ከከፋው የአሲድ ጥቃት በኋላም ስጋት ውስጥ ያለችው ሰላማዊት

በአማራ ክልል በሁለት እጁ እነሴ ወረዳ በቀራኒዮ ከተማ ይኼነው ፈንታ በተባለ ግለሰብ የአሲድ ጥቃት የደረሰባት ሰላማዊት ጊዜው፤ አሁንም ከጥቃት አድራሹ ለእሷ እና ቤተሰቧ ማስፈራሪያ እንደሚደርስ ትናገራለች።

በተፈጸመው ወንጀል ጥፋተኛ የተባለው ግለሰቡ የተፈረደበት የ14 ዓመት ቅጣት እጅግ ያነሰ መሆኑን እና ከእስር ቤት ውስጥ ሆኖ እየደወለ ዛቻ ማድረሱ ከእስር ወጥቶ ሌላ ጉዳይ ያደርስብኝ ይሆን ወይ በሚል ስጋት ውስጥ ትገኛለች፤ ሰላማዊት።

ሰላማዊት በተደፋባት አሲድ ሁለቱም ጆሮዎቿ የተቃጠሉ ሲሆን የፊቷን ትከሻዎቿ፣ አንገቷ፣ ጀርባዋ እና አንድ ጡቷ በአሲድ ቃጠሎው ተጎድተዋል።

ከፍተኛ ጉዳት የደረሰበት የቆዳዋን ክፍል ለማከም የፕላስቲክ ቀዶ ጥገና ህክምና እንደተደረገላትም ትናገራለች።

ጥቃት አድራሹ ይኼነው ፈንታ ሰላማዊትን "አፍቅሬሻለሁ'' በሚል ሰበብ ለአምስት አመታት ሲከታተላት ቆይቷል። እንደእርሷ ገለጻ መጀመሪያ ክትትሉን የጀመረው ገበያ ውስጥ ነው።

ጥቃት ሲፈጽምባት ይህ የመጀመሪያው አይደለም

ከአንድ አመት በፊት ወደ ቤተ ክርስቲያን ስትሄድ ጠብቆ አብራት ከነበረች ጓደኛዋ ጋር እንደደበደባት እና ድብደባው እስከ ሕክምና ያደረሳትም እንደነበር ታስታውሳለች።

ነገር ግን በወቅቱ ለሞጣ ከተማ ፖሊስ የደረሰባትን ጉዳት አስመልክቶ አቤት ያለችው ሰላማዊት ከፖሊስ ተጨባጭ ምላሽ ሳታገኝ ጥቃት አድራሹንም የሚያርም ምንም እርምጃ ሳይወሰድ ቀረ።

በማስፈራሪያ እና በዱላ ያልተገታው ግለሰብ ታሕሳስ 18፣2014 የምትሰራበት ፋርማሲ ድረስ ሄዶ በጆግ የያዘውን ሰልፈሪክ አሲድ በመድፋት ቆዳዋን ለከፋ ቃጠሎ እና ስነ-ልቦናዋን ለከባድ ስብራት ዳረገ።

"ያው ማንነቴን ለማጥፋት ነው የፈለገው'' ስትል ሰላማዊት ትናገራለች።

በድብደባዋ ግዜ ያልደረሰላት ፖሊስ፤ ከአሲድ ጥቃቱ ከተረፈች በኋላም ግለሰቡን ለመያዝ እንዳልፈለገ ሰላም እና ወንድሟ አንተነህ ሁነኛው በተደጋጋሚ ይናገራሉ።

"ጥቃቱን አድርሶ እዛው ወረዳ ውስጥ እያለ ፖሊሶቹ ሊይዙት ፈቃደኛ አልነበሩም። ከአንድ ወር በኋላ ሌሎች ሰዎች ናቸው ይዘው ለፖሊስ ያስረከቡት። አሲዱን ከደፋብኝ በኋላም በሕይወት መትረፌ ስለቆጨው ቤተሰቦቼ ጋር እየደወለ ያስፈራራ ነበር'' በማለት ሰላማዊት ታስረዳለች።

የ 24 ዓመቷ ወጣት በፋርማሲ ዲፕሎማዋን ይዛ በቀራኒዮ ከተማ በሚገኝ አንድ የግል ፋርማሲ ውስጥ ትሰራ ነበር።

"ፋርማሲው በር ላይ ቁጭ ብዬ በጆግ የሆነ ነገር ይዞ መጣ። እኔ ይህ ይሆናል ብዬ ስላላሰብኩ ቁጭ ብዬ ጠበቅሁት። ከዛ አምጥቶ ደፋብኝ '' ስትል ለቢቢሲ ተናግራለች።

ከደረሰባት ጉዳት ያላገገመችው ሰላማዊት፤ "አልፈልግም'' በሚል ቃል ብቻ ወደኖረችበት ቀራኒዮ ከተማ ለመመለስ እንደማትፈልግ ትገልጸለች። አሁን ኑሮዋን ባህር ዳር አድርጋ አዲስ አበባ እየተመላለሰች ሕክምናዋን ታደርጋለች።

የሕክምና ወጪዋን ቤተሰቦቿ ሸፍነዋል።

የሰላማዊት ወንድም የሆነው አቶ አንተነህ መላው ቤተሰቡ እስካሁን ድረስ ከ1.2 ሚሊዮን ብር በላይ ለህክምና ማውጣቱን ይናገራል።

"የቅርብም የሩቅም ቤተሰብ ያለውን ከብት በሙሉ ሸጦ ለህክምና አውሏል'' ይላል።

ከዚህ በተጨማሪም ጥቃት አድራሹ ግለሰብ ከእስር ቤት ውስጥ በመሆን ስልክ በመደወለ ቤተሰቡን እያስፈራራ እንደሚገኝም ያክላል።

"አንድ ሞጣ ያለ አጎቷ አለ። እሱ ላይ 'አንተ ነህ እንዳላገባት ያደረከው' በማለት ከመታሰሩ በፊትም ይዝትበት ነበር። እንደውም በእሱ ቤት አቅራቢያም ታይቶ ነበር። አሁንም ጥቃት ሊሰነዝር እንደሚችል ስጋት አለን'' ሲል አንተነህ ለቢቢሲ ተናሯል።

ጥፋተኛውን ግለሰብ የሰላማዊት ቤተሰብ ባደረገው ጥረት ተይዞ ለፖሊስ ተላልፎ እንደተሰጠ አንተነህ ተናግሯል።

በጉዳዩ ላይ የወረዳው ፖሊስ ጽሕፈት ቤት የወንጀል ምርመራ ክፍል ሃላፊ ኤንስፔክተር ብርሃኑ አድማሱ ለምን ተጠርጣሪውን በቁጥጥር ስር ለማዋል ፖሊስ ለምን እንደዘገየ ጠይቀናል።

"በነገራችን ላይ ለረጅም ግዜ አብረው እንደ ነበሩ ነው የሚታወቀው። እኛም ድርጊቱ ከተፈጸመ በኋላ ነው የሰማነው። ከዛ 'ወይ ለይተሽ ወደዛ በይ' ሲላት 'አልፈልግህም' ስትለው ነው ይሄ ድርጊት የተፈጸመው'' ሲሉ ሃላፊው ይጀምራሉ።

ተጠቂዋ እና ቤተሰቦቿ ከሚሉት ይልቅ የበዳዩን ትርክት ይዘው ድርጊቱን ለማስተባበል መሞከር በሕግ ከተሰጣቸው ሃላፊነት አንጻር አግባብ ነው ወይ ተብሎ ከቢቢሲ ጥያቄ የቀረበላቸው የፖሊስ ሃላፊው የሚከተለውን ምላሽ ሰጥተዋል።

"ይሄ እጅግ አሰቃቂ ተግባር አስቀያሚ፤ ብሎም ከግድያ በላይ ነው። እነሱ እንደሚሉት ፖሊስ ጽህፈት ቤት አልመጡም። ግለሰቡ ከተማ ውስጥ ቀንም ለሊትም ይዘዋወር ነበር። በእጃችን እስካልገባ ድረስ ግን የእኛ ቸልተኝነት ነው ሊባል አይችልም። ግን ደግሞ በመልክ አናውቀውም ነበር። እነሱ እንደሚሉት ሳይሆን ከጸጥታ ቢሮ ጋር ተባብረን ነው የያዝነው'' ሲሉ ኢንስፔክተር ብርሃኑ ተናግረዋል።

''የ 14 አመት ፍርድ በቂ አይደለም''

የሰላማዊት ጉዳይን በመከታተል ላይ የሚገኘው የኢትዮጵያ የሕግ ባለሞያ ሴቶች ማሕበር የአማራ ክልል ቅርንጫፍ አስተባባሪ የሆኑት ወ/ሮ ሙሉጎጃም ደምስ እንደሚሉት ጉዳዩ አሳሳቢ ነው።

አቃቤ ሕግ የአሲድ ጥቃትን "ከባድ አካል ጉዳት'' በሚል ክስ መመስረቱ አግባብ እንዳልሆነ፤ ከደረሰውም ጥቃት ጋር የማይመጣጠን ቅጣት እንዲጣል ምክንያት መሆኑን ባለሞያዋ ለቢቢሲ አስረድተዋል።

የአሲድ ጥቃት ነፍስ ሊያጠፋ የሚችል በመሆኑ የነፍስ ማጥፋት ሙከራ ተብሎ መወሰድ እንዳለበትም ይናገራሉ።

"አንድ ግዜ ፍርድ ከተሰጠ ክስ ማሻሻል አይቻልም። ነገር ግን ለወደፊቱ እንዲህ አይነት ጥቃቶች በግድያ ሙከራ እንዲታዩ አቃቤ ሕግ ሰርኩላር አንዲያወጣ በዚህ ሳምንት ደብዳቤ ጽፈን አስገብተናል'' ሲሉ ሙሉ ጎጃም ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ነገር ግን ሰላማዊት ለምታቀርበው የፍትሃ ብሔር ጥያቄ የሕግ ባለሞያ ሴቶች ማሕበር ድጋፍ እያደረገላት እንደሆነ እና ግለሰቡ ያቀረበውን የይግባኝ ጥያቄን የማሕበሩ በጎ ፈቃደኞች እየተከታሉ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

"በሰላማዊት ጉዳይ ላይ ፖሊስም ሆነ አቃቤ ህግ ትኩረት አልተሰጠም ብለን እናምናለን'' ሲሉ የሕግ ባለሞያዋ ያክላሉ።

መፍትሔው ምንድነው ?

በቅርብ ግዜ የተከሰቱ መሰል ጾታዊ ጥቃቶችን ብንመለከት እንኳን በርግጥም አጥቂዎች በግዜ ሂት እየጨመረ የሚሄዱ ጥቃቶችን ያደርሳሉ፤ ተጠቂዎች አንድም ምን ማድረግ እንዳለባቸው ባለማወቅ ወይም ሰሚ አካል ባለማግኘት ዝምታን ይመርጣሉ።

ታኅሣሥ 30/2014 ዓ.ም በፍቅር ጓደኛዋ በእሳት ተቃጥላ ህይወቷ ያለፈው ሰብለ ንጉሴ ጥቃት አድራሹ ቀደም ብሎ ድብደባ ይፈጸምባት እንደነበር ወንድሟ ያቆብ ንጉሴ ከህልፈቷ በኋላ መረዳቱን ለቢቢሲ ገልጾ ነበር።

በርካታ አሰቃቂ የጾታዊ ጥቃቶች ከተፈጸሙ በኋላ መሰል ታሪኮችን መስማት የተለመደ ነው።

በዚህ የምትስማማው የህግ ባለሞያዋ እና በስርአተ ጾታ እኩልነት ላይ አተኩራ የምትሰራው ህሊና ብርሃኑ "እነዚህ ጥቃቶች አሲድ ከመድፋት ወይም ከመግደል አይጀምሩም'' ትላለች።

ማህበረሰቡ በይፋ ሊኮንናቸው የማይፈልጋቸው ነገር ግን በፍጹም ተቀባይነት ሊሰጣቸው የማይገባ የሴቶች ሰላም እና ደህንነት ከሚነኩ ተግባራት እንዲህ ወዳሉ አሰቃቂ ፍጻሜዎች እንደሚያመሩም ትናገራለች።

ሴቶች እንደማንኛውም ዜጋ በሰላምም ሆነ በጦርነት ግዜ በሰላም ወጥተው እንዲገቡ ለማያስችል አገር ግብር እንዲከፍሉ ለምን ይጠያቃሉ ስትልም ትጠይቃለች።

"ይህንን ካላደረገ ወንድን ብቻ ለማገልገል የቆሙ ተቋማት ነው የሚሆኑት" የምትለው ህሊና ይህ ደግሞ ከግማሽ በላይ የሆነውን የኢትዮጵያ ሕዝብን የማያገለግል ተቋም የኢትዮጵያ ሊባል አይችልም'' ስትል ህሊና ትናገራለች።

እንዲሁም እንዲህ ያሉ ጉዳዮችን ነጥለን መመልከት ማቆም ይገባል ትላለች።

"የተማረች፣ ወጣት፣ ሃይማኖተኛ ወይም ቆንጆ እያልን ሃዘኔታችንን የግል ማድረግ የለብንም። ምንም ዜጋ የሆነች ሴት፣ ብናውቃትም ባናውቃትም፣ ወይም የምናውቃት ሴት ስለሆነች ሳይሆን ማንኛዋም ሴት ላይ መፈጸሙ ትክክል አይደለም ማለት አለብን'' ስትል ትወቅሳለች።

የማሕበረሰቡ እይታውን በማሻሻል ብሎም እንደሚዲያ እና ፖሊስ ያሉ የሕዝብ ተቋማት ሴቶችን እንደዜጋ ማገልገል ካልቻሉ ስርዓቱ ከ51 በመቶ በላይ የሆነውን ሕብረተሰብ ክፍል ማገልገል እንዳልቻለ ማሳያ ይሆናል ስትልም ሕሊና ታሳስባለች።