ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ለአፍሪካ ዋንጫ የሚፋለሙት ኃያላን እንስሳት
ለሚቀጥሉት ሦስት ሳምንታት ግብጽ ብምታስተናግደው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ የ24 ሃገራት ቡድኖች ይሳተፋሉ። ቡድኖቹ ከነገቡት የሃገር ባንዲራና ስም ባሻገር መጠሪያ ቅጽል አላቸው።
በአፍሪካ እግር ኳስ ውስጥ ቅጽል ስሞች ጉልህ ቦታ አላቸው። እነዚህ ስሞች ለቡድኖቹ ደጋፊዎች መለያ ከመሆን በተጨማሪ ተጫዋቾችን በማነቃቃት በኩልም ይጠቅማሉ።
የብሔራዊ ቡድኖች ቅጽል ስም፣ በቀለማት ካሸበረቁ ደጋፊዎችና የከበሮ ድምፅ ጋር የአፍሪካ ዋንጫ መለያ ድምቀቶች ናቸው።
ተምዘግዛጊዎቹ ንስሮች
በሚቀጥሉት ሳምንታት ግብጽ ውስጥ ንስሮቹ ጎልተው ይታያሉ ተብለው ይጠበቃል።
የናይጄሪያ ብሔራዊ ቡድን በሚለብሰው አረንጓዴ ማሊያ ተለይቶ የሚታወቅ ቢሆንም ንስሮቹ የሚለው ስያሜያቸው ግን የበለጠ መለያቸው ነው። ብድኑ ይህን ስያሜ የወሰደው ከሃገሪቱ ብሔራዊ መለያ ላይ ነው።
ቱኒዚያ ከካርቴጅ ሥልጣኔ ጋር በነበራት ግንኙነት የተነሳ ቡድኗ የካርቴጅ ንስር የሚል መጠሪያን አግኝቷል። ብሔራዊ መለያቸውም ንስር ነበረ።
እዚህ ጋር የማሊ ንስሮችም ሊዘነጉ አይገባም። በተጨማሪም ኡጋንዳም የበራሪ አእዋፍ (ሽመላ) መለያ ነው ያላት።
የጫካው ግብግብ
እዚህ የእግር ኳስ ሜዳውም ውስጥ ልክ እንደጫካው ዓለም የበላይነት ለማግኘት የሚደረግ ፍልሚያ አለ።
ከአንበሳ እስከ እባብ፣ ከአቦሸማኔ እስከ ዝሆን ያሉት የዱር እንስሳት በዚህ ዓመቱ የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ቦታ አላቸው።
- ካሜሩን - አይበገሬዎቹ አናብስት፣ ስያሜው ቡድኑ ከዚህ በፊት ካሳየው ጥንካሬና ዝና ጋር አብሮ የሚሄድ እንደሆነ ይነገርለታል፤ ያለፈውን ውድድር ጨምሮ አራት ጊዜ ዋንጫውን ለማንሳት ችለዋል።
- ሞሮኮ - የአትላስ አናብስት
- ሴኔጋል - የቴራንጋ አናብስት
- ኮት ዲቯር - ዝሆኖቹ፡ ሃገሪቱ በዝሆን ጥርስ ንግድ በነበራት ዝና ምክንያት ዝሆን የኮትዲቯር መለያ ምልክት ነው።
- ቤኒን - ሸለውለዊቶቹ፡ ቡድኖች ካላቸው ስያሜ መካከል ትንሿ እንስሳ ናት
- አንጎላ - ግዙፎቹ ድኩላዎች
- ዲሞክራቲክ ኮንጎ - አቦሸማኔዎቹ
- አልጄሪያ - ቀበሮዎቹ
- ጊኒ ቢሳዎ - የዱር ውሾች
ነገሥታትና ጦረኞች
መሪዎችን የማክበር ጠንካራ የአፍሪካዊያን ባህል መሠረት አንዳንድ ቡድኖች ስያሜያቸውን ከእነርሱ ወስደዋል።
ሰባት ጊዜ የአፍሪካ ዋንጫን በመውሰድ የውድድሩ ንጉሥ የሆኑት ግብጻዊያን ለውጤታቸው የሚመጥን ፈርዖኖቹ የሚለውን ስያሜ ከቀደምት ንገሥታቶቻቸው ወስደዋል።
ፈርዖኖቹ የዚምባብዌ ጦረኞች ከተባሉት የዚምባብዌ ብሔራዊ ቡድን ጋር የመጀመሪያ ጨዋታቸውን አድርገው ድል ቀንቷቸዋል።
የኬንያ ብሔራዊ ቡድን ስያሜያቸውን ከዱር እንስሳትና ከመሪዎች ውጪ ካደረጉ ቡድኖች መካከል ነው።
የሃራምቤ ከዋክብት ይባላሉ፤ ሃራምቤ የሚለው የስዋሂሊ ቃል ሕብረት መፍጠር ሲሆን ጥሪው ከቡድኑ አልፎ በሃገር ደረጃ ለአንድ ዓላማ መሰባሰብን ያመለክታል።
የዝነኞቹ የጋና ብሔራዊ ቡድን መጠሪያ ጥቋቁሮቹ ከዋክብት ሲሆን ይህም የተወሰደው ሃገሪቱ ሰንደቅ ዓላማ ላይ ካልው ጥቁር ኮከብ ነው። ይህም አንድነትን ለማመልከት እንደዋለ ይነገራል።
ከሳምንታት በኋላ የዘንድሮው የአፍሪካ ዋንጫ ሲጠናቀቅ ንስሮቹ ከሁሉ ከፍ ብለው መብረራቸው፤ አንበሶቹ ኃያልነታቸውን እንዳስከበሩ መቆየታቸውን ነገሥታቱም የበላይ ሆነው በመሪነት መዝለቃቸው የሚለይ ይሆናል።