እርጉዟ የሰደድ እሳት ተከላካይ አውስትራሊያዊት

ካት ሮቢንሰን ዊልያምስ

የፎቶው ባለመብት, Kat Robinson-Williams

የምስሉ መግለጫ, ካት ሮቢንሰን ዊልያምስ

የ23 ዓመቷ ካት ሮቢንሰን-ዊልያምስ የ14 ሳምንት እርጉዝ ናት። ካት አውስትራሊያ ውስጥ የተነሳውን ሰደድ እሳት ለማጥፋት በበጎ ፍቃደኛነት ከተመዘገቡ አንዷም ነች።

"እርጉዝ ሆነሽ እንዴት ከእሳት ጋር ትታገያለሽ!?" የበርካታ ወዳጆቿ ጥያቄ ቢሆንም፤ ካት በበጎ ፍቃደኛነቷ እንደምትገፋበት ትናግራለች።

'ኒው ሳውዝ ዌልስ' ከተባለ የእሳት አደጋ ተከላካዮች ተቋም ጋር እየሠራች ያለችው ካት፤ "የመጀመሪያዋ እርጉዝ እሳት አደጋ ተከላካይ አይደለሁም፤ የመጨረሻዋም አልሆንም" ብላለች።

ካት ለቢቢሲ እንደተናገረችው፤ ሰደድ እሳቱ እንዲጠፋ ድጋፍ ማድረግ የምትችልበት አቋም ላይ ትገኛለች። አውስትራሊያ ውስጥ በተነሳው ሰደድ እሳት ሳቢያ ሦስት ሰዎች ሲሞቱ፤ ከ200 በላይ ቤቶች ተቃጥለዋል።

"አትሳሳቱ ወንድ አይደለሁም፤ እርጉዝ ነኝ"

ካት፤ የእሳት አደጋ ተከላካዮች ልብስ አጥልቃ፣ ሰደድ እሳቱ ወደሚቀጣጠልበት ቦታ ስትሄድ የሚያሳዩ ፎቶዎችን ባለፈው ሰኞ በኢንስታግራም ገጿ ለቃለች።

ከፎቶዎቹ ሥር "አዎን እሳት አደጋ ተከላካይ ነኝ! አትሳሳቱ ወንድ አይደለሁም፤ እርጉዝ ነኝ፤ የማደርገው ነገር ደስ ባይላችሁም ግድ አይሰጠኝም" ስትል ጽፋለች።

ጓደኞቿ የእሳት አደጋ ተከላካይ መሆኗን ቢነቅፉም ድርጊቷን ያደነቁም ብዙዎች ናቸው።

ሀኪሟ አስፈላጊውን የእሳት አደጋ መከላከያ እስከተጠቀመች ድረስ እሳት ከመከላከል የሚያግዳት እንደሌለ እንደገለጹላትም ተናግራለች።

የካት ቤተሰቦች እሳት አደጋ ተከላካዮች ናቸው። የካት እናት እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር በ1995 የተነሳ እሳትን ለመከላከል ሲሞክሩ እርጉዝ ነበሩ።

"ልጅ እያለሁ እያቴ የእሳት አደጋ ተከላካይ ልብስ ሰፍታልኝ ነበር" ስትልም ታስታውሳለች።

አያቷን ጨምሮ ብዙ ቤተሰቦቿ በጎ ፍቃደኛ የእሳት አደጋ ተከላካይ ናቸው። እናቷ ለ30 ዓመት፣ አያቷ ደግሞ ለ50 ዓመት አገልግለዋል። ባለቤቷና የባለቤቷ ቤተሰቦችም እንዲሁ።

"ልጄም የኔን ፈለግ እንደሚከተል ተስፋ አለኝ፤ ምርጫው ግን የራሱ ነው" የምትለው ካት፤ ሰደድ እሳቱን ለማጥፋት ስትንቀሳቀስ አንዳችም ፍርሀት እንደማይሰማትም ትገልጻለች።