የቀድሞው የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት ዋና ዳይሬክተር የነበሩት አቶ ጌታቸው አሰፋ የእስር ትዕዛዝ እንደወጣባቸው ተገለፀ

ዋናው አቃቤ ሕግ አቶ ብርሃኑ ፀጋዬ በትናንትናው ዕለት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረቡት የአምስት ወራት ሪፖርት የቀድሞው የደህንነት መስሪያ ቤት ኃላፊ አቶ ጌታቸው አሰፋን ለመያዝ ከትግራይ ክልል መንግሥት ትብብር ያለማግኘታቸውን ገልፀው ነበር።
ይህንን ተከትሎ የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ የሥራ ኃላፊዎች ዛሬ ከቀትር በኋላ በጽህፈት ቤታቸው በዚህና በሌሎች ጉዳዮች ላይ ለጋዜጠኞች መግለጫ ሰጥተው ለቀረቡላቸው ጥኣቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።
የቀድሞው የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት ዋና ዳይሬክተር የነበሩት አቶ ጌታቸው አሰፋ የፍትህ ተሳዳጅ ናቸው ወይ? በሚል ከቢቢሲ ለቀረበላቸው ጥያቄ በወንጀል የተጠረጠሩ እና የእስር ማዘዣ የወጣባቸው መሆኑን የጠቅላይ አቃቤ ጽህፈት ቤት ቃል አቀባይ አቶ ዝናቡ ቱኑ በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ ተናግረዋል።
ከዚህም በተጨማሪ በቡራዩ፣ በቤንሻንጉል፣ በሐዋሳና በሶማሌ ክልል በነበሩት ብጥብጥ እና ሁከቶች የመንግሥት ኃላፊዎችና የፀጥታው መዋቅር ተሳትፈዋል ሲል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ጽህፈት ቤት ተናግሯል።
የጽህፈት ቤቱ ቃል አቀባይ አቶ ዝናቡ ቱኑ ለጋዜጠኞች እንዳሳወቁት የብሔር ግጭትን እና መፈናቀል እንዲከሰት አንዳንድ የመንግሥት እና የፀጥታ ኃላፊዎች በማቀድ እና በገንዘብ በማገዝ ጭምር ድጋፍ አድርገዋል የተባሉ ተጠርጣሪዎችን የመለየት እና የመያዝ ሥራ እየተሰራ ነው።
የድንበር ተሻጋሪ እና አገራዊ ጉዳት የሚያደርሱ ወንጀሎች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ፍቃዱ ፀጋ ሐዋሳ ላይ የነበረውን ግጭት በሦስት መዝገብ ምርመራ ሲደረግነት ቆይቶ በሁለቱ መዝገቦች ላይ ክስ ተመስርቷል ብለዋል።
ተጠርጣሪዎቹ በከተማዋ በወላይታ እና በሲዳማ ብሔሮች መካከል ግጭት እንዲከሰት ያደረጉ እንዲሁም በማረሚያ ቤት የተፈፀመን ወንጀል ያከናወኑ ሲሆኑ ክስ ከተመሰረተባቸው መካከልም የቀድሞው የከተማዋ ከንቲባ ይገኙበታል።
75 ተጠርጣሪዎች ያሉበት መዝገብ ምርመራው አልተጠናቀቀም።
የኦሮሞ ነፃነት ግንባርን ለመቀበል ከነበረው ሥነ ሥርዓት ጋር በተያያዘ በቡራዩ እና አካባቢው ተከስቶ በነበረው ግጭት 37 ሰው የሞተ ሲሆን፤ በተተጨማሪ 26 ሰዎች ከአዲስ አበባ ሞተዋል።
ከሞት በተጨማሪ 315 ግለሰቦች ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን ከ17 ሚሊዮን ብር በላይ ንብረት ላይ ጉዳት ደርሷል።
ከዚህም ጋር በተያያዘ 649 ተጠርጣሪዎች ተይዘው የነበረ ሲሆን 320ዎቹ በወንጀሉ ለመሳተፋቸው ማስረጃ ባለመኖሩ እንዲለቀቁ ተደርጓል።
109 ተጠርጣሪዎች በግድያ በመሳተፍ እና በማነሳሳት ክስ ተመስርቷባቸዋል፤ እንዲሁም አስራ ሦስት በዋስ ተፈትተዋል።
በአዲስ አበባ ደግሞ 'ቄሮ አይገባም' በሚል ግጭት ያነሳሱና የተሳተፉ 68 ሰዎች ክስ ተመስርቶባቸዋል።
በቡራዩ በነበረው ግጭት አስቀድሞ የታቀደ ስለመሆኑ ምንም ዓይነት ማስረጃ አላገኝንም ያሉት ፍቃዱ፤ ኦነግን ለመቀበል ወደ አዲስ አበባ ይመጡ የነበሩ ወጣቶች አትገቡም እንገባለን በሚል ሙግት ግጭቱ ተለክሷል ብለዋል።
ሐሰተኛ ወሬዎች መሰራጨታቸው ለግጭቱ መፋፋም ምክንያት ሆኗል ያሉት አቶ ፈቃዱ፤ የስድስት ዓመት ልጅ ተገድላ በኦሮሞ ነፃነት ግንባር ሰንደቅ ዓላማ ተጠቅልላ መሞቷ መወራቱ ወንጀሉ ላይ እንዲሳተፉ የገፋፋቸው ሰዎች እንደነበሩ የገልፀው፤ የተባለው ድርጊት ስለመፈፀሙ ማስረጃ አላገኘንም ብለዋል።
በሀሰት የስድስት ዓመት ልጅ በቡድን ስትደፈር አይቻለሁ ያለች ግለሰብ እንዲሁም የእህቴ ጡት ተቆርጧል ያለ ግለሰብም በሐሰት ወሬ ሰውን በማነሳሳት ክስ ተመስርቷል።
በተጨማሪም መጪውን የገና በዓል ምክንያት በማድረግ በፌዴራል እና በክልል ማረሚያ ቤቶች ይገኙ ለነበሩ 530 የፌዴራል ታራሚዎች ይቅርታ ተደርጓል።
በይቅርታው ተጠቃሚ ከሆኑ ታራሚዎች መካከል ከህፃናት ጋር አብረው የታሰሩ ታራሚዎች፤ ዕድሜያቸው ከስድሳ ዓመት በላይ የሆናቸው ታራሚዎች፣ ታማሚ ታራሚዎች የሚገኙበት መሆኑን የፌዴራል የይቅርታ እና ምህረት ቦርድ ኃላፊ አቶ ዘለቀ ተናግረዋል።
የህገ ወጥ የገንዘብ እና የጦር መሳሪያ ዝውውር በተለያዩ ምክንያቶች እንዲበራከቱ ሆነዋል ያሉት የፅህፈት ቤቱ ቃል አቀባይ አቶ ዝናቡ ናቸው።
የህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር በአንድ በኩል የህግ ማዕቀፉ የላላ መሆኑ በሌላ በኩል ደግሞ በየቦታው ያለው ግጭት ገበያውን ስላደረው ይሄንን የሚከላከል ኮስተር ያለ ህግ መረቀቁን ቃል አቀባዩ አክለው ገልፀዋል።












