በጎንደር የኢድ ሶላት በአደባባይ ሳይከናወን መቅረቱን ነዋሪዎች ተናገሩ

ከሳምንት በፊት ሃይማኖታዊ ይዘት ያለው ግጭት ባስተናገደችው ጎንደር ከተማ ሕዝበ ሙስሊሙ ለኢድ ሶላት አደባባይ ሳይወጣ መቅረቱን ነዋሪዎች ተናገሩ።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች ከዚህ ቀደም የኢድ ሶላት ሥነ ሥርዓትን ያስተናግድ የነበረው ፋሲለደስ ስታዲየም ጭር ብሎ ውሏል ብለዋል።

የጎንደር ከተማ ነዋሪ የሆኑ የእምነቱ ተከታዮች እንደሚሉት ወደ ስታዲየም ሄዶ በጀመዓ [በጋራ] መስገድ የቀረው የደኅንነት ስጋቶች ስላሉ ነው ይላሉ።

ይህ የተሰማው ትናንት የጎንደር ከተማ ኡለማ ምክር ቤት ሕዝበ ሙስሊሙ በየመኖሪያ ቤቱ በዓሉን እንዲያሳልፍ ጥሪውን ካስተላለፈ በኋላ ነው።

ምክር ቤቱ ትናንት ሚያዚያ 23/2014 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ ላይ "መንግሥት ተገቢውን ኃላፊነት ለመወጣት በማይችልበት ሁኔታ ውስጥ እራስን ከጉዳት መታደግ" በማስፈለጉ የኢድ አልፈጥር በዓልን ምዕምናን በየቤታቸው እንዲያሳልፉት ውሳኔ አስተላልፏል።

ምክር ቤቱ በመግለጫው በጎንደር ከተማ ሚያዚያ 18 ባጋጠመው ግጭት ሕይወታቸው ላለፉት ፍትሕ እንዲሰጥ እና ንብረታቸው ለወደመ ተገቢው ካሳ እንዲከፈል ጨምሮ ጠይቋል።

"ምንም እንኳን መንግሥት እንደከዚህ ቀደሙ የኢድ ሶላት ሥነ ሥርዓት በስታዲየም እንዲከበር ቢጥርም፤ ሕዝበ ሙስሊሙ በቤቱ ነው ያሳለፈው" ሲሉ ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ የጎንደር ከተማ ነዋሪ ለቢቢሲ ገልጸዋል።

የእምነቱ ተከታዮች በጋራ ሆነው በአደባባይ መስገድ ባይችሉም በየአካባቢው ባሉ መስጅዶች የሰገዱ ሰዎች መኖራቸውን ቢቢሲ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች ተናግረዋል።

የሁለት ልጆች አባትና በጎንደር የቀበሌ 18 ነዋሪ የሆኑት የእምነቱ ተከታይ ደግሞ ባለፈው ሳምንት ማክሰኞ የተፈጠረውን ግጭትና ጥቃት ተከትሎ በግጭቱ እጃቸው ያለበት ተጠርጣሪዎችን የመያዙ ሥራ ፍትሃዊ አይደለም ይላሉ።

"ገለልተኛ ሰው አጣርቶ ድርጊቱን የፈፀሙ ሰዎች ለሕግ እስካልቀረቡ ድረስ አሁንም ለሞት አንዳረግም ብለን ነው ከቤት አንወጣም ያልነው" የሚሉት ነዋሪው፣ ሕዝበ ሙስሊሙ አደባባይ ወጥቶ በጋራ ያልሰገደው ጥያቄዎች ስላልተመለሱ ነው ብለዋል።

የፌደራል መንግሥትና የአማራ ክልል መስተዳደር ግጭቱን ተከትሎ እየተወስዱ ስላሉ እርምጃዎች እንዳሳወቁት ከተከሰተው ችግር ጋር በተያያዘ ከ300 በላይ ተጠርጣሪዎች በፀጥታ ኃይሎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን መግለጻቸው ይታወሳል።

ሌላኛው ለደኅንነቱ ሲል ስሙ እንዲጠቀስ ያልፈለገ ነዋሪ በከተማዋ የሚገኙ መስጊዶች የሚያሰሙትን 'አዛን' [የሶላት ጥሪ] ካቆሙ አራት ቀን እንዳለፋቸው ይናገራል።

"ዛሬ ጎንደር ምንም የለም። ብዙ እንቅስቃሴም የለም፤ ኢድ ኢድ አይመስልም" ብሏል ነዋሪው።

ይህ በእንዲህ እንዳላ ዛሬ ሚያዝያ 24/2014 ዓ.ም. በአዲስ አበባ የኢድ ሶላት ላይ በተከሰተ ረብሻ በንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን ፖሊስ አስታውቋል።

የአዲስ አበባ ፖሊስ በረብሻው ምክንያት በሰው ላይ የደረሰ ጉዳት ስለመኖሩ ያለው ነገር የለም።

በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በቀጥታ የተላለፉ ተንቀሳቃሽ ምስሎች ፖሊስ ድንጋይ ሲወረውሩ ወደነበሩ ሰዎች አስለቃሽ ጭስ ሲተኩስ አሳይተዋል።

በቀጥታ የተላለፉት ተንቀሳቃሽ ምስሎች ወደ ፀጥታ ኃይሎች እና ሕንጻዎች ድንጋይ ሲወረውሩ የነበሩ ሰዎችን ለማስቆም ሲከላከሉ የነበሩ ሰዎችንም አሳይተዋል።

ባለፈው ሳምንት መጀመሪያ ላይ በጎንደር ከተማ ሃይማኖታዊ ይዘት ያለው ግጭት ተቀስቅሶ ከ20 ያላነሱ ሰዎች መገደላቸውን የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት አስታውቆ ነበር።

መንግሥት ከዚህ ግጭት በኋላ በሁከቱ እጃቸው አለበት ያላቸውን ከ300 በላይ ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር ማዋሉን አስታውቆ ነበር።

የፌደራል የደኅንነትና የጸጥታ የጋራ ግብረ ኃይል ሐሙስ ሚያዚያ 20/2014 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች በሃይማኖት ሽፋን ሁከትና ብጥብጥ ለመፍጠር በሚንቀሳቀሱ አካላት ላይ እርምጃ እየተወሰደ ነው ብሎ ነበር።

በተመሳሳይ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ይልቃል ከፋለ (ዶ/ር) "ክልሉን የትርምስ ቀጣና ለማድረግ የሽብር ድርጊት በሚፈጠሩ አካላት ላይ የማያዳግም እርምጃ እንወስዳለን" ብለው ነበር።

ምንም እንኳ የክልሉ መንግሥትም ሆነ የፌደራል መንግሥት ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ሥር ከማዋል ባሻገር መሰል ድርጊቶችን እንደማይታገሱ ቢገልጹም፤ ከጎንደሩ ክስተት በኋላ በሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች በሚገኙ የእምነት ተቋማት ላይ ውድመት ደርሶ ነበር።

የአማራ ክልል የእስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ሚያዝያ 20፣ 2014 ዓ.ም. በደባርቅ ከተማ ሁለት መስጊዶች እንደተቃጠሉ የገለጸ ሲሆን የሀዲያና ስልጤ አገረ ስብከት ጽሕፈት ቤት ደግሞ በስልጤ ዞን፣ ወራቤ ከተማ በተመሳሳይ ቀን ሚያዝያ 20 ሁለት ቤተ ክርስቲያኖች ላይ ውድመት እንደደረሰ ባወጣው መግለጫ አስታውቆ ነበር።