ኮንጎ፡ ከ6ሺህ ሰዎች በላይ የሞቱበት የኩፍን ወረርሽኝ

የፎቶው ባለመብት, AFP/Getty
በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በኩፍኝ ወረርሽኝ የሞቱ ሰዎች ቁጥር 6ሺህ ማለፉን የዓለም ጤና ድርጅት አስታወቀ።
የዓለም ዓቀፍ ጤና ድርጅት ይህ ወረርሽኝ በስፋትና በፍጥነት የተዛመተ መሆኑን በመግለጽ ከዓለማችን ትልቁ ነው ብሎታል።
እ.ኤ.አ. በ2019 ብቻ 310 ሺህ ሰዎች በኩፍኝ በሽታ የተጠረጠሩ ሰዎች መመዝገባቸውን ድርጅቱ ጨምሮ አስታውቋል።
የኮንጎ መንግሥት ባለፈው መስከረም ወር አስቸኳይ የኩፍኝ መከላከያ ክትባት መርሀ ግብርን ይፋ አድርጓል።
እንደ ዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት መግለጫ ከሆነ በ2019 ብቻ እድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች የሆነ ከ18 ሚሊየን በላይ ሕፃናት ተከትበዋል።
ነገር ግን ደካማ የሆነ መሰረተ ልማት፣ በጤና ተቋማት ላይ የሚደርስ ጥቃትና ተከታታይ የሆነ የጤና እንክብካቤ አለመኖሩ የበሽታውን በፍጥነት መዛመት ሊገታው እንዳልቻለ ተገልጿል።
በኮንጎ የሚገኙ 26 ግዛቶች ውስጥ ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር ላይ በሽታው በወረርሽኝ ለመልክ መከሰቱ ከተነገረ ጊዜ ጀምሮ በርካታ በኩፍኝ የተያዙ ሰዎች ተመዝግበዋል።
በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ያለው የኩፍኝ ወረርሽኝ በማዕከላዊ አፍሪካ ካለው የኢቦላ ወረርሽን በሁለት እጥፍ የሚልቁ ሰዎችን እየገደለ ነው።
"ይህንን ወረርሽን ለመቆጣጠር የአቅማችንን ሁሉ እያደረግን ነው" ያሉት የዓለም ጤና ድርጅት የአፍሪካ ዳይሬክተር ዶ/ር ማትሺድሶ ሞዬቲ ናቸው።
"በትክክል ውጤታማ ለመሆን ግን ማንኛውም ሕጻን በቀላሉ በክትባት መከላከል በሚቻል በሽታ እንዳይሞት ማድረግ አለብን። አጋሮቻችን በፍጥነት ድጋፋቸውን እንዲያደርጉልን ጥሪ እናቀርባለን" ብለዋል።
የዓለም ጤና ድርጅት በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እድሜያቸው ከ6 እስከ 14 የሆኑ ሕፃናትን በመከተብ መከላከሉን ለማጠናከር ተጨማሪ 40 ሚሊየን ዶላር ያስፈልገኛል ሲል ተናግሯል።
በዓለም ላይ በየዓመቱ 110ሺህ ሰዎች በኩፍኝ በሸታ ተይዘው ይሞታሉ ሲል ድርጅቱ በመግለጫው ላይ አስታውቋል።


















