ቴህራን ጥቃት ከፈፀመች በሚል አሜሪካ 52 የኢራን ተቋማት ላይ መሳሪያዋን አነጣጥራለች

ፕሬዝዳንት ትራምፕ ኢራን አሜሪካውያንን አልያም የአሜሪካ ንብረቶች ላይ ጥቃት ብትፈጽም በምላሹ 52 የኢራን ተቋማት ላይ መሳሪያቸውን ማነጣጠራቸውን ገልጸው፤ ሁሉም በፍጥነት እና በማያዳግም ሁኔታ ምላሽ ይሰጣሉ ሲሉ ዝተዋል።

ይህንን አስተያየታቸውን የሰጡት ኢራናዊው ከፍተኛ የጦር አበጋዝ ቃሲም ሱሊማኒ በአየር ጥቃት መገደላቸውን ተከትሎ ነው። ኢራንም የጄነራሏን ደም እንደምትመልስ ዝታለች።

ፕሬዝዳንት ትራምፕ በቲውተር ገጻቸው ላይ እንዳሰፈሩት ኢራን በጄነራሉ ግድያ አጸፋ ለመስጠት "የአሜሪካ ንብረቶች ላይ ማነጣጠሯን በድፍረት እየተናገረች ትገኛለች" ብለዋል።

አክለውም አሜሪካ 52 የኢራን ተቋማት ላይ ማነጣጠሯን በመግለጽ ኢራን ጥቃት ከፈጸመች "አንዳንዶቹ ለኢራንና ለኢራናውያን ባሕል ትልቅ ቦታ ያላቸው ናቸው፤ በፍጥነትና በማያዳግም ሁኔታ ነው ምላሽ የምንሰጠው" ብለዋል።

"አሜሪካ ሌላ ማስፈራሪያ አትፈልግም" ሲሉም አክለዋል።

ፕሬዝዳንቱ የኢራን 52 ስፍራዎች የተመረጡት በአውሮፓውያኑ 1979 በኢራን በሚገኘው የአሜሪካ ኢምባሲ ታግተው የነበሩትን 52 አሜሪካውያንን ለማስታወስ መሆኑን ገልፀዋል።

እነዚህ የኢምባሲው ሠራተኞች ለአንድ አመት ያህል ታግተው ቆይተው ነበር።

ፕሬዝዳንት ትራምፕ ይህንን የትውተር መልዕክታቸውን ባሰፈሩ በጥቂት ደቂቃ ውስጥ የአሜሪካ መንግስት ተቋም የሆነ አንድ ድረገጽን "የኢራን ሳይበር ሰኪዩሪቲ ግሩፕ ሀከር" የተሰኘ የኮምፒዩተር ጠላፊ ቡድን እንዳይሰራ አድርጎታል።

በፌደራሉ ዲፖዚተሪ ላይብረሪ ፕሮግራም ድረገፅ ላይ "ይህ ከእስላማዊ ሪፐብሊክ ኢራን የተላለፈ ነው" የሚል ጽሁፍም ይነበብ ነበር።

"በቀጠናው ያሉ ወዳጆቻችንን መርዳት አናቆምም። የተጨቆኑ ፍልስጤማውያኖችን፣ የመኖችን፣ የሶሪያ ህዝብን፣ ኢራቅና ባህሬን ሁሌም በእኛ ይደገፋሉ" ይላል መልዕክቱ።

በድረገፁ ላይ የቀረበው የትራምፕ ምስል ፊታቸው ላይ ተመትተው ሲደሙ ያሳያል። ጠላፊዎቹ "ይህ ትንሹ የኢራን የሳይበር አቅም ነው" ሲሉ መልዕክታቸውን ያጠናቅቃሉ።

ምን ነበር የሆነው?

ፔንታጎን ባወጣው የጽሑፍ መግለጫ "በፕሬዝደንቱ ትዕዛዝ፤ ከሃገር ውጪ የሚኖሩ አሜሪካዊያንን ደህንነት ለመጠበቅ የአሜሪካ ጦር በወሰደው የመከላከል እርምጃ ቃሲም ሱሊማኒን ገድሏል" ብሏል።

"ጥቃቱ ኢላማ ያደረገው የወደፊት የኢራንን ጥቃት ለማስወገድ ነው። አሜሪካ ዜጎቿን እና ጥቅሞቿን ለማስጠበቅ በማንኛውም አካል ላይ፤ በየትኛውም የዓለማችን ሥፍራ ቢገኙ አስፈላጊውን እርምጃ መውሰዷን ትቀጥላለች" ይላል የፔንታጎን መግለጫ።

ፔንታጎን ከዚህ በተጨማሪም፤ ጀነራሉ በኢራቅ የሚገኙ የአሜሪካ ዲፕሎማቶችን ለመግደል ሲያሴር ነበር ብሏል።

አሜሪካ ይህን ጥቃት የሰነዘረችው አደባባይ በወጡ ሰልፈኞች ባግዳድ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ላይ ጥቃት ከተሰነዘረ በኋላ ነበር። በወቅቱ የኤምባሲው አሜሪካዊያን ጠባቂዎች ከሰልፈኞቹ ጋር ተጋጭተው ነበር።

ፔንታጎን እንደሚለው ከሆነ ጀነራል ሱሊማኒ በኤምባሲው ላይ ጥቃቱ እንዲቃጣ ፍቃድ ሰጥተዋል።

አሜሪካ በአየር ማረፊያው በወሰደችው ጥቃት ከጀነራሉ በተጨማሪ የኢራቅ ሚሊሻ መሪ አቡ ማሃዲ አል-ሙሃንዲስ እንደተገደሉ የኢራን አብዮት ጥበቃ አስታውቋል።

የኢራን አብዮታዊ ጥበቃ፤ ከፍተኛ የጦር ኃላፊዎቹ የተገደሉት የአሜሪካ ሄሊኮፕተሮች በወሰዱት እርምጃ ነው ብሏል።

የጀነራል ሱሊማኒ ግድያ በአሜሪካ ሁለት ጎራዎችን ፈጥሯል። የፕሬዝደንት ትራምፕ የፖለቲካ አጋር የሆኑት ሪፐብሊካኖች 'ሱሊማኒ የአሜሪካ ጠላት ነው' በማለት ግድያውን ደግፈዋል።

የውጪ ጉዳይ ሚንስትሩ ማይክ ፖምፔዮ፤ ኢራቃዊያን የጀነራሉን ግድያ ተከትሎ ደስታቸውን ሲገልጹ የሚያሳይ ምስል በትዊተር ገጻቸው ላይ አጋርተዋል።

በሌላ በኩል ዲሞክራቶች የሱሊማኒን ግድያ አጥብቀው ኮንነዋል። ፕሬዝደንት ትራምፕ ጀነራሉ እንዲገደሉ ትዕዛዝ ከመስጠታቸው በፊት ከአሜሪካ ኮንግረስ ፍቃድ መጠየቅ ነበረባቸው እያሉ ነው።

ኢራናውያን በጀነራል ሱሊማኒ ግድያ ብስጭታቸውን እየገለጹ ነው። የኢራን ባለሥልጣናት በበኩላቸው ይህ የጦርነት ትንኮሳ ነው ብለውታል።

ቃሲም ሱሊማኒ ማን ነበሩ?

እ.አ.አ. ከ 1998 ጀምሮ ሜጀር ጀነራል ሱሊማኒ የኢራን ኩድስ ኃይል ሲመሩ ቆይተዋል። ይህ ኃይል ከሃገር ውጪ የሚፈጸሙ ሚስጥራዊ ኦፕሬሽኖችን የሚያከናውን ነው።

ጀነራሉ በኢራቅ ውስጥ አይኤስ እና አል-ቃይዳን በመዋጋ ትልቅ አስተዋጽኦ ነበራቸው። ከዚህ በተጨማሪም፤ እኚህ የሽብር ቡድኖች እግራቸውን በኢራን እንዳይተክሉ ተከታትለው ድባቅ የመቷቸው ጀነራል ሱሌይማኒ ነበሩ ተብሏል።

ጀነራሉ የሚመሩት ኃይል በሶሪያ ግጭት ውስጥ ተሳትፎ እንዳለው አምኗል። ለፕሬዝደንት በሽር አል-አሳድ ታማኝ ለሆኑ ወታደሮች የጦር ምክር ይሰጣል። እንዲሁም ለበሽር አል-አሳድ ታማኝ የሆኑ በሺዎች የሚቆጠሩ ሺዓ ሙስሊሞችን አስታጥቋል። በኢራቅ ደግሞ አይኤስን እየታገሉ ለሚገኙ ለሺዓ ሙስሊም ሚሊሻዎች ድጋፍ ያደርጋል።

በመካከለኛው ምስራቅ ሃገራት የተከሰቱት ግጭቶች ጀነራሉ ኢራን ውስጥ እጅግ ዝነኛ ሰው እንዲሆኑ አድርጓቸዋል።

ጀነራል ሱሊማኒ ባለፈው የፈረንጆቹ ዓመት የኢራን ከፍተኛ የጦር ሽልማት ተቀብለዋል።

አሜሪካ በበኩሏ ጀነራሉ የሚመሩት የኩድስ ኃይል በመካከለኛው ምስራቅ የሚገኙ አሜሪካን በጠላትነት በመፈረጅ በሽብር መናጥ ለሚፈልጉ ኃይሎች ፈንድ፣ ሥልጠና እና የጦር መሳሪያን ጨምሮ የቁስ ድጋፍ ያደርጋል ስትል ትወነጅላለች።

አሜሪካ እንደምትለው ከሆነ ይህ የኩድስ ኃይል ድጋፍ ከሚያደርግላቸው ኃይሎች መካከል፤ የሌባኖሱ ሄዝቦላ እንዲሁም የፍልስጤሙ እስላማዊ ጅሃድ ተጠቃሽ ናቸው።

የቀድሞ የሲአይኤ አለቃ የአሁኑ የአሜሪካ የውጪ ጉዳይ ሚንስትር ማይክ ፖምፔዮ የኢራንን አብዮታዊ ጥበቃ እና ኩድስ ኃይሉን "የሽብር ቡድን" ሲሉ ከወራት በፊት ፈርጀውት ነበር።