ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ዙም መሰብሰቢያ ብቻ ሳይሆን ከሥራ ማባረሪያም ሆኗል
ኮሮናቫይረስ ብዙዎች ቤታቸውን ቢሮቿው እንዲያደርጉ አስገድዷል። ስብሰባዎች በዙም መካሄድ ከጀመሩም ወራት ተቆጥረዋል። ዙም ስብሰባ ማከናወኛ ብቻ ሳይሆን ከሥራ ማባረሪያም ሆኗል። ለዚህ ጥሩ ምሳሌ ‘ፓና’ የተባለ ድርጀት ነው። የድርጅቱ ኃላፊዎች ሁለት ስብሰባ እንደሚካሄድ አስታወቁ። የመጀመሪያው ስብሰባ 3፡00 ላይ ሁለተኛው ደግሞ 3፡45 ላይ።
የሦስት ሰዓቱ ስብሰባ ከተቋሙ ጋር ለሚቀጥሉ ሰዎች ነበር። ቀጣዩ ስብሰባ ደግሞ ለሚባረረሩ ተቀጣሪዎች። ሠራተኞቹ ለየትኛው ስብሰሰባ እንጠራ ይሆን? ብለው ተጨንቀው ነበር።
ከነዚህ አንዷ የሽያጭ ኃላፊዋ ሩቲ ታውንሰንድ ናት። በጣም ከመጨነቋ የተነሳ የ3 ሰዓቱና የ3፡45ቱ ስብሰባ ትምታታባት።
“ከሥራ የሚባረሩ ሰዎች አሉ የሚለው ዜና አስደንግጦኝ ስለነበር ስብሰባዎቹ ተምታቱብኝ። የሦስት ሰዓቱን ስብሰባ በዙም ከተቀላቀልኩ በኋላ ልባረር እንደሆነ ሲገባኝ ቪድዮውን አቋረጬ ወጣሁ።”
ዴንቨር የሚገኘው የጉዞ ድርጅቱ በኮሮናቫይረስ ሳቢያ ገቢው ስለቀነሰ ሠራተኞችን ለማሰናበት ተገዷል። ሌሎች ኪሳራ የገጠማቸው ድርጅቶችም ተመሳሳይ እርምጃ ከመውሰድ ውጪ አማራጭ አጥተዋል።
ቀድሞ ቀጣሪና ተቀጣሪ ፊት ለፊት ተገናኝተው ያወሩ ነበር። አሁን ግን ሠራተኞች የሚባረሩት እንደ ዙም እና ማይክሮሶፍት ቲም ባሉ ቴክኖሎጂዎች ሆኗል።
ክሪስ ማሎን መርሀ ግብሮች የሚያዘጋጀው የዩኬው ‘ስፓርክ’ የተባለ ድርጅት ውስጥ ይሠራ ነበር። የድርጅቱን የማይክሮሶፍት ቲም የቪድዮ ስብሰባ ከሰው ኃይል ክፍል ተቀጣሪዎች ጋር እንደሚያካሂድ ሲነገረው፤ ከሥራ ሊባረር እንደሆነ ጠርጥሮ ነበር።
የፈራው አልቀረም ስብሰባው ላይ ከሥራህ ተሰናብተሀል ተባለ።
“በስልክ ቢሆን የሚያባርርህን ሰው ፊት አታየውም። ለቪድዮ ስብሰባ ብለህ የክት ልብስህን አድርገህ በተቀመጥክበት መባረር ግን ምቾት ይነሳል። ከሚያባርረው ሰው ጋር አንድ ክፍል ውስጥ ብትሆን ከሰውነት እንቅስቃሴው ምን ለማለት እንደፈለገ ስለምትረዳ እንግዳ ስሜት አይሰማህም።”
ክሪስ እንደሚለው፤ የአንድ ድርጅት ሠራተኞች ባጠቃላይ በቪድዮ በተሰበሰቡበት ከመባረር ይልቅ ቀጣሪ ለተቀጣሪው ለብቻው ደውሎ ቢያሰናብተው ይመረጣል።
ሩቲ ሥራዋን ከማጣቷ በፊት በተሳተፈችበት የመጨረሻ ስብሰባ 15 ሰዎች ነበሩ።
“እኔና አለቃዬ ብቻ ብንሆን ስሜቴን መረዳት ይችላል። የቡድን ስብሰባ ስለነበረ መጠየቅ የምፈልጋቸውን ጥያቄዎች ሳላነሳ ነው ስብሰባውን ያቋረጥኩት።”
ጄኤምደብሊው የተባለ የሕግ አማካሪዎች ተቋም ውስጥ የምትሠራው ሣራ ኢቫንስ እንደምትለው፤ ሥራ ቦታ ላይ የሚከናወኑ ነገሮችን ለተቀጣሪዎች ግልጽ ማድረግ አስፈላጊ ነው።
“በዙም ትልቅ ስብሰባ ጠርቶ ለሁሉም ሠራተኞች ምን እንደተፈጠረ ማሳወቅ ያስፈልጋል” ስትል ታስረዳለች።
ሠራተኞች ከተሰናበቱ በኋላ ምን እንደሚጠብቃቸው እንዲሁም ተቋሙ ስላለበት ሁኔታም ለማወቅ ግልጽነት የተሞላቸው ስብሰባዎች መካሄድ አለባቸው ትላለች።
ሣራ እንደምትለው፤ ለአንድ ሰው ስልክ ደውሎ ተባረሀል ማለት ይሻላል? ወይስ በቪድዮ ስብሰባ ከሥራ መሰናበቱን ማሳወቅ? የሚሉት ጥያቄዎች በሕግ ማዕቀፍ ምላሽ ያላቸው አይደሉም። ተቀጣሪ እንዴት ይባረር የሚለው ጉዳይ የሥነ ምግባር ጥያቄ ነው።
አሜሪካ ውስጥ በቡድን የቪድዮ ስብሰባዎች ላይ ተቀጣሪዎችን ማባረር ቢቻልም፤ በዩናይትድ ኪንግደም ግን ሕገ ወጥ ነው።
ሩቲ የዩኬ ዜጋ ብትሆን፤ አለቃዬ ያባረረኝ ፍትሐዊ ባልሆነ መንገድ ነው ብላ መክሰስ ትችል ነበር።
ቪድዮ ስብሰባዎች ሲካሄዱ መቅረጽ ይቻላል ወይ? ሌላው ጥያቄ ነው።
ኮርከር ቢኒንግ የተባለው የሕግ አማካሪዎች ድርጅት አጋር መስራች ፒተር ቢኒንግ እንደሚለው፤ ማንም ሰው የስብሰባ ቪድዮ ከመቅረጹ በፊት በይፋ ማስታወቅ አለበት።
አንድ ሰው በቪድዮ የተባረረው ኢ-ፍትሐዊ በሆነ መንገድ መሆኑን ለማሳየት የቪድዮ ማስረጃ ለመጠቀም ቢፈልግም፤ ሕጋዊነቱ ላይ ጥያቄ ሊነሳ የሚችልባቸው አጋጣሚዎች እንዳሉ ባሙያው ያስረዳል።
ቪድዮ የሰው ለሰው ግንኙነትን ለውጧል። ይህም በሥራ ቦታ ላይ ማጥላቱ አልቀረም።
የሥነ ልቦና አማካሪዋ ፐርን ካንዶላ እንደሚሉት፤ አንድ ሰው ከሥራ ሲሰናበት ፍትሐዊ በሆነ መንገድ ግልጽ መረጃ ሊሰጠው ይገባል።
“የአንድን ሰው አይን እያዩ ማባረር ምቾት ሊነሳ ይችላል። ንዴቱና ቁጣው ፊቱ ላይ ይነበባልና። ሆኖም ግን ግልጽ ሆኖ መነጋገር ያዋጣል።”