ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ስለአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ እስካሁን የምናውቀው
አርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ማንነታቸው ባልታወቁ ሰዎች ሰኞ ምሽት 3፡30 አካባቢ በጥይት ተመትቶ መገደሉን ፖሊስ አስታውቋል።
ስለአርቲስቱ ግድያ እና ከግድያው ጋር ተያይዘው ስለተከሰቱ ነገሮች የእስካሁን የሚታወቁ ጉዳዮች የሚከተሉት ናቸው።
የሃጫሉ ሁንዴሳ በጥይት ተመቶ የመገደል ዜና በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ መዘዋወር የጀመረው ከምሽት 5፡30 አካባቢ ጀምሮ ነበር።
በርካቶች የታዋቂውን ድምጻዊ ግድያን በማስመልከት ሃዘናቸውን በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ ሲገልጹ ነበር።
ከዚያም ከእኩለ ለሊት በኋላ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው በብሔራዊው ቴሌቪዥን ላይ ቀርበው አርቲስት ሃጫሉ በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ገላን ኮንዶሚኒየም ተብሎ በሚታወቀው አካባቢ ከምሽቱ 3፡30 አከባቢ በጥይት ተመቶ መገደሉን አረጋገጡ።
ኮሚሽነሩ ጨምረውም በግድያው ወንጀል የተጠረጠሩ የተወሰኑ ሰዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ገልጸዋል።
ከእኩለ ለሊት በኋላ አዲስ አበባን ጨምሮ በበርካታ የኦሮሚያ ከተሞች ሰዎች ሃዘናቸውን ለመግለጽ ወደ መንገድ ወጡ። ሌሊቱን በፌስቡክ አማካኝነት ሲሰራጩ በነበሩ የቀጥታ ስርጭቶች፤ በርካቶች መንገድ ላይ በመውጣት ሲያለቅሱ ታይተዋል።
በምሥራቅ እና ምዕራብ ኦሮሚያ ከተሞችም ንጋት ላይ መንገድ ዝግ የተደረገባቸው ከተሞች ነበሩ።
የአስከሬን ሽኝት ከአዲስ አበባ
የሃጫሉ ሁንዴሳ አስክሬን ወደ ትውልድ ከተማው አምቦ እንደተሸኘ የተነገረ ሲሆን። ቁጥሩ ከፍተኛ የሆነ ሕዝብ የአርቲስቱን አስከሬን ለመሸኘት ወጥቷል።
አስከሬን ለመሸኘት የወጡ ሰዎች ሃዘናቸውን በተለያየ መልክ ሲገልጹ ነበር። በዚህ ጊዜ ፖሊስ አስለቃሽ ጪስ ሲተኩስ በስፍራው የነበሩ ሰዎች በፌስቡክ የቀጥታ ካሰራጩት ምስል ላይ ታይቷል። በተጨማሪም የድምጻዊውን አስክሬን ለመሸኘት ከወጡ ሰዎችም ቢቢሲ አረጋግጧል።
የአስከሬን አቀባበል በአምቦ
ዛሬ ንጋት ላይ የአርቲስት ሃጫሉ አስከሬን በበርካታ አድናቂዎቹ ታጅቦ ወደ አምቦ ሲያመራ የነበረ ቢሆንም ቀብሩ መፈፀም ያለበት አዲስ አበባ ነው የሚሉ ተቃውሞዎች መሰማታቸውን ተከትሎ አስክሬኑ ወደ አዲስ አበባ እንዲመለስ ተደርጎ ነበር።
ወደ አዲስ አበባ ከተመለሰም በኋላ አስክሬኑ ስታዲየም አቅራቢያ በሚገኘው የኦሮሞ ባህል ማዕከል እንዲያረፍ ተደርጎ ቆይቷል።
ከዚያም አስክሬኑ ወደ አምቦ በሄሊኮፕተር ተጭኖ ወደ ከአምቦ ከተማ በቅርብ ርቀት ወደ ሚገኘው ሆሚቾ አሙኔሽን ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪ መወሰዱ ተነግሯል።
ማለዳ አምቦ ቁጥሩ እጅግ ከፍተኛ የሆነ ሕዝብ አስክሬኑን ለመቀበል በመጠባበቅ ላይ ነበር። “የከተማው ሕዝብ ወደ ዋና መንገድ ወጥቷል። ከገጠርም በጣም ብዙ ሰዎች በፈረስ እየመጡ ነው” ሲሉ አንድ የከተማው ነዋሪ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎችም በነዳጅ ማደያ እና ባንክ ቤቶች በመሳሰሉት ተቋማት አካባቢ እንጂ በብዛት በከተማዋ ውስጥ እንደማይታዩ አኚሁ ነዋሪ ጨምረው ተናግረው ነበር።
የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ የቀብር ስነስርዓት መቼ እንደሚፈፀም ከቤተሰቡም ሆነ ከመንግሥት አካል እስካሁን ምንም የተባለ ነገር የለም።
ሃጫሉ ከዚህ ቀደም ምን ብሎ ነበር?
ሃጫሉ ሁንዴሳ ከዚህ ቀደም ቢቢሲን ጨምሮ ከሌሎች መገናኛ ብዙሃን ጋር ባደረገው ቃለ መጠይቅ ተደጋጋሚ የግድያ ዛቻዎች ይደርሰው እንደነበረ ተናግሯል።
ከሳምንት በፊት ሰኔ 15/2012 ዓ.ም በኦሮሚያ ሚዲያ ኔትዎርክ ላይ በተላለፈው ቃለ መጠይቁ፤ ሃጫሉ “እየታገልኩ እኮ ነው የምኖረው” በማለት ተደጋጋሚ የግድያ ዛቻ እንደሚደርስበት ተናግሯል።
የሃጫሉን ግድያ ተከትሎ ማን ምን አለ?
ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ በድምጻዊው ሞት የተሰማቸውን ሀዘን "ውድ ህይወት አጥተናል" በማለት "የዚህ ድንቅና አንፀባራቂ ወጣት አርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ህይወት መቀጠፍ ከተሰማ ጀምሮ በከባድ ሃዘን ውስጥ ለምንገኝ ሁሉ መፅናናትን እመኛለሁም" በማለት ሃዘናቸውን ገልጸዋል።
የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ በድምጻዊው ግድያ ከባድ ሐዘን እንደተሰማቸው ገልጸው "ሃጫሉን የገደለው ማንም ይሁን ማን ከህግ ማምለጥ አይችልም" ብለዋል። ጠቅላይ አቃቤ ሕጓ ጨምረውም "በዚህ እኩይ እና አስነዋሪ ተግባር የተሳተፉ በሕግ ዋጋቸውን ያገኛሉ" ሲሉ ተናግረዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ “መራር ሃዘን . . .” ካሉ በኋላ በኦሮምኛ “ውስጤ ነው ያለቀሰው፣ ልቤ ነው የደማው” በማለት ሃዘናቸውን ገልጸዋል።
በአሁኑ ሰዓት የአርቲስቱ አስክሬን ወደ አምቦ እየሄድ ይገኛል። የኢንተርኔት አገልግሎ በመቋረጡ ተጨማሪ መረጃዎችን ማግኘት አልተቻለም። በአዲስ አበባ፣ መቀሌ፣ ባህር ዳር፣ ነቀምት እና አምቦ የኢንተርኔት አግልግሎት መቋረጡን አረጋግጠናል።
ቁጣና አለመረጋጋት
የታዋቂው ሙዚቀኛ ሞትን ተከትሎ በአንዳንድ የኦሮሚያ አካባቢዎች ቁጣና አለመረጋጋት መከሰቱን ቢቢሲ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች ገልጸዋል። በዚህም መሰረት ከአዲስ አበባ በስተ ምሥራቅ በምትገኘው በአዳማ ከተማ የተቃውሞ ሰልፎችና አለመረጋጋት እንዳለ ቢቢሲ ከቦታው አረጋግጧል። በከተማዋ አንዳንድ የመንግሥት ህንጻዎች ላይ ጉዳት እንደደረሰባቸው የዓይን ምስክሮች ለቢቢሲ ሪፖርተሮች ገልጸዋል።
በአዳማ የሆስፒታል ምንጮች ለፈረንሳዩ የዜና ወኪል እንዳጋገጡት ወደ ሆስፒታል በጥይት ተመትተው የመጡ ሰዎች ሲኖሩ ሶስት ሰዎች ደግሞ ሞተዋል።በተጨማሪም በአዳማ ከተማ ለተቃውሞ ወደ ኦቢኤን የቴሌቪዥን ጣቢያ ሲያመሩ የነበሩ ሰልፈኞች በጸጥታ ኃይሎች የተበተኑ ሲሆን፤ አንድ ሰው መቁሰሉን የዓይን ምስክሮች ተናግረዋል።የጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ የትውልድ አካባቢ በሆነው ጅማ ውስጥም ሰልፎች እየተደሩጉ መሆኑን ከቦታው ያናገርናቸው ነዋሪዎች ገለጸዋል።
ቢቢሲ ከጭሮ ማረጋገጥ እንደቻለው ሁለት ተቃዋሚ ሰልፈኞ በጥይት ተመትተው ሲሞቱ የመንግሥት ሕንጻዎችም ተቃጥለዋል።