በአውስትራሊያ ከባድ ድርቅ አጋጠመ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ከአውስትራሊያ ግዛቶች በሕዝብ ብዛት ትልቋ የሆነቸው ኒው ሳውዝ ዌልስ ሙሉ በሙሉ በድርቅ መመታቷን ባለስልጣናት ተናገሩ።
ደረቃማው የበጋ ወቅት ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ በምሥራቃዊ አውስትራሊያ የከፋ የተባለውን ድርቅ አባብሶታል።
የኒው ሳውዝ ዌልስ ግዛት በአውስትራሊያ ከሚገኘው የእርሻ ምርት ውስጥ አንድ አራተኛውን የምታቀርብ ሲሆን፤ የሃገሪቱ ባለስልጣናት ዛሬ እንዳስታወቁት ግዛቲቱ ሙሉ በሙሉ በድርቅ ተመትታለች።
ይህንን ድርቅ ለመቋቋምም የግዛቲቱ አስተዳደርና የፌደራል መንግሥቱ 430 ሚሊዮን ዶላር የአስቸኳይ ጊዜ የእርዳታ ገንዘብ መድበዋል።
ይህ የተመደበው ገንዘብም በድርቁ ምክንያት ምርታቸውን አጥተው ለችግር ለተጋለጡ አርሶ አደሮች ድጋፍ፣ የውሃ እጥረትን ለመቋቋምና ለእንስሳት መኖ ለማቅረብ እንደሚውል ተገልጿል።
ባለፈው እሁድ ጠቅላይ ሚኒስትር ማልከም ተርንቡል አውስትራሊያ "ድርቅ የሚደጋገምባት ምድር" እየሆነች እንደሆነ አስጠንቅቀው ነበር።
ባለፈው ሐምሌ ወር በኒው ሳውዝ ዌልስ ግዛት ውስጥ በጣም ዝቅተኛ የዝናብ መጠን መመዝገቡን ባለስልጣናት ተናግረዋል። በቀጣዮቹ ወራትም ከተለመደው የበለጠ ደረቅ የአየር ሁኔታ እንደሚኖርም የአየር ትንበያ አመልክቷል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት አርሶ አደሮች ተደጋግሞ የሚከሰተው ድርቅ "የአውስትራሊያ የአየር ንብረት አካል" መሆኑን እንደተገነዘቡ ነገር ግን ድጋፍ እንሚያስፈልጋቸው ገልፀዋል።
በኒው ሳውዝ ዌልስ የሚገኙ አርሶ አደሮች ለአንድ የጭነት መኪና የእንስሳቶች መኖ እስከ 10ሺህ የአውስትራሊያ ዶላር እያወጡ እንደሆነ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልፀዋል።
"እንደዚህ አይነት አስቸጋሪ ጊዜ ሲያጋጥም መንግሥት ማድረግ የሚጠበቅበት ለአርሶ አደሮቹ ድጋፍ ማድረግ ነው" ሲሉ በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለአውስትራሊያ ብሮድካስቲን ኮርፖሬሽን ተናግረዋል።
ከኒው ሳውዝ ዌልስ ባሻገር አጎራባቿ የኩዊንስላንድ ግዛት ግምሽ ክፍልም በድርቅ ተመትቷል። በተጨማሪም የቪክቶሪያና ሳውዝ አውስትራሊያ ግዛቶች የተወሰኑ ክፍሎች ደረቅ የአየር ሁኔታ አጋጥሟቸዋል።













