ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኮቪድ-19፡ በመላው ዓለም በኮቪድ የሞቱ ሰዎች ትክክለኛው ቁጥር 15 ሚሊዮን እንደሚጠጋ ተገለጸ
የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ከተከሰተበት ጊዜ አንስቶ እስካሁን በዓለም ዙሪያ 15 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎችን ሕይወት መቅጠፉን የዓለም ጤና ድርጅት ግምት አመለከተ።
ይህም ባለፉት ሁለት ዓመታት በበሽታው ሰበብ ሞተዋል ተብለው ከታሰቡት ሰዎች ቁጥር በ13 በመቶ ከፍ ያለ ነው ተብሏል።
የዓለም ጤና ድርጅት እንደሚያምነው በርካታ አገራት በወረርሽኙ ሰበብ የሞቱ ሰዎችን አሃዝ በትክክል ሪፖርት ባለማድረጋቸው በይፋ የተመዘገበው የሟቾች ቁጥር 5.4 ሚሊዮን ብቻ ነው።
ሕንድ ውስጥ 4.7 ሚሊዮን ሕዝብ በበሽታው እንደሞቱ የሚያምነው ድርጅቱ፣ ይህም አገሪቱ ሪፖርት ካደረገችው በአስር እጥፍ የሚበልጥ ነው።
የሕንድ መንግሥት የዓለም የጤና ድርጅት ባቀረበው ግምት ሥነ ዘዴ ላይ ጥያቄ እንዳለው ቢገልጽም፣ ነገር ግን የሟቾች ቁጥርን በተመለከተ ሌሎች ጥናቶች ተመሳሳይ መደምደሚያ ላይ ደርሰዋል።
የዓለም ጤና ድርጅት ባደረገው ጥናት በወረርሽኙ የሞቱ ሰዎችን በሚመለከት የተለያዩ መመዘኛዎችን የዳሰሰ ሲሆን አብዛኞቹ ሰዎች ለህልፈት የተዳረጉት በቀጥታ ከበሽታው ጋር በተያያዙ ምክንያቶች መሆኑን አመልክቷል።
የሟቾቹን አሃዝ በተመለከተ የዓለም ጤና ድርጅት የመረጃ ክፍል ባልደባ የሆኑት ዶ/ር ሳሚራ አስማ እንዳሉት በወረርሽኙ ሰበብ የሞቱት ሰዎች ቁጥር እጀግ አስደንጋጭ ነው።
"ቁጥሩ እጅግ ከፍተኛ ነው፣ ስለዚህም በወረርሽኙ ሰበብ ለተቀጠፉ ነፍሶች እውቅና መስጠት ያስፈልጋል። ፖሊሲ አውጪዎችንም ተጠያቂ ማድረግ ያስፍለጋል" ብለዋል።
አክለውም "የሞቱ ሰዎችን አሃዝ በትክክል ካላወቅን፣ ወደፊት ለሚከሰቱ ወረርሽኞች በአግባቡ ለመዘጋጀት የሚኖረን ዕድል ያመልጠናል።" ሲሉ ተናግረዋል።
ከሕንድ በተጨማሪ በወረርሽኙ ሰበብ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ዜጎች የሞቱባቸው አገራት ሩሲያ፣ ኢንዶኔዢያ፣ አሜሪካ፣ ብራዚል፣ ሜክሲኮ እና ፔሩ መሆናቸውን የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ አመልክቷል።
"ዜሮ ኮቪድ" መመሪያን፣ የጅምላ ምርመራና ለይቶ የማቆየት መንገድን የምትከተለው ቻይናን ጨምሮ በርካታ አገራት ደግሞ ዝቅተኛ የሞት መጠን የተመዘገበባቸው ሲሆን፣ አውስትራሊያ፣ ጃፓንና ኖርዌይ ቫይረሱን ለመከላከል ጥብቅ የጉዞ ቁጥጥር እያደረጉ ነው።
በወረርሽኙ የሞቱ ሰዎችን በተመለከተ የወጣውን ሪፖርት በማዘጋጀት የተሳፉት ባለሙያዎች አፍሪካን በተመለከተ በጣም ውስን መረጃ ብቻ ስላላቸው በአብዛኛው በግምት ላይ ለመመርኮዝ መገደዳቸውን ተናግረዋል። በአፍሪካ ካሉ 54 አገራት ከ41ዱ አስተማማኝ መረጃ ለማግኘት አዳጋች እንደሆነ ተነግሯል።
ባለሙያዎቹ ጨምረውም ስለበሽታው አስተማማኝ መረጃ ለማግኘትና ወደፊት ለሚከሰቱ ተመሳሳይ የጤና ችግሮች ቀድሞ ለመዘጋጀት አገራት አስፈላጊውን ሥርዓት መዘርጋት እንዳለባቸው አሳስበዋል።