ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ለዶናልድ ትራምፕ ቅሬታ ምላሽ ሰጡ

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ

የፎቶው ባለመብት, AFP

ባሳለፍነው ሳምንት ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ በአገራት መካከል ሊከሰት የነበረን 'ትልቅ ጦርነት' ማስቆማቸውን እና እርሳቸው ጦርነት እንዳይከሰት በማድረጋቸው የአገሪቱ መሪ የኖቤል ሽልማትን እንዲያገኙ ስለማስቻላቸው ገልጸው ነበር።

በርካቶችም የፕሬዝዳንቱ ንግግር ስለ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ነው የሚል ድምዳሜ ላይ ደርሰዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይም ከዚሁ ጋር በተያያዘ ከጋዜጠኞች ለተነሳላቸው ጥያቄ ምላሽ ሰጥተዋል።

ለይፋዊ ጉብኝት በደቡብ አፍሪካዋ ዋና ከተማ ፕሪቶሪያ የነበሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ አስተያየት እንዲሰጡ ሲጠየቁ፤ እኔ ስለ ሽልማቱ አካሄድ የማውቀው ነገር የለም ብለዋል።

''የኖቤል ሸልማት ኮሚቴው አሸናፊዎችን ለመመርጥ ከግምት ውስጥ ስለሚያስገባቸው መስፈርቶች ምንም የማውቀው ነገር የለም። ፐሬዝዳንት ትራምፕ ቅሬታ ካላቸው ኦስሎ ወደሚገኘው ኮሚቴ ሄደው ቅሬታቸውን ማሰማት ይችላሉ።''

አክለውም ''እኔ ሽልማቱን ለማግኘት ብዬ አይደለም የምሠራው። በቀጠናው በጣም ወሳኝ ነገር ለሆነው ሰላም ነው የምሠራው'' ብለዋል።

ፕሬዝደንት ትራምፕ በንግግራቸው ስለ የትኛው አገር መሪ ወይም በየትኞቹ አገራት መካከል ሊከሰት ስለነበረው 'ትልቅ ጦርነት' በቀጥታ ያሉት ነገር ባይኖረም፤ በርካቶች ንግግራቸውን ከኢትዮጵያው መሪ እና የኖቤል ሽልማት አሸናፊ ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አህመድ እንዲሁም ከግብጽ እና ኢትዮጵያ ጋር አገናኝተውታል።

ከግብጽ በተጨማሪ ጉዳዩን ከኤርትራ እና ኢትዮጵያ ጋር ያያዙትም አሉ።

ፕሬዝዳንቱ በንግግራቸውም እንዲህ ሲሉ ተደምጠዋል።

''ስለ የኖቤል የሰላም ሽልማት ልነግራችሁ እችላለሁ፤ ከስምምነት ደረስኩኝ፤ አገር አዳንኩኝ፤ እንደሰማሁት የዚያ አገር መሪ 'አገሩን በመታደጉ' የኖቤል ሽልማት ማግኘቱን ሰማሁ። እኔ በዚህ ላይ ተሳትፎ ነበረኝ? አዎ!። ግን እኛ እውነታውን እስካወቅነው ድረስ ምንም አይደለም። ትልቅ ጦርነት ነው ያስቀረሁት። ሁለት አገሮችን ነው ያዳንኩት።''

ጠቅላይ ሚንስትሩ የኖቤል ሽልማትን ያሸነፉት በዋነኝነት በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል ሠላም እንዲሰፍን ላበረከቱት አስተዋጽኦ መሆኑን በማስታወስ ትራምፕ ደግሞ በዚህ ላይ የነበራቸው ድርሻ ምንም ነው ያሉ በርካቶች ናቸው።