ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አሜሪካ፡ የስድስት ቀን ጨቅላ በቦርሳዋ ይዛ የተገኘችው ሴት ተከሰሰች
የስድስት ቀን ጨቅላን በቦርሳዋ ደብቃ ከፊሊፒንስ ልትወጣ ስትል በፖሊስ የተያዘችው አሜሪዊት በሕገ ወጥ የሰው ዝውውር ክስ ተመሰረተባት።
ጄኔፈር ታልቦት የተባለችው የ43 ዓመት ሴት በቁጥጥር ሥር የዋለችው ባለፈው ረቡዕ ፊሊፒንስ በሚገኝ የአውሮፕላን ማረፊያ ውስጥ ነበር። ወደ አሜሪካ የሚበር አውሮፕላን እየጠበቀች የነበረችው ጄኔፈር፤ ቦርሳዋ ውስጥ ከተወለደ ስድስት ቀን የሆነው ጨቅላ ቦርሳዋ ውስጥ መገኘቱን ፖሊስ አስታውቋል።
የኢሚግሬሽን ኃላፊዎች እንደተናገሩት ጄኔፈር ልጅ እንደያዘች አልነገረቻቸውም ነበር። የፊሊፒንስ የወንጀል ምርመራ ቡድን፤ ግለሰቧ ጨቅላውን ደብቃ ከአገር ለማስወጣት ሞክራለች ብሏል።
የጨቅላው እናትና አባት፤ የልጆችን መብት በመጋፋት ክስ ተመስርቶባቸዋል። የስድሰት ቀን ልጃቸውን ማኅበራዊ ሠራተኞች ተረክበዋል።
ጄኔፈር ታልቦት ክሱ ከቀረበባት በኋላ፤ ልጁን ወደ አሜሪካ ለመውሰድ ፍቃድ አግኝቼበታለሁ ያለችውን ሰነድ ብታቀርብም፤ ሰነዱ ላይ የልጁ እናት ፊርማ አልሰፈረም ተብሏል።
ጥፋተኛ ሆና ከተገኘች የእድሜ ልክ እሥራት ይጠብቃታል።