ኮሮናቫይረስ፡ የበርሊን ማራቶን መቼ እንደሚካሄድ አልታወቀም

ባለፈው ዓመት በበርሊን ማራቶን 47000 ሰዎች ያህል ታሳትፈዋል

በአለማችን ከሚካሄዱ ስድስት ታላላቅ የስፖርት ውድድሮች መካከል የሆኑት የበርሊንና የለንደን ማራቶን በተያዘላቸው ጊዜ እንደማይካሄዱ ታወቀ።

የበርሊን ማራቶን በጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር ሴፕቴምበር 27 ቀን 2020 ይካሄዳል ተብሎ የታቀደ ቢሆንም ጀርመን የእንቅስቃሴ ገደቧን እስከ ጥቅምት ወር መጨረሻ ድረስ በማራዘሟ የተነሳ እንደማይካሄድ ታውቋል።

የውድድሩ አዘጋጆች በመግለጫቸው በታቀደለት ጊዜ "አይካሄድም" ከማለት ውጭ ለሌላ ጊዜ ይተላለፍ አይተላለፍ የገለፁት ነገር የለም።

ቀጣዩን እርምጃ እንደሚያስተባብሩም ጨምረው ገልፀዋል።

የበርሊኑ ውድድር ሊካሄድ ታቅዶ የነበረው ከለንደኑ ማራቶን በፊት አንድ ሳምንት ቀደም ብሎ ሲሆን በኋላ ላይ ግን የለንደኑ ማራቶን እኤአ ወደ ኦክቶበር 4 ተገፍቷል።

የለንደኑ ማራቶን በመጀመሪያ እቅዱ መሰረት በዚህ ሳምንት መጨረሻ ለመካሄድ እቅድ ተይዞ የነበረ ሲሆን በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ነው ወደ ሌላ ጊዜ የተላለፈው።

የበርሊን ማራቶን አዘጋጆች በቅርብ ጊዜ እንዲካሄድ የሚወስኑ ከሆነ በሕዳር ወር አጋማሽ ሊሆን ይችላል የተባለ ሲሆን በዚያ ወቅትም ግን የኒው ዮርኩ ማራቶን እንደሚካሄድ የወጣው የጊዜ ሰሌዳ ያሳያል።

የበርሊን ማራቶን ፈጣን ውድድር ሲሆን ባለፉት አመታት በወንዶች ማራቶን ውድድር ሰባት ጊዜ ክብረ ወሰን ተሻሽሎበታል።

እአአ በ2018 ኬንያዊው ኤሉድ ኪፕቾጌ ሁለት ሰዓት ከአንድ ደቂቃ ከ39 ሰከንድ በመግባት ክብረወሰኑን በእጁ አስገብቷል።

ባለፈው አመት ቀነኒሳ በቀለ ሁለተኛው ፈጣን ሰዓት ሆኖ የተመዘገበውን 2:01:41 በመግባት ያሸነፈ ሲሆን በዚህ ዓመት ከኪፕቾጌ ጋር በለንደን ማራቶን ለመፎካከር ቀጠሮ ነበራቸው።

ጀርመን ከዩናይትድ ኪንግደም አንጻር አነስተኛ ሰዎች ብቻ ነው የሞቱባት።

ጆንስ ሆፕኪንስ ባጠናቀረው መረጃ መሰረት በጀርመን 4,948 ሲሞቱ በዩናይትድ ኪንግደም 17,337 ሞት ተመዝግቧል። በዚህም የተነሳ ጀርመን በከፊል የእንቅስቃሴ ገደቧን አንስታለች።

ኮሮና