በኢትዮጵያ በአስክሬን ምርመራ ኮቪድ-19 መገኘቱ ምን ያመላክታል?

የጤና ሚንስቴር እና የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ተቋም በጋራ በሚሰጡት ዕለታዊ መግለጫ ላይ፤ በአስክሬን ምርመራ ኮቪድ-19 መገኘቱ ሲገለጽ ሰንብቷል። የሰኔ 7 ቀን 2012 ዓ. ም. ሪፖርትን እንኳ ብንመለከት በሁለት አስክሬኖች ላይ ኮቪድ-19 ተገኝቷል። ሁለቱም ግለሰቦች የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ነበሩ።

ለመሆኑ የሰዎች አስክሬን ተመርምሮ በኮቪድ-19 ተይዘው እንደነበረ ማወቁ ምን ያመላክታል? እነዚህ ሰዎች የሞቱት በኮሮናቫይረስ ነው ወይስ በተጓዳኝ ህመሞች? በሽታው በማኅበረሰቡ ውስጥ እየተሰራጨበት ስላለው ፍጥነትስ ምን ይነግረናል?

ለእነዚህ ጥያቄዎች በስዊድን አገር ማላርጋለን ተብሎ በሚጠራው ዓለም አቀፍ የጤና ተቋም ውስጥ መምህርና የሕብረሰብ ጤና ሳይንስ ተመራማሪ የሆኑት በንቲ ገለታ ምላሽ አላቸው።

እሳቸው እንደሚሉት፤ ሕይወታቸው ካለፈ በኋላ በቫይረሱ መያዛቸው የሚታወቅ ሰዎች መኖራቸው በሽታው ማኅበረሰቡ ውስጥ በከፍተኛ ሁኔታ መሰራጨቱን ያሳያል።

“ባለፈው ሳምንት የተጠቀሰውን አሃዝ ብንወስድ ሕይወታቸው ካለፈ 27 ሰዎች መካከል አስራ አንዱ ከሞቱ በኋላ ቫይረሱ እንደነበረባቸው ታውቋል። ይህ ወደ 41 በመቶ አካባቢ ነው። ቀድሞ የሌሎች በሽታዎች መኖር ለቫይረሱ መባባስ ምክንያት ሊሆን ይችላል። የሞት ምክንያቱም በቫይረሱ ወይም ከዚህ ቀደም የነበረባቸው በሽታ ምክንያት ሊሆን ይችላል” ሲሉ ያስረዳሉ።

አሁን ላይ በሕብረተሰቡ ውስጥ ያለው የበሽታ ቅኝት ደካማ መሆኑን ተመራማሪው ይናገራሉ። በአስከሬን ናሙና ምርመራ ኮቪድ-19 መገኘቱ ብዙ በሽታው እንዳለባቸው ያልታወቁ ሰዎች እንዳሉ እንደሚጠቁምም ያክላሉ።

የጤና ባለሙያዎች ቤት ለቤት ተዘዋውረው የሙቀት ልኬት ማድረጋቸው ብቻውን በቂ እንዳልሆነና፤ ስለ በሽታው ምልክቶች ለማኅበረሰቡ ግንዛቤ ሰጥቶ፤ ሰዎች ምልክቱን ሲያዩ በአቅራቢያቸው ወደሚገኝ የጤና ተቋም በአፋጣኝ እንዲሄዱ ማነሳሳት እንደሚያስፈልግም ይመክራሉ።

“አሁን ባለው አካሄድ የበሽታውን ሥርጭት ማወቅና ትስስሩን ማግኘት አልተቻለም። የዓለም ጤና ድርጅትና ሌሎችም ከዚህ በፊት ለሌሎች ተላላፊ በሽታዎች ሲጠቀሙበት የነበረው የማኅበረሰብ ጤና ቅኝት አሠራር ነው። እያንዳንዱ ሰው ዋና ዋና የበሽታውን ምልክቶች እንዲያውቅ መደረግ አለበት። ምልክቱን እንዳየ ለጤና ተቋም ያሳውቅና በጤና ባለሙያ ምርመራ ይደረግለታል።”

የጤና ባለሙያዎች እንደሚሉት ከሆነ፤ የበሽታውን ምልክት የማያሳዩ ነገር ግን ቫይረሱ ያለባቸው ሰዎች አሉ። ታድያ አንድ ሰው በሽታው ኖሮበት ምልክቱን ካላሳየ እንዴት ወደ ጤና ተቋም ያመራል? ስንል ለመምህር በንቲ ጥያቄ አቅርበን ነበር።

እርሳቸው እንደሚያስረዱት፤ ከ80 በመቶ በላይ የሚሆኑ ሰዎች የበሽታውን ምልክት ላያሳዩ ይችላሉ። ምንም ሳይታወቅባቸው (ስፓንታንየስ ሪዞሉሽን የሚባለው) ሊድኑ ይችላሉ። ወደ 14 በመቶ የሚሆኑ ሰዎች ደግሞ የበሽታውን ምልክት ቢያሳዩም ወደ ጤና ተቋም በሚያስኬድ ደረጃ በጠና አይታመሙም።

የተቀሩት ስድስት በመቶ የሚሆኑ ሰዎች ግን የሕክምና እርዳታ ያስፈልጋቸዋል። ከነዚህ መካከል ከበሽታው የሚያገግሙ፣ በቫይረሱ ሳቢያ ሕይወታቸውን የሚያጡም አሉ።

“የበሽታውን ምልክት የማያሳይ ሰው ቫይረሱን ወደ ሌላ ሰው እንዳያስተላልፍ ለማድረግ መወሰድ ያለባቸው ጥንቅቃቄዎች አሉ። ማንኛውም ሰው በሽታው ኖረበትም አልኖረበትም እስካሁን ሲባሉ የነበሩ ጥንቃቄዎች መተግበር አለበት። ማለትም እጅ አዘውትሮ መታጠብ፣ አካላዊ ርቀት መጠበቅ፣ ሲስሉም ሆነ ሲያስነጥሱ በክንድ አፍን መሸፈን መተግበር አለባቸው።”

ከዚህ ቀደም ሕይወታቸው ካለፈ በኋላ በአስክሬን ምርመራ ኮቪድ-19 የተገኘባቸው አሉ። ከነዚህ መካከልም አዲስ አበባ ልደታ አካባቢ ይኖሩ የነበሩት አዛውንት ይጠቀሳሉ።

አዛውንቷ የቀብር ሥነ ሥርዓታቸው ተፈጽሞ፤ ወዳጅ ዘመዶቻቸው ሀዘን ተቀምጠው ሳለ ነበር ከአስክሬናቸው በተወሰደ ናሙና ኮቪድ-19 እንዳለባቸው የታወቀው።

የአካባቢው ነዋሪዎች ለጥቂት ቀናት እንቅስቃሴ ገትተው እንደነበርም ይታወሳል።

እንዲህ ያሉ ገጠመኞች፤ በሽታው እንዳለባቸው ሳይታወቅ በሚሞቱ ሰዎች ሳቢያ ቤተሰቦቻቸው እንዲሁም በአቅራቢያቸው የሚኖሩ ሰዎች ለወረርሽኙ ተጋላጭ አይሆኑም? የሚል ጥያቄ ያስከትላሉ። መምህሩም እነዚህ ግለሰቦች በአካባቢያቸው ያሉ ሰዎችን ለበሽታው ማጋለጣቸው እንደማይቀር ይናገራሉ።

በኢትዮጵያ ኮሮናቫይረስ ያለበት ሰው ሲገኝ፤ የጉዞ ታሪክ ያላቸው ሰዎች ከዛም ከእነርሱ ጋር ንክኪ ያላቸው ግለሰቦችና በአስገዳጅ ለይቶ ማቆያ የነበሩ ሰዎች በግንባር ቀደምነት ሲመረመሩ ነበር።

ተመራማሪው በንቲ እንደሚሉት፤ አሁን ላይ በሽታው በስፋት በማኅበረሰቡ ውስጥ ተሰራጭቷል።

“የሚመረመረው ሰው በጨመረ ቁጥር በሽታው የሚገኝበትም ሰው እየጨመረ ነው። ማኅበረሰቡ ውስጥ በርካታ በበሽታው የተያዘ ሰው እንዳለና በተመረመረ ቁጥር የሚገኝ የማኅበረሰብ ክፍል እንዳለ ያሳያል። ከምንገምተውም በላይ ከፍተኛ ሊሆን ይችላል። ሁሉም ሰው ቢመረመር ደግሞ በጣም ከፍተኛ ቁጥር ይገኛል” ሲሉም ያስረዳሉ።

አያይዘውም፤ በሽታውን አንዳች ነጥብ ላይ መግታት የሚቻልበት ተስፋ አለ? ወይስ መግታት የሚቻልበት ጊዜ አልፎ በሽታው ከቁጥጥር ወጥቷል? የሚለውን ጥያቄ መመለስ አዳጋች እንደሆነ ይናገራሉ።

“በጣም ያስፈራኛል። ምክንያቱም አሁን ጫፉን [ፒክ] አላየንም” የሚሉት መምህሩ፤ ወደፊት የሚመጣውን መገመት አስቸጋሪ መሆኑን ይገልጻሉ።

ሆኖም ግን የጤና ባለሙያዎች የሚያደርጉት ቅኝትና በሽታውን ለመከላከል የተቋቋመው ግብረ ኃይል እንቅስቃሴ ብቻ በቂ አይደለም ይላሉ። ማኅበረሰቡ ስለ በሽታው ግንዛቤ ኖሮት ምልክቶችን ካየ እንዲያሳውቅ (ሰልፍ ሪፖርት የሚባለው) መደረግ እንዳለበት ያስረግጣሉ።

“ሰው ሰልፍ ሪፓርት እንዲያደርግ ለማበረታታት በበሽታው የተያዙ ሰዎች ጥሩ እንክብካቤ እንደሚሰጣቸው ማሳየት ያስፈልጋል። በለይቶ ማቆያ ውስጥ ያሉ ሰዎች ክብራቸው ተጠብቆ አገልግሎት አንደሚሰጣቸው ሲታይም ሰዎች ሰልፍ ሪፖርት ለማድረግ ይደፋፈራሉ።”