ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ፌደራል ፖሊስ ድምፃዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ በጥይት የተመታው መኪናው ውስጥ መሆኑን ገለፀ
የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጄነራል እንደሻው ጣሰው የድምፃዊ ሃጫሉ ሁንዴሳን አሟሟት በተመለከተ ለአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን አመሻሹ ላይ መግለጫ ሰጥተዋል።
ኮሚሽነሩ በመግለጫው ላይ እንደተናገሩት ድምፃዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ ከመኪናው ወርዶ እንደተመለሰና ፤ ወደ መኪናው ከገባ በኋላ ተጠርጣሪዎቹ የመኪናውን በር ከፍተው በጥይት መትተውታል ብለዋል።
ድምፃዊው ከመኪናው ለምን ወርዶ እንደተመለሰ ኮሚሽነሩ ያሉት ነገር የለም።
ኮሚሽነር ጄነራል እንደሻው በወንጀል ድርጊቱ ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር የዋሉ ሰዎች መኖራቸውን አስታውሰው "በክትትል ሥር ያሉም አሉ" ብለዋል።
የፌደራል ፖሊስ እና የአዲስ አበባ ከተማ ፖሊስ ኮሚሽን የምርመራ ቡድን በጋራ ማዋቀራቸውን የገለፁት ኮሚሽነሩ ቀን ከማታ መረጃዎች ሳይጠፉ ከወንጀል ሥፍራ አስፈላጊ መረጃዎችን ለመውሰድ እየሰሩ መሆናውን ገልፀዋል።
አክለውም "ከእሱ ጋር የተያያዙ ኬዞችን በማጣራት በአጭር ጊዜ ለህብረተሰቡ የበሰለ መረጃ እናቀርባለን ብለን እናምናለን" ብለዋል ኮሚሽነር ጄነራሉ።
"የወንጀሉ አፈጻጸም የተደራጀ እና የረቀቀ ስለሆነ ትዕግስት የሚጠይቅ ነው" ያሉት ኮሚሽነር ጄነራሉ፤ ተጽእኖ ፈጣሪ የሆኑ ግለሰቦች ላይ ግድያ ከሚፈጸምባቸው ምክያቶች አንዱ "አገር ወደ ትርምስ እንድትገባ ነው" ብለዋል።
"ስለዚህ ይህን የምርመራ አካላችን አድርገን በጥንቃቄ ጠንካራ መርማሪዎች መድበን የማጣራት ሥራው በስፋት እየተሰራ ነው የሚገኘው" በማለት አስረድተዋል።
ኮሚሽነሩ "በድርጊቱ የተቆጡ ወጣቶች የሰላማዊ ዜጎች ንብረትን በአዲስ አበባ ከተማ ጨምሮ በተለያየ የአገራችን ክፍሎች እንዳወደሙ መረጃ ደርሶናል" በማለት መሰል ድርጊቶች ስህተት መሆናቸውን ጠቁመው "እያንዳንዱ እርምጃችን ኃላፊነት በተሞላበት መልኩ መሆን አለበት" በማለት መልዕክት አስተላለፈዋል።