ከቤንሻንጉል ጉሙዝ የተፈናቀሉ አርሶ አደሮች ችግር

በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች አብረው በሚኖሩ ህዝቦች መካከል የሚቀሰቀሱ ግጭቶች እንዲሁም የሚሰነዘሩ ጥቃቶች ሞት እና ውድመትን ከማስከተላቸውም ባለፈ በርካቶችን ለመፈናቀል መዳረጋቸው በተለይም ባለፉት ጥቂት ዓመታት ተደጋግሞ የሚስተዋል እውነታ ሆኗል።
የተፈናቃዮቹ ቁጥር እጅጉን ከፍተኛ መሆን ለችግሩ መፍትሄ ለመስጠት የሚደረገውን ጥረት አዳጋች ያደረገው ይመስላል።
ግጭቶች በተከሰቱባቸው አካባቢዎች ያሉ ቅራኔዎችን የመፍታቱን ያህል መልሶ የማስፈር እና የማቋቋም ኃላፊነቶች ለአገሪቷ ከባድ የራስ ምታት ሆኗል።
ባለፈው ጥቅምት ወር ከቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ካማሼ ዞን የተፈናቀሉ አርሶ አደሮች እስካሁን ድረስ ይህ ነው የሚባል መፍትሄ አላገኘንም ይላሉ።
በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ካማሼ ዞን በአካባቢው ተወላጆች እና ከተለያዩ ቦታዎች ወደ ስፍራው በማቅናት ኑሯቸውን በመሰረቱ አርሶ አደሮች መካከል ግጭት ተቀስቅሶ ሞትና የንብረት ውድመትን ማስከተሉ ባለፈው ጥቅምት ወር መዘገቡ የሚታወስ ነው።
ግጭቱ ካፈናቀላቸው በመቶዎች የሚቆጠሩ ቤተሰቦች መካከል ከአምስት መቶ የሚልቁ አባወራዎች በባህር ዳር ከተማ ተጠልለው ይገኛሉ።
ከተፈናቃዮቹ መካከል አንዱ የሆኑት አቶ አበባው ጌትነት በምዕራብ ጎጃም ዞን ውስጥ የምትገኘውን የትውልድ ቀያቸው ቋሪት ወረዳን ለቀው ወደ ካማሼ ዞን ደዴሳ ቀበሌ ያመሩት በ1992 ዓ.ም እንደነበር ይናገራሉ። ብዙ አዝመራ በማይሰበሰብበት ጥቅምት ወር ላይ ግጭቱ በመነሳቱ ጨርቄን ማቄን ሳይሉ ጥለው እንደወጡ ይናገራሉ።
"ግጭቱንም አላወቅነውም። ትንሽ የተወሰነ ረብሻ ነበር የመሰለን። አዝመራ የሚሰበሰብበት ወቅት ስላልነበር 527 አባወራ ምንም ነገር ሳይዝ ትልቅ ኪሳራ ደርሶበት ንብረቱን አጥቶ ለመሰደድ ተገዷል። በባህርዳር አባይ ማዶ የምግብ ዋስትና ግቢ መጋዘን ውስጥ ነው የምንገኘው" ብለዋል።
ግጭቶችም ሆነ መፈናቀል ሲከሰቱ የጥቅምቱ የመጀመሪያው ባይሆንም ከወትሮው ግን በጉዳት መጠን የላቀ እንደሆነ የሚያስረዱት ደግሞ ሌላኛው ተፈናቃይ አቶ ልመንህ መኩሪያ ናቸው።
ኑሯቸውን በደዴሳ ቀበሌ ከመሰረቱበት 1999 ዓ.ም አንስቶ በእርሻ፣ በከብት ማርባት እና በአነስተኛ ንግድ ይተዳደሩ እንደነበር የሚገልፁት አቶ ልመንህ፤ አሁን ራሳቸውንም ሆነ የሚያስተዳድሩትን ቤተሰብ ለመደጎም በባህር ዳር ከተማ የተለያዩ የጉልበት ሥራዎችን ከማፈላለግ የዘለለ አማራጭ እንዳጡ ይገልፃሉ።
"የሚያሳዝንና የሚያስለቅስ ነገር ነው ያለንበት ሁኔታ። ከዛሬ ነገ ችግራችሁ ይፈታል በማለት እስካሁን ድረስ ህብረተሰባችን እየተንገላታና እየተሰቃየ ይገኛል። መሬት ላይ ነው የምንተኛው፤ ምንም ነገር የለንም። በቃ የቀን ሥራ እየሰራሁ ነው ያለሁት " ብለዋል።
ተፈናቃዮቹ ችግሮቻቸውን ይዘው ዘላቂ መፍትሄ ይበጅላቸው ዘንድ ለክልሉ አስተዳደር ፅህፈት ቤቶች ጥያቄ ማቅረባቸውን ይናገራሉ።
ባለፈው እሁድም ከክልሉ ፕሬዚዳንት አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ጋር ተቀምጠው መወያየታቸውንም ያስረዳሉ።
ነገር ግን ክልሉ ያቀረበላቸው ሁለት አማራጮች ፤ ወደተፈናቀሉበት ካማሼ ዞን መመለስ ወይንም ቀድሞ ትተዋቸው በሄዷቸው የትውልድ ቀየዎቻቸው ዳግመኛ መስፈር፤ ያስደሰቷቸው አይመስልም።
"ወደ ቀያችን እኮ ተመልሳችሁ ተቀመጡ ሲባል ቦታ፣ መጠለያና መቋቋሚያ እንስጣችሁ አይደለም የተባልነው። ምንም የተመቻቸ ነገር የለም። ወደቀያችሁ ተመልሳችሁ ራሳችሁን በራሳችሁ ማቋቋም ወይም መመለስ የሚል አማራጭ ነው የተሰጠን። ከዚህ በኋላ የፌደራል መንግሥት የሚለንን ሰምተን እግዚአብሄር እንዳደረገን ከመሆን ውጭ ምንም ተስፋ የለንም" በማለት በተስፋ መቁረጥ ይናገራሉ።












