ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ቀይ መስቀል ህወሓት ምርኮኞችን እለቃለሁ ባለበት ኦፕሬሽን ላይ ተሳትፎ የለኝም አለ
ዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ማኅበር የትግራይ አመራሮች ምርኮኞችን እንለቃለን ባሉት ሂደት ውስጥ ምንም አይነት ተሳትፎ የለኝም ሲል ለቢቢሲ ገለጸ።
የትግራይ ኃይሎች ትናንት ሐሙስ ግንቦት 11፣ 2014 ዓ.ም በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት የተማረኩ ናቸው ያሏቸውን ከ4ሺህ በላይ የአገር መከላከያ ሠራዊት አባላትን በምህረት እንለቃለን ብለው ነበር።
በህወሓት የሚተዳደረው የክልሉ ቴሌቪዥን ጣቢያ እንደዘገበው በምህረት የሚለቀቁት ወታደሮች ለቀይ መስቀል ተላልፈው ይሰጣሉ ብሎ ነበር።
ትግራይ ቴሌቪዥን በዚህ ዘገባው ምርኮኞች የሚለቀቁት ከፌደራሉ መንግሥት ጋር አንዳች ስምምነት ተደርሶ ስለመሆኑ ያለው ነገር የለም።
በተመሳሳይ የአሜሪካ ድምጽ ራዲዮ የመቀለ ምርኮኞች ማዕከል አስተባባሪ ብርሃነ በቀለን ጠቅሶ በሰራው ዘገባ፤ 4208 የጦር ምርኮኞች ዛሬ የትግራይ ኃይሎች እስከሚቆጣጠሩት አካባቢ በመኪና ተጓጉዘው ለዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ማኅበር ተላልፈው እንደሚሰጡ ዘግቧል።
ይሁን እንጂ የዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል ማኅበር የአፍሪካ ቃል አቀባይ አሊዮና ሲዬንኮ፤ "ዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ማሕበር በእዚህ ኦፕሬሸን ውስጥ ተሳታፊ አይደለም" ሲሉ ለቢቢሲ ምላሽ ሰጥተዋል።
ቢቢሲ በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ ለመጠየቅ የህወሓት ባለሥልጣናትን ለማግኘት ያደረገው ጥረት አልተሳካም። በተመሳሳይ የፌደራል መንግሥቱ በጉዳዩ ላይ እስካሁን ያለው ነገር የለም።
በትግራይ ክልል ተቀስቅሶ ወደ አጎራባች አማራ እና አፋር ክልሎች ተዛምቶ በነበረው የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ካስከተለው ከፍተኛ ሰብዓዊ ኪሳራ በተጨማሪ፤ በሁለቱም ወገን ያሉ በሺዎች የሚቆጠሩ የሠራዊት አባላት ምርኮኛ እንደሆኑ ይታመናል።
ይህ ህወሓት በምርኮ የያዝኳቸውን የኢትዮጵያ አገር መከላከያ ጦር አባላት በምህረት እለቃለሁ የሚለው መግለጫ የተሰማው ጋብ ብሎ የነበረው ጦርነት ዳግም ሊያገረሽ ይችላል የሚል ከፍተኛ ስጋት ባደረበት ወቅት ነው።
ግንቦት 09/2104 ዓ.ም. የኤርትራ መንግሥት በማስታወቂያ ሚኒስቴሩ በኩል ባሰፈረው መልዕክት ህወሓት በኤርትራ ድንበር በኩል እና በምዕራብ ትግራይ አቅጣጫ በሁለት ግንባሮች ጦርነት ለመክፈት እየተዘጋጀ ነው ብሎ ነበር።
ለዚህም ከትግራይ አመራሮች በኩል በተሰጠው ምላሽ ኤርትራ በጦርነቱ በርካታ ጥሰቶችን እንደፈጸመችና እንዲሁም የትግራይን ግዛቶች ተቆጣጥራ እንደምትገኝ ጠቅሰው በሰላምም ይሁን በሌላ መንገድ ከእነዚህ ግዛቶች ነጻ ይወጣሉ ብለዋል።
ከቀናት በፊት ደግሞ የአማራ ክልል ከህወሓት በኩል ሊሰነዘር ይችላል ላለው ሌላ ዙር ወረራ የክልሉ የፀጥታ መዋቅር ዝግጁ እንዲሆን ትዕዛዝ አስተላልፎ ነበር።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በበኩሉ በሰሜን ኢትዮጵያ በትግራይ ኃይሎች እና በፌደራል መንግሥት ኃይሎች መካከል ውጥረት እየጨመረ መምጣቱ እንዲሁም አልፎ አልፎም ግጭቶች ሪፖርት መደረጋቸው እንዳሳሰበው ገልጾ ነበር።