በድምጻዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ ሞት የተቆጡ ወጣቶች በለንደን የኢትዮጵያ ኤምባሲ ላይ ጥቃት አደረሱ

በድምጻዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ ሞት የተቆጡና ብረትና ተቀጣጣይ ነገር ያዙ ወጣቶች በለንደን የኢትዮጵያ ኤምባሲ ላይ ጥቃት ማድረሳቸውን በእንግሊዝ የኢትዮጵያ ኤምባሲ የዳያስፖራና የሚዲያ ኃላፊ የሆኑት አቶ ያለው ከበደ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

አቶ ያለው ከበደ ለቢበሲ እንደገለፁት በትናንትናው እለት በድምጻዊ ሃጫሉ ሞት የተቆጡ በርከት ያሉ ወጣቶች ተሰባስበው ወደ ኤምባሲው በመምጣት የተለያዩ ጉዳቶችን አድርሰዋል ብለዋል።

ወጣቶቹ የኢትዮጵያን ሰንደቅ አላማ በማውረድ ለማቃጠል መሞከራቸውን በምትኩ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ሰንደቅ አላማ መስቀላቸውንና በሰውና በንብረት ላይ ጉዳት ማድረሳቸውን ጨምረው አስረድተዋል።

ወጣቶቹ ወደ ኤምባሲው የመጡት ከሰዓት ስምንት ሰዓት ላይ ነው ያሉት ኃላፊው ወደ ኤምባሲው ለመግባት መሞከራቸውንም ገልፀዋል።

በኤምባሲው የቆንስላር ክፍል ውክልና ለመስጠት መጥቶ የነበረ አንድ ተገልጋይን ሲወጣ በማግኘት መደብደባቸውንም ጨምረው ተናግረዋል።

የወጣቶቹ ዋና አላማ ኤምባሲው በመግባት ጉዳት ማድረስ እንደነበር ያመላከቱት አቶ ያለው ተቀጣጣይ ነገርና ብረት ይዘው እንደነበር አስረድተዋል።

አቶ ያለው አክለውም በወቅቱ የኤምባሲው ሠራተኞች በሙሉ በሥራ ገበታቸው ላይ ነበሩ በማለት ንብረት ላይ ጉዳት ከማድረስና አንድ ተገልጋይ ከመደብደቡ ውጪ ሌሎች ሰዎች ላይ ጉዳት አለመድረሱን ገልፀዋል።

ኤምባሲው ጉዳዩን ለፖሊስ ማመልከቱን ገልፀው በንብረት ላይ ያደረሱት ጉዳት፣ ተገልጋይን በመደብደባቸው በሕግ ለመጠየቅ የሚያስችል መረጃ ወስደዋል።

ወጣቶቹ የፈቃድ ሠልፍ ሳይጠይቁ በድንገት በመምጣታቸው ምክንያት ማንነታቸውን ለመለየት ከሲሲቲቪ ካሜራ ላይ መረጃ መውሰዳቸውን አስረድተዋል።

እስካሁን ድረስ ግን ከጥፋት አድራሾቹ መካከል የተያዘ አለመኖሩን አቶ ያለው ተናግረዋል። ከዚህ በኋላ ግን ፖሊስ ክስ እንደሚመሰርት መናገራቸውን ተናግረዋል።

ኤምባሲው ላይ ጥቃት ከደረሰ በኋላ በለንደን የሚገኘው የአጼ ኃይለስላሴ ሃውልት መፍረሱን በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ የተሰራጨው ፎቶ ያሳያል።

አቶ ያለው ኃውልቱ ከኤምባሲው ርቆ እንደሚገኝና እርሳቸውም በፌስቡክ ላይ ማየታቸውን በመግለጽ ከዚህ ውጪ ተጨማሪ መረጃ እንደሌላቸው ገልፀዋል።

አቶ ያለው አክለውም ወጣቶቹ አሁን በድንገት በመምጣታቸውና የከፋ ጉዳት ባለማድረሳቸው እንጂ ኤምባሲውም ላይ ሆነ ሠራተኞቹ ላይ የከፋ ጉዳት ሊደርስ የሚችልበት እድል መኖሩን አስታውሰው፣ በቪየና ስምምነት መሰረት ኤምባሲውን የመጠበቅ የእንግሊዝ መንግሥት ግዴታ እንዳለበት አስታውሰው ፖሊስ አስፈላጊውን ጥበቃ እንደሚያደርግላቸው መናገሩን ገልፀዋል።

"የኤምባሲው ሠራተኞች በአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ሞት ሀዘን ውስጥ በነበሩበትና መንግሥት ወንጀሉን ፈጻሚዎች አድኖ ለፍርድ ለማቅረብ ቁርጠኝነቱን በተናገረበት ሰአት ይህ መድረሱ አሳዝኖናልም" ብለዋል።