የቀድሞ የብሔራዊ መረጃና ደህንነት ኃላፊ የነበሩት አቶ ጌታቸው አሰፋ ላይ ክስ ተመሰረተ

ማንነቱ የማይታወቅ ሰው ምስል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

አቶ ጌታቸው አሰፋን ጨምር በ26 የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት የሥራ ኃላፊዎችና ሠራተኞች ላይ ክስ መመስረቱን የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ አስታወቀ።

የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ይፋ ባደረገው መረጃ መሰረት፤ ከባድ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ፈጽመዋል በሚል በፌደራል ፖሊስ ወንጀል መርማሪዎች፣ በማረሚያ ቤት የሥራ ኃላፊዎች እንዲሁም በብሔራዊ መረጃና ደህንነት የሥራ ኃላፊዎች ላይ የወንጀል ምርመራ ሲያካሂድ ነበር።

በዚህ መሰረት፤ አቃቤ ሕግ በወንጀል መርማሪዎች፣ በማረሚያ ቤቱ የሥራ ኃላፊዎች ላይ እንዲሁም በብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት የሥራ ኃላፊዎችና ሠራተኞች ላይ በሦስት የተለያዩ መዝገቦች ክስ መስርቷል።

በመርማሪዎች ላይ በፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የተከፈተው እና በማረሚያ ቤት ኃላፊዎች በነበሩት ላይ በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የተከፈቱት መዛግብት የክስ ሂደት ቀጥሎ፤ ምስክር ለመስማት ተቀጥረዋል።

በሦስተኛው መዝገብ ላይ 26 የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት የሥራ ኃላፊዎችና ሠራተኞች በጠቅላላው 46 ክሶች ተመስርቶባቸዋል።

በክሶቹ ውስጥ 22ቱ ተከሳሾች በአሁኑ ወቅት በእስር ላይ የሚገኙ ሲሆን፤ በሌላ በኩል የቀድሞ የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው አሰፋን ጨምሮ አቶ አጽብሃ ግደይ፣ አቶ አሠፋ በላይ እና አቶ ሽሻይ ልዑል በተባሉ የቀድሞ የአገልግሎቱ የሥራ ኃላፊዎች ላይ በሌሉበት ዛሬ ሚያዚያ 29 ቀን 2011 ዓ. ም. በከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት ክስ ይመሰረትባችዋል፡፡

የፍርድቤት መዶሻ

የፎቶው ባለመብት, Mark Metcalfe

በአቶ ጌታቸው ላይ፤ በ1996 ዓ. ም. የወጣውን የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32/1/ (ሀ) (ለ) እና 407/1/ (ለ) (ሐ) እና 407/3/ ላይ የተደነገገውን በመተላለፍ ሥልጣንን ያለአግባብ መገልገል ከባድ የሙስና ወንጀል መፈጸም እንዲሁም በ1996 ዓ. ም. የወጣውን የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32 (1) ሀ እና ለ እንዲሁም የሙስና ወንጀሎችን ለመደንገግ የወጣውን አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 9 /1/ (ለ) እና (ሐ) እና 9/3/ ላይ የተደነገገውን በመተላለፍ ሥልጣንን ያለአግባብ መገልገል ከባድ የሙስና ወንጀል ፈጽመዋል በሚል ክስ ቀርቦባቸዋል ሲል የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ አስታውቋል።

በሌሎቹ ሁሉም ተከሳሾች ላይ፤ በ1996 ዓ. ም. የወጣውን የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32/1/ (ሀ) (ለ) እና 407/1/ (ለ) (ሐ) እና 407/2/ ላይ የተደነገገውን በመተላለፍ ስልጣንን ያለአግባብ መገልገል፣ ከባድ የሙስና ወንጀል መፈጸም እንዲሁም በ1996 ዓ. ም. የወጣውን የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32 (1) ሀ እና ለ እንዲሁም የሙስና ወንጀሎችን ለመደንገግ የወጣውን አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 9 /1/ (ለ) እና (ሐ) እና 9/2/ ላይ የተደነገገውን በመተላለፍ ሥልጣንን ያለአግባብ መገልገል ከባድ የሙስና ወንጀል ፈጽመዋል በሚል ክስ እንደተመሰረተባቸው ተመልክቷል።

ሥልጣንን ያለአግባብ መጠቀም ክስ ሊቀርብባቸው የቻለው ተከሳሾች በግልጽ ከተሰጣቸው ሥልጣን ወይም ኃላፊነት አሳልፈው በመሥራት እንዲሁም ሥልጣናቸው ወይም ኃላፊነታቸው የማይፈቅድላቸውን በተለይም ሥልጣን ወይም ኃላፊነት ሳይኖራቸው በሌላ ሰው መብት ላይ ጉዳት እንዲደርስ በማሰብ በተበዳዮች ላይ ከባድ የሰብዓዊ መብት ጥሰት በመፈጸማቸው ነው ተብሏል።