አዘጋጅ ኦስማን ኡኩሜን ዋቢ በማድረግ ጠቅሷል።

ኦስማን ምን ያህል ጋዜጠኞች በቁጥጥር ስር እንደዋሉና የት እንደታሰሩም እንደማያውቅ መናገሩንም ሲፒጄ በመግለጫው አስፍሯል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ በትናንትናው ዕለት ከድምጻዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ የአስከሬን ሽኝት መስተጓጎልና ከአንድ የፖሊስ አባል ግድያ ጋር በተያያዘ የኦሮሚያ ኔትወርክ ስራ አስኪያጅ አቶ ጃዋር መሐመድን ጨምሮ ሌሎች 35 ሰዎች በፖሊስ ቁጥጥር መሆናቸውን የፌደራልና እና የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽኖች በጋራ በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል።

ከትናንት በስቲያ የተገደለው ድምፃዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ መኪናው ውስጥ እያለ በጥይት መመታቱን የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጄነራል እንደሻው ጣሰው በትናንትናው ዕለት ገልፀዋል።

ኮሚሽነር ጄራል እንደሻው በግድያው በቁጥጥር ሥር የዋሉ ሰዎች እንዳሉና "በክትትል ሥር ያሉም አሉ" ብለዋል።