ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የአፍሪካ አገራት ከህፃናት የተመጣጠነ ምግብ አንፃር የልማት ግብን አያሳኩም
አንድም የአፍሪካ አገር በ2030 የህፃናት የተመጣጠነ ምግብ ጉድለትን የማስወገድ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ያስቀመጠውን የዘላቂ ልማት ግብን እውን እንደማያደርጉ የህፃናት እድገት ላይ የተሰሩ ሁለት ሰፊ ጥናቶች ጠቆሙ።
ይህ ግብ ከተመድ ዘላቂ የልማት ግቦች መካከል አንዱ ነው።
አገራቱ ግቡን እውን ለማድረግ እንደማይችሉ ጥናቶቹ ቢያመለክቱም ቢያንስ በእያንዳንዱ የአፍሪካ አገር የህፃናት ጤና የተሻሻለ የሚሆንበት አንድ አካባቢ መኖሩን አስቀምጠዋል።
ጥናቶቹ በመሰረታዊነት የሚያተኩሩት የህፃናት እድገትና በመውለድ እድሜ ክልል ውስጥ ላሉ ሴቶች የትምህርት ተደራሽነትን ነው።
ይህ የሆነው እነዚህ ነገሮች ከህፃናት ሞት ጋር ተያያዥነታቸው ከፍተኛ በመሆኑ ነው።
"እነዚህ ሁለት ነገሮች አንድላይ ህዝብ የቱ ጋር ጤናማ እንደሆነ ወይም እንዳልሆነም ጠቋሚዎች ናቸው" ይላሉ፤ የዋሽንግተን ዩኒቨርሲቲው የዓለም አቀፍ ጤና ተመራማሪው ፕሮፌሰር ሲሞን ሃይ።
ጥናቱ የአፍሪካ አገራት ግቡን እውን ማድረግ አይችሉም ቢልም ግን የህፃናት የተመጣጠነ ምግብ ችግርን በመቅረፍ ረገድ ብዙዎቹ ከሰሃራ በታች ያሉ፤ ምሥራቃዊና ደቡባዊ የአፍሪካ አገራት መሻሻሎች ማሳየታቸውን ይጠቁማል።