ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኢራን ከዚህ በኋላ ለአሜሪካና አጋሮቿ ማዕቀብ እንደማትገዛ አስታወቀች
ኢራን ከዚህ በኋላ ለ2015 [በግሪጎሪ ኦቆጣጠር] የኒውክሌር ስምምነት እንደማትገዛ አስታውቃለች።
ኢራን ባወጣችው የአቋም ሃተታ በስምምነቱ መሠረት የተጣሉባት ማዕቀቦች ከዚህ በኋላ እንደማይገዟትና እንዳሻት እንደምትንቀሳቀስ አስታወቃለች።
የኢራን ካቢኔ ዋና ከተማዋ ቴህራን ላይ ከመከረ በኋላ ነው አቋሙ የወጣው።
ኢራናዊው ኃያሉ የጦር ጄኔራል ቃሲም ሶሌይማኒ በትራምፕ ትዕዛዝ ባግዳድ ውስጥ መገደላቸውን ተከትሎ አሜሪካና ኢራን ውጥረት ውስጥ ናቸው።
ባግዳድ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ዕሁድ አመሻሹን ጥቃት እንደተሰነዘረበትም ተሰምቷል። የቢቢሲ ምንጮች እንደሚሉት አራት ጊዜ ኤምባሲውን ዒላማ ያደረጉ ጥቃቶች ተሠንዝረዋል። የደረሰ አደጋ ስለመኖሩ የታወቀ ነገር የለም።
በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ኢራናውያን ለጄኔራል ሶሌይማኒ የጀግና አሸኛኘት ለማድረግ ጎዳናዎችን ሞልተው ታይተዋል። የጄኔራሉ ቀብር ማክሰኞ ዕለት ይከናወናል ተብሎ ይጠበቃል።
አሜሪካ ኢራቅ ውስጥ 5000 የጦር ሠራዊት አላት። ወታደሮቹ አይኤስ የተሰኘውን ታጣቂ ቡድን ለመዋጋት በሥፍራው የከተሙ ናቸው።
ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ በትዊተር ገፃቸው ባስተላለፏቸው በርካታ መልዕክቶች ኢራን የአሜሪካንን የጦር ሠፈሮች ልታጠቃ ብትሞክር ምላሹ የከፋ እንደሚሆን አስጠንቅቀዋል።
2015 ላይ ዩናይትድ ኪንገደም፣ ፈረንሳይ፣ ሩስያ፣ ቻይና፣ ጀርመን እና የአውሮጳ ሕብረት እንዲሁም አሜሪካ ሆነው የደረሱት ስምምነት ኢራን ኒውክሌር ማብላላቷን እንድትገታ ያስስባል።
ፕሬዝደንት ትራምፕ ስምምነቱ ከምርጫ ቅስቀሳቸው ጀምሮ ሲያጣጥሉት ከርመው ሥልጣን ከጨቡ በኋላ ከስምምነቱ ሃገራቸውን ማግለላቸው አይዘነጋም።
ኢራን ለስምምነቱ የማትገዛ ከሆነ ኒውክሌር ማብላላቱን በነፃነት ትገፋበታለች የሚል ስጋት ከሌሎቹ የስምምነት ፊርማ ካኖሩ ሃገራት ይደመጣል።
በሃገሪቱ ቴሌቪዠን ጣቢያ የተደመጠው የኢራን አቋም መግለጫ 'ኢራን ኒውክሌር ማብላላቷን ያለምንም ገደብ ትገፋበታለች' ሲል ተሰምቷል።
ኢራን ኒውክሌር የማብላላው ለሰላማዊ ተልዕኮ ነው የሚል የቀደመ አቋም አላት።