ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
“ኮሮናቫይረስን ለሦስት ሳምንታት በሦስት ሆስፒታሎች ታገልኩት”
ሦስት ልጆች በዊልቸር ያለ አባታቸውን እየቦረቁ ሲቀበሉ የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምስል በማኅበራዊ ሚዲያ በሺህዎች ታይቷል።
ልጆቹ የጃክ ማክሊሀህ ናቸው። ቪድዮው የተቀረጸው በሦስት የተለያዩ ሆስፒታሎች ለሦስት ሳምንት የኮሮናቫይረስ ምርመራ ተደርጎለት ወደ ቤቱ ሲገባ ነው።
ድሩሞር በተባለች ከተማ ይኖራል። የአይቲ ባለሙያ ነው።
ህክምናውን ሲያጠናቅቅ፤ በክሪያጋቮን፣ በማተር ሆስፒታል እና በናይቲንጌል ሆስፒታል ኦፍ ቤልፋስት እንክብካቤ ያደረጉለትን የህክምና ባለሙያዎችን በአጠቃላይ አመስግኗል። ምስጋናውን በማኅበራዊ ሚዲያም አጋርቷል።
ሆስፒታል የገባው በእናቶች ቀን ነበር። አገግሞ ከወጣ በኋላም ድካም እንደሚሰማው ይናገራል።
“ትንሽ በእግሬ ስንቀሳቀስ ይደክመኛል፤ ሆስፒታል ሳለሁ ከስቻለሁ፤ ሰውነቴን ዳግመኛ መገንባት አለብኝ” ይላል።
ህመሙ የጀመረው ሚያዝያ ላይ ነው። አስር ቀን ራሱን አግልሎ ቤቱ ባለው ቢሮ ተቀመጦ ነበር። ከሚስቱ፣ ከሦስት ልጆቹና ከአማቹ ጋር አይገናኝም ነበር።
በሽታው ተባብሶ ለመተንፈስ ሲቸገር ሆስፒታል ተወሰደና በጽኑ ህሙማን ማቆያ ገባ። ወቅቱን እንዲህ ያስታውሳል. . .
“ለባለቤቴ ደወልኩላትና ጠዋት ህሊናዬን ስቼ ልታገኚኝ ትችያለሽ አልኳት። ወደ ጽኑ ህሙማን ማቆያ ክፍል እየተወሰድኩ ነው፤ ቬንትሌተርም ተደርጎልኛል ብዬም ነገርኳት። ከዚያ ከሁለት ሳምንት በኋላ ራሴን ሌላ ሆስፒታል ውስጥ አገኘሁት።”
ከሆስፒታሉ የወጣው በሦስተኛ ሳምንቱ ቢሆንም የተፈጠረውን ነገር በቅጡ አያስታውስም።
ባለቤቱ ያኔ የየዕለት ውሎ ማስታወሻ ትይዝ ነበር። የጤና ሁኔታውን፣ የጻፈችለትን ደብዳቤ፣ አስቸጋሪ የነበረውን ወቅት እና ተስፋ የጣለችበትን ጊዜም በጽሁፍ መዝግባለች።
ለፋሲካ ቤቱ ቢመለስም ሙሉ በሙሉ አላገገመም ነበር። ዶ/ር ማይክል መኪያና እንደሚሉት፤ ለማገገም ጊዜ ይወስዳል።
“በቫይረስ ሳቢያ የተከሰተ በሽታ የያዛቸው ሰዎች ቬንትሌተር የሚያስፈልጋቸው ለሁለት ወይም ቢበዛ ለአራት ቀን ነበር። አሁን ግን ከ14 እስከ 20 ቀን ሲያስፈልጋቸው እናያለን” ይላሉ።
ጃክ በቤቱ መናፈሻ ከባለቤቱ ጋር የውሎ መዝገቧን ያገላብጣል። ወደ ቤት ከተመለሰ በኋላም ለማገገም ቀላል እንዳልነበረ ይናገራል።
“እናቴ ከዓመታት በፊት ታማ የገዛሁላትን ዊልቸር ነው የተጠቀምኩት። መጸዳጃ ቤት፣ ማዕድ ቤትም ለመሄድ እሱን እጠቀም ነበር። ሁሉም ቅርብ ቢሆኑም የምንቀሳቀሰው በዊልቸር ድጋፍ ነበር” ሲል ጃክ ያለፈበትን ያስታውሳል።
ዶክተሩ እንደሚሉት ከሆነ፤ የትኛው ሰው ከበሽታው በቶሎ እንደሚያገገም ማወቅ አዳጋች ነው።
ጃክ የአሁኑን የበጋ ወቅት ያለፈውን ጊዜ በማስታወስ ማሳለፍ ይፈልጋል። ምን እንደገጠመው እና ገጠመኙ ሕይወቱን እንዴት እንደቀየረውም ያሰላስላል።
“በጽኑ ህሙማን ማቆያ ሆኜ፤ ቤቴ መመለስ አለብኝ ብዬ ሳስብ አስታውሳለሁ” ይላል።
ምኞቱ ሰምሮ ቤቱ በመመለሱ ደስተኛ ነው።
“ከቤተሰቤና ከልጆቼ ጋር መሆን እጅግ አስደሳች ነው። ምንም እንኳን ከቤት ባንወጣም አብረን መሆናችን ያስደስታል። በሕይወት የሚያስፈልገው ነገር ምን እንደሆነም አሳይቶናል።”