ደሃ ሃገራት የምግብ እጥረት እንዲሁም ከልክ በላይ ውፍረት እንደሚያስቸግራቸው ተገለፀ

በደሃ ሀገራት የሚገኙ ሰዎች ከልክ በላይ ውፍረትም ሆነ ከፍተኛ የምግብ እጥረት እንደሚያስቸግራቸው አንድ የወጣ ሪፖርት አስታወቀ።

ዘ ላንሴት ላይ የወጣው ይህ ሪፖርት ለዚህ ምክንያት ያለውን ሲያስቀምጥ በፋብሪካ የተቀነባበሩ ምግቦች በብዛት መመገብ እንዲሁም የስፖርታዊ እንቅስቃሴ አለማድረግ መሆኑን አስፍሯል።

ሪፖርቱን ይፋ ያደረጉት ባለሙያዎች ይህንንን ከልክ በላይ ውፍረት እንዲሁም ከፍተኛ የምግብ እጥረት "ዘመናዊ አመጋገብ ሥርዓት" በማለት እንዲለውጡ ጠይቀዋል።

በዚህ የተጎዱ የተባሉ ሀገራት ከሰሃራ በታች ያሉ የአፍሪካ ሀገራትና የእስያ ሀገራት ናቸው።

ይህ ሪፖርት በዓለማችን ላይ 2.3 ቢሊየን ህጻናትና አዋቂዎች ከልክ በላይ ውፍረት እንደተጠቁ የተጠቀሰ ሲሆን፣ 150 ሚሊየን ሕጻናት ደግሞ የተገደበ እድገት አላቸው ሲል ያስቀምጣል።

ዝቅተኛ እና መካከለኛ ገቢ ያላቸው ሀገራት በእነዚህ በሁለት ጉዳዮች በተመሳሳይ እንደሚጠቁ ያሰፈረው ሪፖርቱ ይህንንም " የምግብ ዕጥረት መንታ መልኮች" ሲል ይገልጻቸዋል።

ይህም ማለት 20 በመቶ ሰዎች ከልክ በላይ ወፍራም፣ 30 በመቶ ዕድሜያቸው ከአራት ዓመት በታች የሆኑ ሕጻናት ተገቢ እድገት ያለመኖር፣ እንዲሁም 20 በመቶ ሴቶች ደግሞ ከመጠን በላይ ቀጭን ናቸው ይላል።

ማሕበረሰብም ሆነ ቤተሰብ እንዲሁም በየትኛውም የሕይወት መስክ የተሰማሩ ግለሰቦች በዚህ ዓይነት የምግብ ዕጥረት ሊጠቁ እንደሚችሉ ሪፖርቱ ያስቀምጣል።

በ1990ዎቹ ይላል ሪፖርቱ ከ123 ሀገራት መካከል 45ቱ በዚህ ችግር ተጠቅተው የነበረ ሲሆን በጎርጎሳውያኑ 2010 አካባቢ ደግሞ ከ126 ሀገራት 48 ተጠቅተዋል።

በ2010 በተደረገ ፍተሻ፣ ከ1990ዎቹ ጀምሮ 14 ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ሀገራት በምግብ ዕጥረት መንታ መልኮች [በተመሳሳይ ሰዓት የተገደበ እድገት እንዲሁም ከልክ በላይ ውፍረት ] ተጠቅተዋል ይላል።

ሪፖርቱን ያዘጋጁ አካላት እንዳሉት ከሆነ የሃገራት መሪዎች፣ የተባበሩት መንግሥታት እንዲሁም ምሁራን ይህንን ችግር በማስተዋል የበኩላቸውን ማድረግ አለባቸው ያሉ ሲሆን ጣታቸውንም የአመጋገብ ስርዓት መለወጥ ላይ አድርገዋል።

የበርካታ ግለሰቦች የአመጋገብ፣ አጠጣጥ እንዲሁም የአካል ብቃት እንቅስቃሴ መለወጥ ለዚህ ሁሉ ምከንያት ነው ያሉት ባለሙያዎቹ፣ በሀገራት በየገበያ አዳራሹ የሚገኙ በቀላሉና በርካሽ የሚገኙ ምግቦች በርካታ ሰዎች ከልክ በላይ እንዲወፍሩ እያደረገ ነው ብለዋል።

እንደ ሪፖርቱ ከሆነ በፋብሪካ የተቀነባበሩ ምግቦችን ከልጅነት ጀምሮ መመገብ እድገት ባለበት እንዲቀር የራሱ አስተዋጽኦ አለው ብለዋል።

" አዲስ የተመጣጠነ ምግብ እውነታን እየተጋፈጥን ነው" ያሉት በዓለም ጤና ድርጅት የሥነ ምግብ ጤናና ዕድገት ክፍል ዳይሬክተር ዶ/ር ፍራንሲስኮ ብራንካ ናቸው።

" ከአሁን በኋላ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን በምግብ እጥረት የተጎዱ ወይንም ከፍተኛ ገቢ ያላቸውን ደግሞ ከልክ በላይ ውፍረት ጋር ማዛመዳችን መቅረት አለበት" ብለዋል።

ሁሉም ዓይነት የምግብ ዕጥረት ጉዳት የጋራ መለያ ነው። የምግብ ስርዓታችን ጤናማ፣ በጥንቃቄ የተዘጋጁ፣ በቀላሉ የሚገኙ፣ ርካሽ፣ እና በቂ የሆነ የተመጣጠነ ምግብ ይዘት ያላቸው አይደሉም ሲሉ ወቅሰዋል።

ዶ/ር ብራንካ እንዳሉት የምግብ ስርዓታችን ከምርት እስከ ማቀነባበሪያ፣ ከሽያጭ እስከ ስርጭት፣ ከዋጋ ትመና እስከ ገበያ፣ አስተሻሸግና ፍጆታ እንዲሁም አወጋገድ ላይ መለወጥ ይኖርበታል።

አክለውም " ፖሊሲዎችና እስካሁን በዚህ ጉዳይ ላይ የፈሰሱ ኃብቶች በሙሉ ዳግመኛ መፈተሽ አለባቸው" ይላሉ ዶ/ር ብራንካ።