ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አፍሪካዊያን ተወዳጅ ምግባቸውን መተው ሊኖርባቸው ይሆን?
የዛምቢያው ምክትል ፕሬዝዳንት የአገሬው ሰዎች የአመጋገብ ሥርዓታቸውን ሙሉ በሙሉ መቀየር አለባቸው ብለዋል። በጣም ተወዳጁንና የዕለት ተዕለት ምግብ ውስጥ የማይጠፋውን በቆሎ እርግፍ አድርጋችሁ ተዉት ማለታቸው ደግሞ ብዙዎችን አስገርሟል።
አፍሪካውያን በቆሎን አትመገቡ ማለት ጣልያናዊያንን ፓስታ መመገብ አቁሙ እንደማለት ነው።
ከበቆሎ የሚሠሩ ምግቦች በደቡባዊ እና ምሥራቃዊ አፍሪካ በእጅጉ የሚወደዱና የሚዘወተሩ ሲሆን ጥናቶች እንደሚጠቁሙት ዓለማችን ከምታመርተው በቆሎ 21 በመቶ የሚሆነው ለምግብነት የሚውለው ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ አገራት ውስጥ ሲሆን ይህም በጣም ትልቁ ቁጥር ነው።
የዛምቢያው ምክትል ፕሬዝዳንት ኢኖንጌ ዊና ይህንን ያሉት አገራቸውና አንዳንድ የጎረቤት አገራት ባጋጠማቸው ዝቅተኛ ዝናብ ምክንያት የምግብ እጥረት ከተከሰተ በኋላ ነው።
ይህ ቀውስ ከአገሬው ሕዝብ 18 በመቶ በሚሆኑት 1.7 ሚሊዮን ዛምቢያዊያን ላይ ከፍተኛ የምግብ እጥረት አስከትሏል። ከእነዚህ መካከል ደግሞ 40 በመቶ የሚሆኑት ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ጨቅላዎች ናቸው።
ችግሩን ለመቅረፍም ዜጎች የምግብ ሥርዓታቸውን በመቀየር እንደ ካሳቫ፣ ማሽላ እና ስኳር ድንች ያሉ የምግብ አይነቶችን መሞከር አለባቸው ብለዋል ምክትል ፕሬዝዳንቷ።
''ቀስ በቀስ በቆሎ ላይ የተመሰረተውን የአመጋገብ ሥርዓታችንን መቀየር ብንችል ወጪ ቆጣቢ ከመሆኑ ባለፈ ለሰውነት እድገት የሚጠቅሙ የተመጣጡ ምግቦችን ዜጎች ማግኘት ይችላሉ። በምግብ እጥረት የሚሰቃዩ ሰዎች ቁጥርም ይቀንሳል'' ሲሉ ተደምጠዋል።
ነገር ግን ምክትል ፕሬዝዳንቷ ከባድ ፈተና ይጠብቃቸዋል።
ዛምቢያዊያንን ጨምሮ ብዙ አፍሪካዊያን በቆሎን በቀን ሁለት ወይም ሦስት ጊዜ ይመገባሉ። ዛምቢያዊያን ንሺማ ተብሎ የሚጠራውንና ከበቆሎ የሚሰራውን ምግብ በቀን አንድ ጊዜ እንኳን ካልበላን ቀኑን ሙሉ ምግብ እንደበላን አንቆጥረውም ብለዋል።
ይህ ምግብ በማላዊ ንሲማ ሲባል በዚምባብዌ ሳድዛ፣ ፓፓ ወይም ፓፕ በደቡብ አፍሪካ እንዲሁም በኬንያ ደግሞ ኡጋሊ ተብሎ ይጠራል።
በዛምቢያ ዩኒቨርሲቲ የአራተኛ ዓመት ተማሪ የሆነው ክሊፎርድ ቺርዋ እንደሚለው መንግሥት የበቆሎ አመጋገብ ሥርዓትን በቀላሉ መቀየር አይችልም።
''ሰዎችን ድንገት ተነስቶ ምግባችሁን ቀይሩ ማለት የማይቻል ነገር ነው። በቆሎ ምግብ ብቻ ሳይሆን ከማህበረሰቡ አኗኗርና ባህል ጋር ቁርኝት ያለው ነገር ነው'' በማለት ምን ያህል ከባድ እንደሆነ ለቢቢሲ ተናግሯል።
ሌላኛዋ በዋና ከተማዋ የምትኖረውና አነስተኛ ምግብ ቤት ከፍታ የምትተዳደረው ኦሊፓ ሉንጉ ደግሞ የምታቀርባቸውን ምግቦች ለመቀየር ያደረገችው ሙከራ ውጤታማ እንዳልነበር ታስረዳለች።
''ድንበኞቼ ሁሌም ከበቆሎ የሚሰራው ንሺማ ተብሎ የሚጠራውን ምግብ ነው የሚመርጡት'' ብላለች።
ምክትል ፕሬዝዳንቷ ያቀረቡት ሃሳብ ግን ከተቃውሞ በተጨማሪ ድጋፍም እያገኘ ነው። ጥሪውን ከደገፉት መከካል ደግሞ የዛምቢያ ገበሬዎች ማህበር አንዱ ነው።
የማህበሩ ቃል አቀባይ ካኮማ ካሌዪ እንደሚሉት እየተከሰተ ካለው የአየር ንብረት መቀያየር አንጻር ሌሎች አማራጮችንም ከግምት ውስጥ ማስገባት ምንም ችግር የለውም፤ ለረጅም ዓመታትም በቆሎ ብቻ በልተናል፤ ስለዚህ አዲስ ነገር መሞከሩ ጠቃሚ ይሆናል'' ብለዋል።
አንዳንድ የምግብ ባለሙያዎች እንደሚሉት በብዙ ደሃ አፍሪካዊያን ቤተሰቦች ዘንድ በቆሎ እጅግ ተመራጭ ምግብ ነው። በቆሎ በመንግሥታት ድጎማ በቅናሽ ዋጋ እንዲቀርብ ይደረጋል።
ስለዚህ ሌሎች የምግብ አማራጮችን መንግሥት ሲያቀርብ ስለጥቅሙ ብቻ ሳይሆን ማውራት ያለበት እንደ አማራጭ የቀረቡት ምግቦች በተመጣጣኝ ዋጋ መገኘት መቻላቸውንም ማረጋገጥ ይጠበቅበታል።
ብዙዎቹ ገበሬዎች እንዴት በቀላሉ በቆሎን ማምረት እንደሚችሉ በጊዜ ብዛት ተምረዋል። ስለዚህ ሌሎቹን ዘሮችም በተመሳሳይ መንገድ ማምረት እንዲጀመሩ ማድረግ የመጀመሪያው እርምጃ እንደሆነ ባለሙያዎች ይመክራሉ።