ለተከታታይ ስምንት ዓመታት የህዳሴ ግድቡን ቦንድ የገዙት ኢትዮጵያዊ

ኪሮስ አስፋው በዓብዪ ዓዲ ሆስፐ[ኢታል ፊዝዮቴራፒስት በመሆን ያገለግላል

የፎቶው ባለመብት, Kahsay Gebru

የምስሉ መግለጫ, "የአባይ ውሃ ለኔ ፀበሌ ነው፤ የኢትዮጵያ ህዝብም ፀበል ነው"

ወላጆቹ ስድስት ልጆች ወልደዋል፤ ሁሉም ሊያድጉላቸው ግን አልቻሉም። አንድ በህይወት የተረፈላቸውን ልጃቸውን ግን፤ እንደ ሴት 'አንቺ' ብለው እየጠሩ አሳደጉት። ሰባት ዓመት ሲሞላው ደግሞ ኪሮስ የሚል ስም አወጡለት።

እናቱ ግን፤ ልጄ አንድ ብቻውን ስለሆነ 'ሁለት ሰባት [14 ዓመት] እስኪሞላው አንቺ ነው የምለው' ብለው አንቺ ማለታቸውን ቀጠሉ።

'ልክ 14 ዓመት ሲሞላኝ፤ እናቴ 'አንተ' ብላ ጠራችኝ፤ በዛው ለትግል ወደ በረሃ ወጣሁ' የሚሉት አቶ ኪሮስ አስፋው፤ በ1972 ዓ.ም ህወሓትን እንደተቀላቀሉ ያስታውሳሉ።

ከሁለት አመት በኋላ ግን የሻእቢያ ሰራዊትን ለመደገፍ ሳሕል ላይ በተካሄደው ጦርነት ለመሳተፍ ከሄዱት ታጋዮች አንዱ ስለነበረ፤ ጭንቅላታቸው ላይ ከባድ ጉዳት ደረሰባቸው።

በዚህ ጉዳት፤ ለስድስት ወራት ራሳቸውን ስተው ቆዩ ፤ አንድ አይናቸውም በዚሁ አደጋ ጠፋ። ከስድስት ወራት ህክምና በኋላ ያገገሙት አቶ ኪሮስ፤ ወደ ትግራይ ተመልሰው ፊደል ቆጥረው፣ ዳግም ወደ ኤርትራ በመሄድ የህክምና ትምህርት አጥንተው ተመለሱ

ከ1984 ዓ.ም ጀምሮ በትግራይ ማእከላይ ዞን አብዪ አዲ ከተማ በሚገኘው የአብዪ አዲ ሆስፒታል ነርስ ሆነው ሲሰሩ ቆይተው አሁን በፊዚዮቴራፒ ማዕከል እያገለገሉ የሚገኙ አካል ጉዳተኛ ናቸው አቶ ኪሮስ።

ኪሮስ አስፋው ለተከታታይ 8 አመታት ያለማቋረጥ ለታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ የሚውል ቦንድ በየወሩ በግማሽ ወርሃዊ ደመወዛቸው እየገዙ ይገኛሉ።

ቢቢሲ፤ ዓብዪ ዓዲ ላይ 'ኪሮስ ቦንድ' ብለው የሚጠሩዎት ሰዎች እንዳሉ ሰማሁ፤ ለምንድን ነው?

ኪሮስ አስፋው፤ የድሮ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ ህያው ከሚያደርጉት ስራዎቹ አንዱ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ላይ የወሰደው ቆራጥ ውሳኔ ነው። የግድቡ ግንባታ ሲያበስሩ ካላቸው ሦስት ነገሮች በገንዘብ፣ ጉልበትና ሞያ ራሳችን የምንገነባው ግድብ ነው ማለቱን መቼም አልረሳም።

በዚህ ምክንያት ግድቡ ተሰርቶ እስኪያልቅ የወርሃዊ ደሞዜን ግማሹ እሰጣለሁ የሚል ቃል ገባሁ። ቃሌን በማክበር እነሆ ስምንት አመት ሙሉ ቦንድ እየገዛሁ ነው።

ቢቢሲ፤ ምን ያክል ቦንድ አለዎ ማለት ነው?

ኪሮስ አስፋው፤ ባጠቃላይ 95 ቦንድ ገዝቻለው፤ የመጨረሻዋ 25 የካቲት 2012 የገዛኋት ናት።

ቢቢሲ፤ ይሄን ያክል ለቃልዎ ተገዢ እንዲሆኑ ያስቻለዎት ምንድን ነው?

ኪሮስ አስፋው፤ ቃሌ ለአባይ ነው የሰጠሁት። የበረሃው ትግልም የገባሀው ቃል እንደማይታጠፍ አስተምሮናል። የኢትዮጵያ ህዝብ ግድቡ እንዲሰራ ይፈልጋል፤ ተሰርቶም ለህዝብ ጥቅም ይውላል ብዬ አምናለሁ። እኔ ይሄ ሁሉ ቦንድ ለመግዛት ገንዘብ ተርፎኝ ወይም የሚያግዘኝ ሰው ኖሮ ሳይሆን፤ አባይ ተገንብቶ ጥቅም ላይ ሲውል እኔም ተጠቃሚ እሆናለሁ የሚል እምነት ስላለኝ ነው።

ቢቢሲ፤ ከግድቡ እንደ ግለሰብ ምን እጠቀማለሁ ይላሉ?

ኪሮስ አስፋው፤ በቀጥታ ተጠቃሚ ባልሆንም፤ የኢትዮጵያ ህዝብ ተጠቃሚ ሲሆን እኔም እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ጥቅሙ ይደርሰኛል እላለሁ። ግድቡ ወደ ሚገነባበት ቦታ ሂጄ ምን ይዤ መጣሁ መሰለሽ፤ አንድ ድንጋይና ከወንዙ በላስቲክ ኮዳ የቀዳሁት ውሃ ይዤ መጥቻለሁ።

ቢቢሲ፤ ለምን?

ኪሮስ አስፋው፤ ድንጋዩ ግድቡ የሚገነባበት ቦታ እጅግ አስቸጋሪና ጠንካራ መሆኑን፤ እኛም ይህን እውን ለማድረግ ያለን እምነት ጽኑ መሆኑን ለማሳየት ነው። ውሃው ግን የአባይ ጸበል ነው። አንድ ሰው የሚካኤል፣ የማርያም ወዘተ . . . ብሎ የሚያምንበት ጸበል ይጠቀማል። እኔ ከአባይ ያመጣሁት ውሃ ደግሞ፤ የኢትዮጵያ ህዝብ መድሃኒት ነው ብዬ ስላመንኩ ነው።

ቢቢሲ፤ እሺ ቅድም ወደ ጀመርነው ወሬ እንመለስ

ኪሮስ አስፋው

የፎቶው ባለመብት, Kahsay Gebru

ኪሮስ አስፋው፤ መልካም፤ ስለዚህ እንደ ሰው አስፈላጊውን ገንዘብ ከህዝቡ ተሰብስቦ ግድቡ ይገነባል። ከተገደበ በኋላ ደግሞ የኢትዮጵያ ህዝብ ይጠግባል፤ ከምን ነገር በላይ ግን የመለስ አደራ መወጣት እፈልጋለሁ። የኢትዮጵያ ችግር ገንዘብ ሳይሆነ፤ ፖለቲካና ሰላም ማጣት ነው።

እንደጀመርነው ብንቀጥል ኑሮ አሁን ሁለተኛ አባይ ጀምረን ነበር እላለሁ። በተያዘለት ጊዜ አልቆ፣ ተመርቆ ስራ ቢጀምር ብዙ ተጠቅመን ነበር። ግን ባለው የፖለቲካ አመራር ችግር እስከ አሁን ወደ ኋላ እየተጎተተ ሲደናቀፍ ቆይቷል። ችግሮች ቢገጥሙንም ግን ይገነባል።

ቢቢሲ፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ ወደ ስልጣን እንደመጡ ግድቡ የፕሮፖጋንዳ ስራ ሲሰራበት እንጂ ሲገነባ እንዳለነበረ በመግለጽ፤ ገንዘቡም በሙስና መጥፋቱን ጠቁመዋል። በዚህ ምክንያት በ10 አመት እንኳ አያልቅም ብለው ነበር። ፕሮጀክቱን ሲመሩ የነበሩት ኢንጀነርም በመኪናቸው ውስጥ ሞተው ተገኝተዋል። በወቅቱ እነዚህን ነገሮች ሲሰሙ ተስፋ አልቆረጡም?

ኪሮስ አስፋው፤ ልክ ነው፤ ይህ ስሰማ አዝኛለሁ። ከዚህ ሁሉ ልብ የሚሰብር ንግግር በኋላ ቦንድ መግዛት ማቆም አላቃተኝም። ግን ይህ አመራር የአባይ ግንባታ የማያምንበት ከሆነ፤ በግድቡ አስፈላጊነት እምነት ያለበት አመራር መጥቶም ቢሆን ያልቃል የሚል እምነት ማስቀደም እንዳለብኝ አወቅኩ።

የኢንጅነሩና የመለስ ሞት ለእኔ አንድ አይነት ናቸው፤ በቃ የኢንጅነር ስመኘው በቀለ መሞት ግድቡ እንዳይሰራ ማድረግ ይሆን እንዴ የሚል ስሜት ፈጥሮብኛል። በዚህ ደንግጬ፣...አዝኜ፣ አልቅሻላሁ፤ ግን መልሶ እንጽናናለን። እኔ ታጋይ ነኝ። በትግል ወቅት ታላላቅ መሪዎቻችን ሲሞቱ አዝነን እናለቅስና፤ አሁንስ ማን ይመራናል እንል ነበር። ሆኖም ግን ሌሎች ጀግና መሪዎች ይተኩና ትግሉን መርተው፣ አሸንፈናል። ስለዚህ ግድቡን መርተው ማሳካት የሚችሉ ጀግና ለመኖራቸው ተስፋ አልቆርጥም። አባይም በህዝብ ተሳትፎ ያልቃል፤ እነሱ ወደ 'ኔጋቲቭ' እኛ ደግሞ ወደ 'ፖዘቲቭ' እየገባን መንገድ ላይ እንገናኛለን።

ቢቢሲ፡ ከማን ጋር?

ኪሮስ አስፋው፤ የአባይ ግድብ እንዳይገነባ ሲያደርጉ ከነበሩና፣ ገንዘባቹ ተበልቷል በማለት ተስፋ እንድንቆርጥ ካደረጉን ጋር።

ቢቢሲ፤ አሁን ግን በወሬ ብቻ አይደለም፤ ከግብጽ፣ አሜሪካና ሌሎች ትልልቅ አለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ እየገነባችው ያለችውን ግድብ የመጠቀም መብቷን ወደ ምታጣበት መስመር እንድትገባ ጫና እየተደረገባት ነው ብለው ምሁራን እየገለጹ ነው፤ ይህ እርሶን ጨምሮ ህዝቡ ለአመታት የከፈለው ገንዘብ ሜዳ ላይ እንዳይቀር አያሰጋዎትም?

ኪሮስ አስፋው፤ ለእኔም በግሌ እኮ ብዙ ነገር ደርሶብኛል። ከህጻን ልጅ ጀምሮ ብዙ ሰዎች እየመጡ አባይ ተሽጧል፣ አባይ ተከልክሏል፣ አባይ ተወርሷል፣ ገንዘብህ ጠፍቷል ይሉኛል። መሪዎቻችን በግድቡ ዙርያ ቆራጥ የሆነ አመራርና አቋም ባለማሳየታቸው አሁን እነዚህ አገራት እየፈከሩ ነው፤ ግን ትርጉም ስለ ሌለው ይሄም ያልፋል።

ቢቢሲ፤ እንዴት ትርጉም አይኖረው? ሃያላን አገራት አይደሉም?

ኪሮስ አስፋው፤ ቢሆኑስ? የእኔ የቃል እምነት መለስ ያልቃል ማለቱ ነው። አሜሪካም ትሁን ግብጽ እንዲሁም ከራሳችን የግድቡን ግንባታ ሊያደናቅፉን ይችላሉ፤ ግን እንሻገረዋለን የሚል ጠንካራ እምነትና ጽናት እንዲኖረን በማድረግ አበርትቶን አልፏል። እኔም ከዚህ ቃል ነው የምነሳው፤ በማንኛውም አጋጣሚ ያልቃል የሚለው እምነቴን ይዤ ነው የምጓዘው።

ቢቢሲ፤ ኑሮ በተወደደበት [በዚህ] ወቅት ግማሽ ወርሃዊ ደመወዝ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ብሎ መክፈል አይከብድም?

ኪሮስ አስፋው፤ 'ሃብታም እንደሚበላለት፤ ድሃም እንደሆነለት' ይላሉ ወላጆቻችን። ግድቡ ሲያልቅ በተዘዋዋሪ ገንዘቡ እኔ ጋር ይደርሳል። እግዜር ይመስገን ሳልበላ አልዋልኩም፣ አላደርኩም። ልጆቼም ይማራሉ፣ ቤትም አለኝ። ሁሌም የምልከው ገንዘብ ደግሞ፤ ልክ ወደ ልጄ የላኩት ያክል ነው የሚሰማኝ። ስለ ሆነም አካባቢዬ ያለው ባንክ ማረጋገጫ ቦንድ ቢሰጠኝም፤ ስልክ ደውዬ ግን ደርሷል ብየ ጠይቄ አረጋግጣለሁ። እርካታ ይሰጠኛል።

ቢቢሲ፤ ግድቡ የሚጠይቀው ገንዘብ ግን በመቶዎች ሳይሆን በቢሊዮን ዶላር የሚገመት ነው

ኪሮስ አስፋው፤ አውቃለሁ፤ ግን የኢትዮጵያ ህዝብም እኮ በመቶ ሚሊዮን የሚቆጠር ነው። ቦንድ መግዛት የቻለውን ከገዛ፣ ያልቻለውን ደግሞ በቀን አንድ ብር ከሰጠ በአመት ስንት ሚሊዮን ብር ይገኛል? ይህ በየአመቱ ተደምሮ ግድቡን መገንባት የሚችል ገንዘብ ይፈጥራል።

ቢቢስለዚህ?

ኪሮስ አስፋው፤ ስለዚህማ ግድቡ የሚገነባው፤ ገንብተን መጨረስ እንችላለን የሚል እምነት በህጻን፣ አዋቂ፣ ወጣትና የአገር መሪ ልቦና ውስጥ መኖር አለበት። የተበላሸው ፖለቲካዊ አስተሳሰባችንም መለወጥ ይገባዋል። ለብሄርና ሃይማኖታዊ ግጭት፣ መከፋፈልና መራራቅ የዳረገንን ፖለቲካ መስበር አለብን። የኢትዮጵያ ህዝብ ከሰሞኑ ያሳየውን ወኔ አስደስቶኛል፤ መንግስትም ወደ ፊት ባናውቅም አሁን አሜሪካ ያቀረበችለት ሰነድ ባለመፈረሙ እፎይታ ሰጥቶኛል።

በቀጣይም አንፈተንም ማለት ግን አይደለም፤ አሁን የምናያቸው ችግሮች በሙሉ ተደምረው ግን ተስፋ የምናደርግበት የህዳሴአችን ግድብ የሚጎዳ መሆን የለበትም፤ ያ ያሰጋኛል። የፈለገው ፖለቲካዊ ልዩነት ቢፈጠርም አባይ ግን አንድ ሊያደርገን ይገባል። ፈተናዎች አሸንፈን የግድቡ ፍጻሜ የምናይበት ቀንም በተስፋ እጠብቃለው።