አርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ የጀግና አሸኛኘት እንደሚደረግለት ተገለፀ

የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ የቀብር ስነስርዓት የጀግና አሰኛኘት እንደሚደረግለት የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር፣ አቶ ሽመልስ አብዲሳ ገልፀዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ በትናንትናው ዕለት የአርቲስቱን የቀብር ስነ ስርአት አፈፃፀምና አሸኛኘት አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ ነው ይህንን የተናገሩት።

አክለውም ሙዚቀኛውንም ለመዘከር በመላው ኦሮሚያ ሰንደቅ አላማ ለአምስት ቀን ዝቅ ብሎ እንደሚውለበለብ አስረድተዋል።

የቀብር ስነስርዓቱም በትውልድ ከተማው አምቦ በነገው ዕለት ሰኔ 25፣ 2012 ዓ.ም ይፈፀማል።

ርዕሰ መስተዳድሩ ከዚህም በተጨማሪ የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ አስከሬን በመንግሥት የጸጥታ ኃይል ታጅቦ ወደ አምቦ መወሰዱን ተናግረው ነበር።

ትናንት፣ ማክሰኞ፣ ንጋት ላይ የአርቲስት ሃጫሉ አስከሬን በበርካታ አድናቂዎቹ ታጅቦ ወደ አምቦ ሲያመራ የነበረ ቢሆንም ቀብሩ መፈፀም ያለበት አዲስ አበባ ነው የሚሉ ተቃውሞዎች መሰማታቸውን ተከትሎ አስክሬኑ ወደ አዲስ አበባ እንዲመለስ ተደርጎ ነበር።

ወደ አዲስ አበባ ከተመለሰም በኋላ አስከሬኑ ስታዲየም አቅራቢያ በሚገኘው የኦሮሞ ባህል ማዕከል እንዲያርፍ ተደርጎ ቆይቷል።

ከዚያም አስከሬኑ ወደ አምቦ በሄሊኮፕተር ተጭኖ ወደ ከአምቦ ከተማ በቅርብ ርቀት ወደ ሚገኘው ሆሚቾ አሙኔሽን ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪ መወሰዱ ተነግሯል።

የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ርዕሰ መስተዳድር ከደቂቃዎች በፊት በክልሉ መገናኛ ብዙሃን ላይ ቀርበው ዛሬ ንጋት አስክሬኑ ወደ አምቦ እየተወሰደ ሳለ፤ ከቤተሰብ ፍላጎት ውጪ ወደ አዲስ አበባ እንዲመለስ ተደርጓል ብለዋል።

አቶ ሽመልስ ጨምረውም፤ አስከሬኑን በቤተሰብ ጥያቄ በሄሊኮፕተር ተጭኖ ወደ አምቦ እንዲመለስ መደረጉን ተናግረዋል።

የኦሮሚያ ክልል መንግሥት ሙሉ ኃላፊነት ወስዶ ከቤተሰብ ጋር በመመካከር የቀብር ስነ-ስርዓቱን እንደሚያስፈጽም የክልሉ ፕሬዝዳንት ጨምረው ተናግረዋል።

የአምቦ ከተማ ነዋሪ ለቢቢሲ እንደተናገሩት፤ አስከሬኑን በሄሊኮፕተር ከአምቦ በቅርብ ርቀት ወደሚገኘው ሆሚቾ አሙኔሽን ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪ የደረሰው ከአንድ ሰዓት በፊት [9 ሰዓት ገደማ] ነበር። "ከሆሚቾ ወደ አምቦ የመጣው በአንድ አምቡላንስ እና በአንድ ፓትሮል መኪና ታጅቦ ነው። አሁን አስክሬኑ ወላጆቹ ቤት ይገኛል" ሲሉ ተናግረዋል።

ሌላው የከተማው ነዋሪ "አስከሬኑ ያለው አባቱ ቤት ነው። እዛ ሄጄ እየተመለስኩ ነው" ሲል ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

ከትናንት በስቲያ የተገደለው ድምፃዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ መኪናው ውስጥ እያለ በጥይት መመታቱን የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጄነራል እንደሻው ጣሰው በትናንትናው ዕለት ገልፀዋል።

ኮሚሽነር ጄራል እንደሻው በግድያው በቁጥጥር ሥር የዋሉ ሰዎች እንዳሉና "በክትትል ሥር ያሉም አሉ" ብለዋል።