የሕፃናት ጋብቻ ቀንሷል- ዩኒሴፍ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በዓለም አቀፍ ደረጃ ሕፃናት ወደ ትዳር የመግባታቸው አሃዝ በከፍተኛ ደረጃ መቀነሱን የተባበሩት መንግሥታት ሕፃናት ድርጅት አስታወቀ።
እንደዩኒሴፍ ከሆነ ባለፉት አስር ዓመታት 25 ሚሊዮን የሕፃናት ጋብቻን መከላከል ተችሏል።
በአሁኑ ወቅት ከ18 ዓመት በታች ከሆናቸው አምስት ልጆች አንዳቸው የሚዳሩ ሲሆን ይህ ቁጥር ከአስር ዓመት በፊት ከአራት ልጆችን አንድ ነበር።
እንደ አለም አቀፉ የሕፃናት ድርጅት ከሆነ የደቡብ ኤስያ ሀገራት የሕፃናት ጋብቻ ቁጥርን በከፍተኛ ደረጃ በመቀነስ ተጠቃሽ ሆነዋል።
በህንድ ይህ ሊሳካ የቻለው የተሻለ ትምህርት በመስጠት እና የሕፃናት ጋብቻ ያለውን ጉዳት በማሳወቅ በተሰራው ሥራ ነው።
ኢትዮጵያ የሕፃናት ጋብቻን በአንድ ሶስተኛ መቀነስ ብትችልም ችግሩ በአፍሪካ ሃገራት አሁንም ከፍተኛ ነው።
ዩኒሴፍ የጾታ ጉዳይ አማካሪ የሆኑት አንጁ ማልሆርታ እንደሚሉት የሕፃናት ጋብቻ በተለይ ሴቶች ህይወት ላይ ከሚያደርሰው ተጽእኖ አንጻር "የትኛውም መቀነስ የሚያስደስት ዜና ቢሆን ገና ብዙ ርቀት መጓዝ ይጠበቅብናል።"
"ሴቶች በልጅነታቸው እንዲያገቡ ሲገደዱ ወዲያውም ሆነ በቀሪው ህይወታቸው ላይ ችግሮች ይከሰታሉ" ብለዋል።
"ትምህርት የመጨረስ ዕድሏ ሲቀንስ፤ በባሏ ጥቃት የማስተናገድ እና በወሊድ ጊዜ ለሚደርሱ ችግሮች የመጋለጥ ዕድሏ ከፍተኛ ይሆናል። ትልቅ ማህበረሰባዊ ችግሮች እና ከትውልድ ወደ ትውልድ ለሚዘልቅ ድህነት የመጋለጥ ዕድሏም ከፍተኛ ነው።"
እንደሪፖርቱ ከሆነ የሕፃናት ጋብቻ ችግር ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ ሀገራት አካባቢ እየሆነ መጥቷል።
ከአስር ዓመታት በፊት ከአምስት የሕፃናት ጋብቻ አንዱ ብቻ ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ ሃገራት የሚመዘገብ ሲሆን ይህ ቁጥር ወደ አንድ ሶስተኛ ከፍ ማለቱን ዩኒሴፍ አስታውቋል።
የዓለም ሃገራት መሪዎች በተባበሩት መንግስታት ዘላቂ የልማት ጎሎች መሠረት የሕፃናት ጋብቻን በአውሮፓዊያኑ 2030 ለማስቀረት ቃል ገብተዋል።
ይህን ግብ ለማሳካት ጥረቱን በማጠናከር "በዚህ መጥፎ ተግባር ምክንያት የልጅነት ጊዜያቸው የሚነጠቅባቸው በሚሊዮን የሚቆጠሩ ህጻናትን መታደግ ይገባናል" ሲሉ ማልሆትራ አስታውቀዋል።












