በኢራን ቤት ውስጥ የተጠመቀ አልኮል የጠጡ 8 ሰዎች ሞቱ

በኢራን ባንደር አባስ ከተማ በቤት ውስጥ የተጠመቀ አልኮል የጠጡ ስምንት ሰዎች መሞታቸውን የአገሪቱ የመገናኛ ብዙኃን ዘገቡ።

ከሟቾች በተጨማሪ 51 ሰዎች የአልኮል መመረዝ አጋጥሟቸው በሆስፒታል ሕክምና እየተደረገላቸው እንደሆነ የአካባቢው ጤና ኃላፊ ዶ/ር ፋቴማ ኖውሩዚአን በጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ተናግረዋል።

የአካባቢ ጤና ኃላፊዋ በሆስፒታል ከሚገኙ ሰዎች መካከል 7ቱ በጽኑ ታመው እንደሚገኙ ጨምረው ተናግረዋል።

ፖሊስ በበኩሉ ይህን የተመረዘ አልኮል የጠመቁ እና ያከፋፈሉ ናቸው ያላቸውን 8 ሰዎች ይዞ ማሰሩን አስታውቋል።

በኢራን እስላማዊ ሪፓብሊክ የእልምና እምነት ተከታዮች ካልሆኑ ጥቂት ነዋሪዎች ውጪ ለተቀረው ሕዝብ አልኮል መጠጣት፣ ማምረት፣ መሸጥ እና ማከፋፈል በጥብቅ የተከለከለ ተግባር ነው።

በኢራን አልኮል ሲጠጣ የተገኘ ሙስሊም የ80 ጅራፍ ግርፋት ይጠብቀዋል።

የባንዳር አባስ ከተማ ባለሥልጣናት የተጠመቀውን የአልኮል መጠጥ ምን እንደመረዘው እስካሁን ድረስ አላወቁም። ይሁን እንጂ ከዚህ ቀደም በኢራን ሜታኖል የተሰኘ ኬሚካል የተቀላቀለበት የአልኮል መጠጥ የወሰዱ ሰዎች ለሕልፈት ተዳርገው ነበር።

ሜታኖል በረዶ የማይሰራ ፈሳሽ እና ነዳጅ ለማምረት በስፋት ጥቅም ላይ ይውላል። ይሁን እንጂ በአንዳንድ ቦታዎች የመጠጦችን የአልኮል መጠን ከፍ ለማድረግ በሕገ-ወጥ መንገድ ጥቅም ላይ ይውላል።

ይህ አደገኛ ኬሚካል በአነስተኛ መጠን እንኳ ቢወሰድ ዓይነ ስውርነትን ከፍ ሲልም ሞትን ሊያስከትል ይችላል።

የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መቀስቀስን ተከትሎ በኢራን በሜታኖል የሚመረዙ ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ መጠን ጭምሮ ነበር።

ይህም የሆነው ሰዎች በተሳሳተ አመለካከት አልኮል መጠጣት ወይም በአልኮል መጉመጥመጥ የኮቪድ-19 ቫይረስን ይከላከላል የሚል እምነት ስለነበራቸው ነው።

ከአንድ ወር በፊት የኢራን ጤና ሚኒስቴር በሦስት ወራት ውስጥ 500 ሰዎች ተመርዘው ሕይወታቸው ማለፉን እና ከ5ሺህ ያላነሱ ደግሞ ሕክምና እንዳስፈለጋቸው ገልጾ ነበር።