ለ78 ጊዜ የኮቪድ ምርመራ አድርጎ 'ፖዘቲቭ' የሆነው ግለሰብ

ቱርካዊው ሙዛፈር ካያሳን የደም ካንሰር ህመምተኛ ሲሆን ከዓመት በፊት ባደረገው ምርመራ የኮሮናቫይረስ እንዳለበት ሲነገረው ተስፋ ቆርጦ ነበር።

ነገር ግን ኮቪድ ከነበረበት የካንሰር ህመም ጋር ተደምሮ የከፋ ችግር ሳያስከትልበት ወራት ተቆጥረው ከዓመት በላይ ሆኖታል።

ኮቪድ-19 የያዛቸው አብዛኞቹ ሰዎች ለጥቂት ሳምንታት ከታመሙ በኋላ አገግመው ከቫይረሱ ነጻ ይሆናሉ፤ የተወሰኑት ተደግሞ በሚፈጠርባቸው የጤና እክል ለሞት ሊዳረጉ ይችላሉ።

የሙዛፈር ግን የተለየ ነው፤ ባለፉት 14 ወራት ለ78 ጊዜ ምርመራ አድርጎ አስካሁን ድረስ ፖዘቲቭ ነው። ከዚህ አንጻር በኮቪድ ተይዞ ለረጅም ጊዜ ቫይረሱ ከሰውነቱ ሳይጠፋ የቆየ የመጀመሪያው ሰው ሳይሆን አይቀርም።