ሰሜን ኮሪያ ደቡብ ኮሪያን ‹‹እወርሻለሁ›› ስትል አስፈራራች

የሰሜን ኮሪያ ሠራዊት ከወታደር ነጻ ቀጠና ወደሆነው ድንበር ለመግባት ተዘጋጅቻለሁ ሲል ደቡብ ኮሪያን እያስፈራራ ነው።

ይህ ማስፈራሪያ የመጣው ሰሜን ኮሪያ በቅርቡ ወደ አገሯ ከሚላኩባት በራሪ ፊኛዎች ጋር ተያይዞ ደሜ ፈልቷል ማለቷን ተከትሎ ነው።

ሰሜን ኮሪያን የሚያበሳጨው ድርጊት አገሯን የከዱና በጎረቤት ደቡብ ኮሪያ የሚኖሩ የአርበኞች ግንባር አባላት በፊኛዎች ውስጥ ቼኮሌትና ፖስትካርድ እያደረጉ ወደክልሏ የሚልኳቸው ፊኛዎች ናቸው።

በሳምንቱ መጨረሻ እጀግ የሚፈራው የሰሜን ኮሪያ ፕሬዝዳንት የኪም ጆንግ ኡን እህት ኃያሏ ኪም ጆንግ ዮንግ ወታደሮቿን ወደ ድንበር ለመጠጋት እንዲዘጋጁ በሚል በተጠንቀቅ ሁኑ ብያቸዋለው ብላ በአገሯ ብሔራዊ ቴሌቪዥን የክተት አዋጅ የሚመስል ነገር መናገሯ ነው።

ይህን ተከትሎ የሰሜን ኮሪያ ሰራዊት ወደ ድንበር ለመጠጋት ከምንጊዜው በላይ በተጠንቀቅ ላይ እገኛለሁ ሲል የእመቤቲቱን ማስጠንቀቂያ አጠናክሮታል፡፡

ይህን ተከትሎ በድንበር አካባቢ መጠነኛ ውጥረት ተፈጥሯል፡፡

ምን አዲስ ነገር ተከሰተ?

ሰሜንና ደቡብ ኮሪያ ከ1950 እስከ 1953 ያደረጉትን ጦርነት ተከትሎ ወታደር አልባ ቀጠናን በድንበራቸው ፈጥረዋል፡፡

ማክሰኞ ዕለት የሰሜን ኮሪያ ሰራዊት በቀጣይ ይህን ነጻ ቀጠና ለመቆጣጠር ስለሚወስደው እርምጃ እያጠና እንደሆነ ተናገረ፡፡

የሰራዊቱ የዕዝ ማዕከል እንደገለጸው ሰራዊቱ በከፍተኛ ተጠንቀቅ ላይ መሆኑን እና ለመንቀሳቀስ ከበላይ ትዕዛዝ ብቻ እየጠበቀ ስለመሆኑ አስታውቋል፡፡

ይህ መግለጫ ከሰራዊቱ የመጣው የኪም እህት ኃያሏ ኪም ጆንግ ዮንግ "ደቡብ ኮሪያ ሥርዓት የማትይዝ ከሆነ በወታደራዊ እርምጃ እንቀጣታለን" ማለታቸውን ተከትሎ ነው፡፡

በሰሜን ኮሪያ 'አውራ' ፓርቲ ውስጥ አውራውን ሥልጣን ይዛለች የምትባለው እህት ኪም ዮ ጆንግ እንደተናገረችው ይህ ወቅት ከደቡብ ኮሪያ ባለሥልጣናት ግንኙነታችንን የምናቋርጥበት ትክክለኛ ጊዜ ነው ብላለች፡፡

የማያዳግም እርምጃ እንደምትወስድ የተናገረችው ኃያሏ እህት ኪም ጆንግ ደቡብ ኮሪያን አበሻቅጣታለች፡፡ "ቆሻሻ መጣል ያለበት በቆሻሻ ገንዳ ውስጥ ነው" በማለትም ተናግራለች፡፡

ደቡብ ኮሪያ እነዚህን ፌዝ የሚመስሉ ማስፈራሪያዎች በዋዛ አትመለከታቸውም፡፡

የደቡብ ኮሪያ የደኅንነት መሥሪያ ቤት ሁኔታዎችን በቅርብ እየተከታተለ ሲሆን ፕሬዝዳንት ሙን ፒዮንግየንግ እባክሽን ሰላም አውርጂ ሲሉ ተማጽነዋታል፡፡

ሁለቱ አገራት በፊኛ የተነሳ ወደ ሙሉ ጦርነት ይገቡ ይሆን?

ሰሜን ኮሪያ ከአገሯ የከዱና በጎረቤት ደቡብ ኮሪያ ያሉ የአርበኞች ማኅበር አባላት ድርጊት ሁልጊዜም እንዳንገበገባት ነው፡፡

መክዳታቸው ሳያንስ ወደ ድንበር እየተጠጉ በፊኛ ውስጥ ቼኮሌትና ሌሎች ጸረ ሰሜን ኮሪያ መልእክቶችን ወደ አገራቸው ይልካሉ፡፡

ይህ ድርጊት እንዲቆም ሰሜን ኮሪያ በተደጋጋሚ ብትቆጣትም ደቡብ ኮሪያ ለነገሩ ቁብ ሳትሰጠው ቆይታለች፡፡

የሰሜን ኮሪያ ቁጣ እያየለ መምጣቱ ያሳሰባት ደቡብ ኮሪያ ይህን ፊኛ የማስወንጨፉን ነገር ለማቆም እንደምትሞክር ቃል ገብታ ነበር፡፡

በደቡቡ ኮሪያ የሰሜን ኮሪያ የአርበኞች ግንባር አባላት በበኩላቸው የመናገር ነጻነታችን ዲሞክራሲ ባለባት ደቡብ ኮሪያ እንዴት ተደርጎ ይደፈራል ሲሉ በድርጊቱ እንደሚገፉበት ዝተዋል፡፡

ተንታኞች እንደሚሉት ግን ሰሜን ኮሪያን እያስቆጣት ያለው ዋናው ነገር ፊኛው ሳይሆን ተስፋ ጥላበት የነበረው የማዕቀብ ይነሳልኛል ጉዳይ ቸል እየተባለ በመምጣቱ ነው፡፡

ፕዮንግያንግ በሶል ላይ የተቆጣችው በዋናነት ጎረቤት ደቡብ ኮሪያ አሜሪካንን አሳምናም ቢሆን ማእቀቡ እንዲላላ ለምን አታደርግልኝም በሚል ነው፡፡

ሰሜን ኮሪያ እጅግ የሚቆነጥጥ የምጣኔ ሀብትና የወታደራዊ ማዕቀብ ነው የተጣለባት፡፡

ዶናልድ ትራምፕ አቻቸውን ኪምን በአካል አግኝተው ከተወያዩ በኋላ ነገሮች መልካቸውን ይቀይራሉ የሚል ተስፋ የነበረ ቢሆንም ኋላ ላይ ሁሉም ነገር ባለበት ቀጥሏል፡፡

አሁን ሰሜን ኮሪያ ከደቡብ ኮሪያ የሚለቀቁ ፊኛዎች አስቆጥተውኛል ስለዚህ ሰራዊቴን ወደ ድንበር አስጠጋለሁ የምትለው በአካባቢው መጠነኛ ውጥረት በመፍጠር የማእቀቡ ጉዳይ እንደ አዲስ መነጋገሪያ እንዲሆን በመፈለጓ ነው ይላሉ ፖለቲካ አዋቂዎች፡፡