የ87 ዓመቷ አዛውንት በተቆጡ ላሞች ተወግተው ሞቱ

የ87 ዓመቷ ሒላሪ አዳየር በሚኖርበት ምዕራብ ሰሴክስ አካባቢ በተቆጡ ላሞች ተወግተው መሞታቸው ተሰማ።

ሒላሪ ላይ ጥቃት ያደረሱት ወገበ ነጭ የሆኑ የከብት ዝርያዎች ናቸው ተብሏል።

ላሞቹ አዛውንቷን ወግተው ከጣሏቸው በኋላ ለመነሳት ሲሞክሩ በተደጋጋሚ እንደወጓቸው ተነግሯል።

ጥቃቱ ከደረሰባቸው ስፍራ በአውሮፕላን ወደ ህክምና መስጫ የተወሰዱት ሒላሪ፣ ለሳምንት ያህን ሳይሰሙ ሳይለሙ ቆይተው ሕይወታቸው አልፏል።

ላሞቹ እኚህን የእድሜ ባለፀጋ ከማጥቃታቸው አንድ ቀን ቀደም ብሎ ውሻቸውን እያንሸራሸሩ የነበሩ ጥንዶችም ላይ ተመሳሳይ ጥቃት አድርሰዋል።

ላሞቹን በባለቤትነት የሚያስተዳድሩት 'ሊንቺሜር ሶሳይቲና ሊንቺሜር ኮሚውኒቲ ግሬዚንግ ሲአይሲ' በዚህ ጉዳይ ችሎት ፊት የቀረቡ ሲሆን፤ ላሞቹ እያደረሱ ያለውን ጥቃት ከቁብ ጽፈው እየተከታተሉት እንዳልነበር ለማወቅ ተችሏል። እንደውም ከእለታት በአንዱ ቀን የተከሰተ ድንገተኛ አደጋ አድርገው ነው የወሰዱት።

ብራይዮኒ ዲላሞር አዟውንቷ ጥቃት ሲደርስባቸው የተመለከተ ሲሆን፤ አዛውንቷ ራሳቸውን ለማዳን በተንቀሳቀሱ ቁጥር ላሞቹ የበለጠ ቁጡ በመሆን ይወጓቸው እንደነበር መስክሯል።

ራቼል ቶምፕሰን በበኩሏ የደረሰባትን ለችሎቱ ስታስረዳ እርሷና ባለቤቷ አዛውንቷ ከመወጋታቸው አንድ ቀን ቀደም ብሎ በእነዚሁ ላሞች ጥቃት እንደደረሰባቸው መስክራለች።

ባለቤቷም በጉዳቱ መድማት እንደደረሰበት ተናግሮ ላሞቹ "ተቆጥተዋል" ሲል ተናግሯል።

ጥንዶቹ አደጋ እንደደረሰባቸው ላሞቹ ወዲያውኑ ወደ ሌላ መኖሪያ ስፍራ የተወሰዱ ሲሆን፣ ያለውን ሁኔታ በቀጣዩ ማለዳ ለመፈተሽ ታቅዶ ነበር ተብሏል።

ነገር ግን በነጋታው ጠዋት አዛውንቷ ሒላሪ አዳየርና ውሻቸው ጥቃት ደረሰባቸው።

ላሞቹን በባለቤትነት የሚያስተዳድሩት በጋራ ባወጡት መግለጫ "በድርጅታችን ውስጥ በጉዳዩ ላይ ኮስተር ያለ ውይይት እያደረግን ነው፤ ከቤተሰቦቹም ጋር ውይይቶች እያካሄድን ነው፤ ከማኅበረሰቡም ጋር ቢሆን የጋራ የግጦሽ ስፍራውን በሚመለከት ወደፊት በሚኖረን ግንኙነት ላይ ምንም አይነት ውሳኔ ከመወሰናችን በፊት እንነጋገራለን" ብለዋል።

የአካባቢው ፖሊስ ከፍተኛ ኃላፊ "በአዛውንቷም ላይ ሆነ በጥንዶቹ ላይ ላሞቹ ጥቃት ለመፈፀም ምን እንዳነሳሳቸው ምንም የታወቀ ነገር የለም" ብለዋል።

ይህ የሒላሪ አዳየር ሞት፤ ከብቶች በአንዳች ሁኔታ ሲቆጡ ምን ያህል አደገኛ መሆናቸውን ግንዛቤ የፈጠረ ክስተት ነው ሲሉም አክለዋል።