ኢትዮጵያ ለዓለም ዋንጫ ለማለፍ የምድብ ድልድሉን ተቀላቀለች

ከዋልያዎቹ ጨዋታ በፊት

በ2022 ኳታር ለምታዘጋጀው የዓለም ዋንጫ ለማለፍ በአፍሪካ የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታዎች ቅዳሜና እሁድ ተካሂደዋል።

ከቀናት በፊት በባህር ዳር ስታዲየም ከሌሴቶ አቻዋ ጋር ያለምንም ግብ የተለያየችው ኢትዮጵያ፤ የመልስ ጨዋታዋን በሌሴቶ አድርጋ አንድ አቻ ተለያይታለች።

ከሜዳ ውጭ ባገባ በሚለው ህግ መሰረትም ወደቀጣዩ ዙር በማለፍ የምድብ ድልድል ውስጥ መግባቷን አረጋግጣለች። ሃያ ተጫዋቾችን ይዘው ወደ ሌሴቶ ያቀኑት አሰልጣኝ አብራሃም መብራቱ በተቻለ መጠን አጥቅቶ በመጫወት ከሜዳቸው ውጪ ግብ ለማስቆጠር እንደሚጥሩ ገልጸው ነበር።

በመጀመሪያው አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች ተጠንቅቀው የተጫወቱ ሲሆን ዋልያዎቹ የተሻለ የኳስ ቁጥጥር ነበራቸው። ነገር ግን ብዙም የግብ ዕድሎችን መፍጠር ሳይችሉ ቀርተዋል።

በአንጻሩ ሁለተኛው አጋማሽ ፈጣንና ብዙ የግብ ሙከራዎች የታዩበት ነበር። 50ኛው ደቂቃ ላይ በቀኝ መስመር የሚጫወተው ቢንያም በላይ ያሻማውን ኳስ የሌሴቶው ንካይ ኔትሮሊ ሲመልሰው ኳሷ አቅጣጫዋን ቀይራ በራሱ መረብ ላይ ግብ አስቆጥሮ ኢትዮጵያ መምራት ጀመረች።

ነገር ግን ከአምስት ደቆቃዎች በኋላ ሌሴቶዎች አቻ የምታደርጋቸውን ግብ በሴፖ ሴትሩማንግ አማካይነት ማግኘት ችለዋል።

ጨዋታው በዚሁ አንድ አቻ በሆነ ውጤት ቢጠናቀቅም ከሜዳ ውጭ ባገባ በሚለው ኢትዮጵያ ወደ ቀጣዩ ዙር ማለፏን አረጋግጣለች።

በመጀመሪያ ዙር ጨዋታ አሥመራ ላይ ናሚቢያን አስተናግዳ በደጋፊዎቿ ፊት 2ለ1 የተሸነፈችው ኤርትራ ደግሞ የመልስ ጨዋታዋን የፊታችን ማክሰኞ ዊንድሆክ ላይ ታደርጋለች።

ባለፈው ሐሙስ 1ለ0 በሆነ ጠባብ ውጤት ዚምባብዌን በማሸነፍ አስደናቂ ድል ያስመዘገቡት የሶማሊያ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾች፤ ለሁለተኛው ዙር ጨዋታ የፊታችን ማክሰኞ ወደ ሃራሬ ያቀናሉ።

በሌላ በኩል ከአርብ ጀምሮ የአውሮፓ ቻምፒየንሺፕ ጥሎ ማለፍ ጨዋታዎች ተከሂደዋል። በዚህም መሰረት ሆላንድ ጀርመንን 4 ለ2 በማሸነፍ ጥሩ አጀማመር ያደረገች ሲሆን ቤልጂየም ሳን ማሪኖን 4 ለምንም አሸንፋለች።

ክሮሺያም በተመሳሳይ ስሎቫኪያን 4 ለምንም ፤ አውስትራሊያ ደግሞ ላቲቪያን 6 ለባዶ ረምርማለች።

ቅዳሜ በተደረጉ ጨዋታዎች ደግሞ እንግሊዝ ቡልጋሪያን 4 ለምንም፣ ፖርቹጋል ሰርቢያን 4 ለ2 እንዲሁም ፈረንሳይ አልባኒያን 4 ለ1 ማሸነፍ ችለዋል።

ዕሁድ በተደረጉ ጨዋታዎች ደግሞ ጣልያን ፊንላንድን 2 ለ1 ፣ ስፔን ፋሮ አይላንድስን 4 ለምንም ሲያሸንፉ ጆርጂያና ዴንማርክ 0 ለ0 እንዲሁም ስዊድን እና ኖርዌይ 1 ለ1 በሆነ አቻ ውጤት ተለያይተዋል።