ብዙ መመገብ ለምን ያስርበናል?

ብዙዎች ለአውደ ዓመት አብዝተው ይመገባሉ። ለገና ዶሮ፣ ክትፎ፣ ጥብስ፣ ድፎ ዳቦ. . . በልተው በቀኑ ማገባደጃ ላይ ከመጠን ያለፈ ጥጋብም ይሰማቸዋል። ሆኖም ግን በበዓሉ ማግስትም ብዙ ከመብላት ወደኋላ አይሉም።

ሰዎች ብዙ መብላት የሚያስከትለው ጥጋብ ጫና ቢፈጥርባቸውም ነገም፣ ከነገ ወዲያም አብዝተው ይመገባሉ። ለመሆኑ የሰው ልጆች ብዙ ከበሉ በኋላ የሚራቡት ለምን ይሆን?

ጥናቶች እንደሚያሳዩት፤ ብዙ መብላት ረሀብን አይገታም፤ እንዲያውም ረሀብ ይቀሰቅሳል። የሰው ሆድ ሲራብና ሲጠግብ የተለያየ መጠን ይይዛል። ሆድ ለምግብ መፈጨት ሂደት ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር ይኮማተራል። ረሀብ ሲሰማን ሆድ ምግብ ለመቀበል ዝግጁ ስለሚሆን ይሰፋል።

በእርግጥ መብላት ሆድን ይለጥጣል የሚለው አባባል እውነት አይደለም። ሆድ በተፈጥሯዊ ባህሪው ይጠባል፤ ይሰፋልም። ሆዳችን ከአንድ እስከ ሁለት ሊትር የመያዝ አቅምም አለው።

ሰዎች ቢወፍሩም ቢቀጥኑም፣ ቢረዝሙም ቢያጥሩም የሆዳቸው መጠነ ስፋት ተመሳሳይ ነው።

ሰው ሲራብ ገርሊን የተባለ ሆርሞን በሰውነቱ፣ ኤንፒዋይ እና ኤጂፒራ የተባለ ሆርሞን ደግሞ በአእምሮው ይሰራጫል። ስንራብ የሚያሳውቁን፣ ስንጠግብ የሚያረኩንም እነዚህ ዝውውሮች ከሌሎች ሆርሞኖች ጋር ተደማምረው ነው።

ገርሊን የተባለው ሆርሞን በቀጭን ሰዎች ሲበዛ በወፍራም ሰዎች አካል ውስጥ ደግሞ አናሳ ነው።

ሆድ መራቡን ለአእምሮ ሆርሞን በመላክ መልዕክት ያስተላልፋል። ሰውነታችን፤ በቀን ውስጥ በዘልማድ ለምግብ የተመደቡ ሰዓታትንና የረሀብ ስሜት ያስተሳስራል። ስለዚህ ምሳ ብንበላም የእራት ሰዓት ሲድርስ ይርበናል።

አንድ ሰው ሁልጊዜ ፎቴ ላይ ሲቀመጥ ቆሎ የሚበላ ከሆነ፤ ሰውነቱ ፎቴና ቆሎን ያዛምዳቸዋል። ሰውየው ሁሌ ፎቴ ላይ ሲሆን ቆሎ ሊያምረውም ይችላል።

ተመራማሪ ካሮላይን ቫን ዴን አከር እንደሚሉት፤ በአጭር ጊዜ ከመጠን በላይ መመገብ አሳፋሪ ልማድ ተደርጎ ቢወሰድም፤ የሰውነትን ፍላጎት በቀላሉ መግታት ያስቸግራል።

ስለ ምግብ መዓዛ፣ ጣዕም እንዲሁም ከተበላ በኋላ ያለው ሀሴት ሲታሰብ፤ ሰዎች ምግብ ያምራቸዋል። አንዳንድ አይነት ስሜቶች ሰዎች ምግብ እንዲያሰኛቸው ያደርጋሉ። ተመራማሪዋ እንደሚሉት፤ ሰዎች በመጥፎ ስሜት ሲዋጡና ሲደክማቸው አብዝተው ይበላሉ። ደስታ፣ ከወዳጅ ዘመድ ጋር መገናኘትም እንዲሁ ከምግብ ጋር የሚተሳሰሩበት ወቅትም አለ።

ካሮላይን ቫን ዴን አከር፤ ሰዎች ከመጠን በላይ የመመገብ ልማዳቸውን እንዲተዉ ለማድረግ፤ አንዴ ጥሩ ምግብ መብላት በቀጣይ ቀናትም ያንኑ ምግብ ደጋግሞ ከመመገብ ጋር መያያዝ እንደሌለበት ማሳየትን ያካትታል ይላሉ።

ከወዳጅ ዘመድ ጋር ሳሉ ብዙ የሚበሉ ሰዎች፤ በዚያው ቀን ወይም በቀጣዩ ቀን በድጋሚ መራባቸው ብዙም አያስገርምም። ዳግመኛ የሚራቡት የሆዳቸው መጠን ስለሰፋ ሳይሆን፤ ከወዳጅ ዘመዶች ጋር መገናኘትን ከመብላት ጋር አያይዘው ስለሚያስቡ ነው።

ለምሳሌ በገና በዓል ማግስት አንድ ሰው ዶሮ ወጥ ወይም ጥብስ ቢሸተው፤ ለአውደ ዓመት ከቤተሰቡና ጓደኞቹ ጋር የበላው ምግብና የነበረው አስደሳች ቆይታ ትውስ ይለዋል። ስለዚህም ሰውነቱ እንደ አዲስ ምግብ ለመቀበል ዝግጅት ያደርጋል።