ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በሩሲያ 380ሺ ሰዎች በኮሮና ተይዘው ሟቾች እንዴት 4ሺ ብቻ ሆኑ?
ሩሲያ ከዓለም 3ኛ ናት፤ በኮሮናቫይረስ በተያዙ ሰዎች ብዛት፡፡ ከላይ ያሉት አሜሪካና ብራዚል ናቸው፡፡
አሜሪካ 1ሚሊዮን 7መቶ ሺህ ተይዞባት ትናንት የሞቱባት ዜጎች ቁጥር 100 ሺ ማለፉን ተናግራለች፡፡ ብራዚል 440ሺ ተይዞባት 27ሺ ዜጎች ሞተውባታል፡፡
ሩሲያ 380ሺህ ዜጎች ተይዘውባት እንዴት የሟቾች ቁጥር 4ሺ ብቻ ሆነ የሚለው የብዙዎች ጥያቄ ነው፡፡
ተቺዎች ሩሲያ የምታወጣው ቁጥር ተአማኒ አይደለም ሲሉ ሩሲያ በበኩሏ በተህዋሱ የሚያዙ ሰዎችን ቶሎ መርምሬ ስለምደርስባቸው ነው የሟቾች ቁጥር ትንሽ የሆነው ትላለች፡፡
ዛሬ የሞስኮ ባለሥልጣናት የቁጥር ማሻሻያ ማድረጋቸው ተሰምቷል፡፡ በሚያዚያ ወር በሞስኮ ከተማ በኮቪድ-19 የሞቱት ሰዎች ቁጥር 639 ብቻ ነው ያልነው ትክክል ስላልሆነ 1ሺህ 561 በሚል ይስተካከል ብለዋል፡፡
እነዚሁ የሞስኮ ባለሥልጣናት የሟቾችን ቁጥር አሳንሳችኋል በሚል ከነጻው ሚዲያ ሲተቹ የነበሩ ናቸው፡፡ ያን ጊዜ የመለሱት ‹‹ሚዲያው ሐሳዊ ነው፤ መቅጠፍ ልማዱ ነው›› የሚል ነበር፡፡ ዛሬ ተነስተው ለምን የቁጥር ማሻሻያ ለማድረግ እንደተገደዱ ግልጽ አይደለም፡፡
አሁን በስፋት እየተነሳ ያለው ጥያቄ በሞስኮ ብቻ ሳይሆን በመላው ሩሲያ የሟቾች ቁጥር 4ሺ 142 ብቻ እንዴት ሊሆን ይችላል የሚለው ነው፡፡
መንግሥት አሁንም ይህን ጥያቄ የሚያነሱ መገናኛ ብዙኃንን መርዶ ናፋቂዎች እያለ ይተቻል፡፡ ‹‹ዜጎቼ የማይሞቱት በስፋት የኮቪድ ምርመራን ተደራሽ ስላደረኩ ነው›› ትላለች ሩሲያ፡፡
ሞስኮ የኮቪድ ወረርሽኝን አስታካ በርካታ ጋዜጠኞችን በሰበብ አስባቡ እያሰረች ትገኛለች፡፡ ይህም ከምዕራቡ ውግዘትን እያስከተለባት ይገኛል፡፡
ሞስኮ የሟች ቁጥር ማስተካከያ ለምን አደረገች?
ባለሥልጣናቱ ለዚህ የሰጡት ምላሽ በኮቪድ እንደሞቱ ያላወቅናቸው ሰዎች ዘግይተን ምርመራ ስናደርግ በበሽታው መያዛቸውን ስለደረስንበት ነው ብለዋል፡፡ በሬሳዎች ላይ ያደረጉት ምርመራ ተጨማሪ ዜጎች በኮቪድ ስለመያዛቸው እንዲያውቁ እንዳደረጋቸው ነው የሚናገሩት፡፡
169 ሰዎች ኮቪድ የለባቸውም ተብለው ከሞቱ በኋላ በሬሳቸው ላይ የተደረገ ምርመራ ፖዘቲቭ ሆነው ተገኝተዋል፤ እንደ ባለሥልጣናቱ መረጃ፡፡
በተጨማሪም በሚያዚያ በሌሎች በሽታዎች ሞተዋል የተባሉ 756 ሰዎች ሲጣራ በኮቪድ መሞታቸው ተደርሶበታል፡፡
የቢቢሲዋ ባልደረባችን ሳራ ሬይንስፎርድ እንደምትገምተው ይህ በሞስኮ ከተማ በሬሳዎች ላይ የተደረገ ምርመራ ቁጥሩን በዚህ ደረጃ የሚቀያይረው ከሆነ በመላው ሩሲያ የሟቾች ቁጥር ከተገለጸው በብዙ እጥፍ ሊሆን ይችላል፡፡
ባለሥልጣናቱ በበኩላቸው የግንቦት ወር የሟቾች ቁጥር በዚህ መረጃ እንዳልተካተተ ተናግረዋል፡፡