ድርቅ፣ ረሃብና ሁከት ያጠላበት የዘንድሮው ረመዳን

አቶ መሐመድ አደን ኑሯቸውን በሶማሌ ክልል፤ ጎዴ ከተማ ካደረጉ አመታት ተቆጥረዋል። የ65 ዓመቱ መሐመድ ምንም እንኳን በሸበሌ ተፋሰስ አቅራቢያ በምትገኘው ጎዴ ቢኖሩም በክልሉ የተከሰተው ድርቅ አሳሳቢነት እና የደረሰውን ጉዳት በቅርብ ያውቁታል።

"ረመዳን ብዙ ግዜ በዝናብ ነበር የሚጀምረው። በዚህ አመት ግን ድርቅ መጣ። ከብቶች አለቁ። አልሃምዱሊላሂ መጨረሻ ላይ ግን ዝናብ ጥሎልናል። ዝናቡ የምንፈልገውን ያህል ባይሆንም አላሃምዱሊላሂ ውሃ አግኝተናል" ሲሉ አቶ መሐመድ ይናገራሉ።

በርካታ የሙስሊም ማኅብረሰብ ባለባት ኢትዮጵያ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሙስሊሞች ለ30 ቀናት ያህል የሚቆየውን የረመዳን ወር በጾም እና በጸሎት ያሳልፋሉ።

ባለፉት ሁለት አመታት የረመዳን ወራት የኮሮናቫይረስ ወረርሺኝን መከሰት ተከትሎ የጾሙ ወቅት ያልተለመዱ ሁነቶች የታዩበት እንደነበረ በወቅቱ የተሰነዱ ዘገባዎች ያስረዳሉ።

በተለይም በ2012 መስጊዶች የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት ተዘግተው ሕዝበ ሙስሊሙም በረመዳን ወቅት ቁልፍ የሚባሉትን የሃይማኖቱን ሥርዓቶች ተሰባስቦ የመስገድ ብሎም ያለው ለሌለው የሚያካፍልበት ሰደቃ በመስጂዶች ማካሄድ ከባድ የነበረበት ወቅት እንደነበርም አይዘነጋም።

ጎንደር

የ2014ቱ የረመዳን ጾም የመጨረሻ ሳምንት ለሕዝበ ሙስሊሙ አዲስ ፈተናዎችን ይዞ ብቅ ያለ ነበር።

በጎንደር እና አካባቢዋ ታዋቂ የባሕል ሃኪም የነበሩት አባ ሼክ ከማል ለጋስ ሥርዓተ ቀብር ለማካሄድ ሚያዚያ 18 በርካታ የከተማዋ ነዋሪዎች ከ400 ዓመታት በላይ አገልግሎት እየሰጠ በነበረው የሼህ ኤልያስ መካነ መቃብር ቦታ ላይ በተፈጠረ ግርግር የበርካታ ሰዎች ሕይወት ተቀጥፏል።

የክልሉ የእስልምና ጉዳዮች በቀብር ሥነ ሥርዓቱ ላይ የታቀደ ጥቃት መፈጸሙን ገልጿል።

በጎንደር ከተማ መስጂዶች፣ የንግድ ሥፍራዎች እንዲሁም የሙስሊም ነዋሪዎች መኖሪያ ቤቶች የጥቃት ሰለባ መሆናቸውን የከተማው የእስልምና ጽሕፈት ቤት መግለፁ የሚታወስ ነው። ቀውሱ በተመሳሳይ ወደ ደባርቅ ከተማ ተዛምቶ የሰው ሕይወት አልፏል፤ እንዲሁም መስጂዶች ተቃጥለዋል።

የሀዲያና ስልጤ አገረ ስብከት ጽሕፈት ቤት ይፋ እንዳደረገው በደቡብ ክልል፣ ስልጤ ዞን፣ ወራቤ ከተማ ሁለት ቤተ ክርስቲያኖች እንዲሁም አንድ ገዳም ቃጠሎ ደርሶባቸዋል። ይህንን ድርጊት የጎንደሩን ጥቃት እያወገዙ የነበሩ የከተማዋ ነዋሪዎች የፈፀሙት ነው ሲልም ሃገረ ስብከቱ ከሷል።

ለአንድ ሳምንት ገደማ የቀጠለው ውጥረት የኢድ አል ፈጥር በአልን በጋራ ሰላት ለመስገድ በተሰበሰቡ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ጋርም ደርሶ በርካቶች ከሰላቱ በፊት ተበትነዋል። እንዲሁም የጎንደር ከተማ ኡለማ ምክር ቤት ሕዝበ ሙስሊሙ በየመኖሪያ ቤቱ በዓሉን እንዲያሳልፍ ባደረገው ጥሪ መሰረት በከተማዋ የኢድ ሰላት እንደ ከዚህ ቀደሙ በአደባባይ ሳይደረግ ቀርቷል።

ትውልድ እና እድገታቸውም በጎንደር የሆነው ኡስታዝ በድሩ ሁሴን ይህንን ክስተት በቅርበት ሲከታተሉ ቆይተዋል። ኡስታዝ በድሩ በጎንደር ከተማ የተፈጠረው ክስተት አንድን ማሕበረሰብ በእምነቱ ነጥሎ ያጠቃ "የሽብር ተግባር ነው" ይላሉ።

"በየትኛውም ዕምነት ያለ ንጹህ ህሊና ያለው ሰው ሊያወግዘው ይገባል። ይህ ሰዎችን ስሜታዊ አድርጎ ከጉዳዩ ጋር ግንኙነት የሌላቸውን ክርሰቲያኖች እና ቤተክርስቲያኖችን ጥቃት ውስጥ እንዳይጥል ጥሪ አደርጋለሁ" ሲሉም ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ኡስታዝ በድሩ ችግሩ በአካባቢው የጸጥታ ኃይል ይፈታል የሚል እምነት እንደሌላቸውም ይናገራሉ። ለዚህም በርከት ያለ ቁጥር ያለው የፌደራል ኃይል ወደ አካባቢው ገብቶ ችግሩን በተለይም በጥፋቱ የተሳተፉ ሰዎች ተለይተው እንዲወጡ ብሎም የጥቃቱን መጠን እንዲለይም ጠይቀዋል።

የፌደራል መንግሥትና የአማራ ክልል መስተዳደር ግጭቱን ተከትሎ እየተወስዱ ስላሉ እርምጃዎች እንዳሳወቁት ከተከሰተው ችግር ጋር በተያያዘ ከ300 በላይ ተጠርጣሪዎች በፀጥታ ኃይሎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን መግለጻቸው ይታወሳል።

መቀለ

በትግራይ ክልል፤ መቀለ ከተማ ነዋሪቱን ያደረገው ሃሰን በመቀለ ዩኒቨርሲቲ መምህር ነው። ሃሰን ትግራይ ውስጥ ጦርነት ከተቀሰቀሰ ወዲህ ለሁለተኛ ጊዜ የረመዳን ጾምን በጦርነት ቀጠና ውስጥ ሆኖ ጾሟል።

ይህ ጦርነት ከተጀመረ ጀምሮ አምስት የቤተሰብ አባላቶቹን በሞት ተነጥቋል። ቀሪዎቹ ከትግራይ ተሰደዋል እንዲሁም ትግራይ ውስጥ ያሉትንም ስላሉበት ሁኔታ የሚያውቀው ነገር እንደሌለም ይናገራል።

"በርግጥ ጾሙን ተላምደነው ቆይተናል። ምክንያቱም ረሃብ አለ፤ ሰውም በጣም ተቸግሯል። ያ ስሜት ስላለ ከሞራል አንጻር ከዚህ በፊት ከነበሩት የረመዳን ጾሞች አንጻር ትክክል የማይመስል ጾም ነው" ሲል ሃሰን ለቢቢሲ ተናግሯል።

ባለፈው አመት ጾሙ የመከላከያ ሰራዊት መቀለ ከተማን ተቆጣጥሮ በነበረበት ወቅት ላይ መዋሉን እና በወቅቱ በነበረው የሰዓት እላፊ ምክንያት ከኢፍጣር በኋላ ወደ መስጊድ ሄዶ ጸሎቶችን ማድረግ ብሎም መሰባሰብ የማይቻልበት ወቅት እንደነበረ ያስታውሳል።

"የተርሃዊ ሰላት በረመዳን ወቅት እጅግ ወሳኝ ከሚባሉት ክንውኖች መሃል ነው። ማታ መውጣት ስለማይቻል ያኔ ተርሃዊን መስገድ አልቻልንም ነበር። የተቸገሩ ሰዎችንም ለማገዝ የመቅሪብ ሰአቷን ነው የምንጠቀምበት፤ ያም የማይቻል ነበር። የበአል አከባበሩን ጨምሮ ብዙም ጥሩ ስሜት አልነበረውም። ወደ ገጠርም መሄድ አይቻልም ነበር" ሲል ሃሰን የ2013ቱን የረመዳን ወር ያወሳል።

ከአንድ አመት በኋላም ሁኔታዎች ተባብሰው ሃሰን ጾሙን ለብቻው መጾሙን ይናገራል። ከመቀለ ከተማ ወጥቶ ለመሄድም በነዳጅ እጥረት ምክኒያት ትራንስፖርት አለመኖሩ እንቅፋት ሆኖበታል።

"መቀለ ላይ ከምዕራብ ትግራይ ተፈናቅለው የመጡ ሰዎች አሉ። ከዚህ በፊት ስራ ኖሯቸው ጥሩ ገቢ የነበራቸው ሰዎች ደጅ ወጥተዋል። ስለዚህ ሁለት ዳቦ ያለው አንዱን ወደ መስጊድ ወስዶ ላልቻሉ ሰዎች ማፍጠሪያ ሲያካፍል ቆይቷል'' ሲልም ሃሰን ያስረዳል።

በትግራይ ክልል ያለውን የምግብ እጥረት ለመቋቋም እና በመጪው 15 ቀናት ውስጥ አስፈላጊውን የምግብ ስርጭት ለማድረግ 4675 ሜትሪክ ቶን እህል በየቀኑ ማስገባት እንደሚያስፈልግ የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ (ዩኤን ኦቻ) ገልጿል።

ነገር ግን በተገባደደው የአውሮፓዊያኑ ወር ወደ ክልሉ የገባው እርዳታ 3400 ሜትሪክ ቶን ሲሆን ይህም በአንድ ቀን እንዲገባ ከሚፈለገው ያነሰ ነው። እንደ ኦቻ መረጃ በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል 5.2 ሚሊዮን ህዝብ አስቸኳይ ሰብአዊ እርዳታ የሚያስፈልገው ሲሆን እስካሁን ድረስ ለ1.5 ሚሊዮኑ ብቻ ነው ድጋፍ ማድረግ የተቻለው።

ሃሰን እንደሚለው እየገባ ያለው እርዳታ ለውጥ አላመጣም። በመሬት ላይ ካለው ፍላጎት ጋር ሲነጻጸር እጅግ አስከፊ አደጋ ላይ ላሉት እንኳን በቂ አይደለም ብሎም ያምናል።

''ሕብረተሰቡ እርስ በእርሱ ለመተጋገዝ መቸገር ጀምሯል'' ሲል ሃሰን ከተማዋ ውስጥ ያለውን ድባብ ያስረዳል።

ጎዴ

ከአርባ አመት ወዲህ ታይቶ የማይታወቅ የተባለለት እና ምስራቅ አፍሪካን ያጠቃው ድርቅ በኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ ስምንት ሚሊዮን ሰዎችን ለድርቅ አደጋ ዳርጓል።

በጎረቤት አገር ሶማሊያም ስድስት ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች በዚሁ ድርቅ የተጠቁ ሲሆን ይህ ቁጥር ሊያሻቅብ እንደሚችል የዩኤን ኦቻ መረጃ ያሳያል። በአጠቃላይ ከ25 ሚሊዮን በላይ የሚሆን የቀጠናው ሕዝብ በዚህ ድርቅ ምክንያት ለረሃብ አደጋ ተጋልጧል።

በሶማሌ ክልልም የዝናብ እጥረቱ ከባድ ሙቀት ከማስከተሉ ባሻገር በዋናነት የከብቶች መኖ እና ውሃ ማጣት ነዋሪውን ስጋት ላይ የጣለ መሆኑን የጎዴው ነዋሪ አቶ መሃመድ አደን ይናገራሉ።

በተገባደደው የጾም ወቅትም ድርቁን እና በተለይም በሰሜን ኢትዮጵያ የተከሰተውን ጦርነት አስመልክቶ ጸሎት በተደረገ ቁጥር ለፈጣሪ ተማጽኗቸውን ሲያሰሙ መቆየታቸውን አቶ መሃመድ ያወሳሉ።

ለትምህርትም ሆነ ለሥራ በተለያዩ የምስራቅ ኢትዮጵያ ክፍሎች ተዘዋውረው የኖሩት አቶ መሃመድ በእድሜያቸው እንዲህ አይነት ፈታኝ ወቅት አይተው እንደማያውቁ ይናገራሉ።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ መሃመድ እስከ ሚያዝያ ወር መጨረሻ ድረስ ብቻ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ከብቶች በድርቁ ምክንያት መሞታቸውን ለመንግሥት መገናኛ ብዙሃን ገልጸው ነበር።

ስለመጪው ረመዳን ተስፋ እና ስጋቶች

የእስልምና ሃይማኖት መምህሩ ኡስታዝ በድሩ ከምንም በላይ የጥላቻ ንግግሮች እና ሰበካዎች ካልቆሙ መጪው ጊዜ ያስፈራቸዋል።

እነዚህ የጥላቻ ንግግሮች በርካታ ሺህ ሕዝብ እየገዛው መሆኑ ደግሞ ይበልጥ ስጋት ውስጥ እንደሚከታቸው ይናገራሉ። ይህ በፖለቲካውም በሃይማኖቱም ዘርፍ ሚዛናዊ አመለካከት ያላቸው ሰዎች የሚደመጡበት እንዲሆን ምኞት አለኝ ይላሉ።

''እኔ የክልሉ ተወላጅ ነኝ። አማራ ክልል በርካታ መስጊዶች ተቃጥለዋል፤ ከሞጣ ጀምሮ። ነገር ግን እስካሁን ለፍርድ የቀረበ ሰው የለም። ጥፋተኞች ፍርድ ማግኘት አለባቸው እንዲሁም ንጹሃንን መወንጀል አያዋጣም'' ሲሉ ኡስታዝ በድሩ ተናግረዋል።

የመቀለ ከተማ ነዋሪው ሃሰን በበኩሉ ሰዎች በረሃብ እየሞቱ መሆኑን ብሎም በእሱ ዕይታ ዘገምተኛ በሆኑት የዲፕሎማሲ እና ሰላምን የማምጣት ስራዎች መጓተት የሚሞተው የሰው ብዛት ያሳስበዋል።

"መጪው ረመዳን ትግራይ ክልል የተከበበችበት ከበባ ተሰብሮና ሳናልቅ የምንቆይበት እንዲሁም ነጻ ትግራይ ላይ የምናከብረው ይሆናል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ። እንደዚህ ሆነን መቀጠል አንችልም'' ሲልም ለቢቢሲ ተናግሯል።

ፖለቲከኞች ልዩነታቸውን በጠረጴዛ ዙሪያ እንዲፈቱ ያሳሰቡት ኡስታዙ "ተነጋግሮ አለመግባባት እና ጦርነት ደረጃ ላይ መድረስ ሽንፈት ነው'' ሲሉም ያስረዳሉ።

በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ያለውን ጦርነት መሪዎች አስቁመው ለሕዝቡ ሰላም እንዲያመጡ ይማጸናሉ።

"ያለቀው የሕዝብ ልጅ ነው። ከምንም በላይ ሰላም ሲኖር ነው ሌላው ነገር የሚኖረው። የእውነት የሆነ ሕዝብን እና ሃገርን ያስቀደመ ድርድር አድርገው ለተጎዳው ሕዝባችን ሰላም ያምጡ" ሲሉም አክዋል።

የጎዴው ነዋሪ አቶ መሐመድ አደን መጪውን ዓመት አስመልክተው ብሩሕ ተስፋ አላቸው።

"ከአላህ መቼም ጥሩ ነገር ነው የምንጠብቀው። የዘንድሮው ብቻ እንዳይደገምብን ነው የምንለምነው። ዋናው ልመናችን ሰላም እና ዝናብ ነበር። ዋናው ዱአችን ይሄው ነው" ሲሉም መጪው የረመዳን ወቅት የተሻለ እንደሚሆን ያምናሉ።