ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
100 ጊዜ የሚታጠብ ሞዴስ የሠራችው ሚካል ማሞ
ሚካል ማሞ የአደይ መሥራች ናት። አደይ 100 ጊዜ የሚታጠብ የወር አበባ ንጽሕና መጠበቂያ ወይም ሞዴስ ያመርታል።
"በአንዲት ሴት ሕይወት የሞዴስ መኖርና አለመኖር፣ ልዩነቱ የብርሃን እና የጨለማ ያህል ነው" ትላለች ሚካል።
ይህን የምትለው ያለ ምክንያት አይደለም።
ጥናቶች እንደሚያሳዮት፣ በኢትዮጵያ 75 በመቶ ገደማ ሴቶች የወር አበባ ማየት ከጀመሩ በኋላ የንጽሕና መጠበቂያ አያገኙም።
በቁጥር ሲሰላ ከ35 ሚሊዮን ሴቶች፣ 22 ሚሊዮኑ ሞዴስ አያገኙም ወይም አይደርሳቸውም።
ሞዴስ ቅንጦት አይደለም። በአገራችን ግን ይህንን መሠረታዊ አቅርቦት በማጣት ሴቶች ይፈተናሉ።
ሚካል ሥራዋ ሞዴስ ማምረት ብቻ አይደለም። የወር አበባ ድህነትን (period poverty) ለመቅረፍ ትታገላለች።
ሞዴስ ከቀረጥ ነጻ እንዲሆን፣ በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲቀርብ፣ በመላው አገሪቱ ተደራሽ እንዲደረግም ንቅናቄ ከሚያደርጉ አንዷ ናት።
ስኮትላንድ የወር አበባ ንጽሕና መጠበቂያ ምርቶችን ለዜጎቿ በነጻ በማቅረብ የመጀመሪያዋ መሆኗ ከተገለጸ ሰነባብቷል።
የኒው ዚላንድ ትምህርት ቤቶች ደግሞ የወር አበባ ንጽሕና መጠበቂያ በነጻ ያቀርባሉ።
"የወር አበባቸው ሲመጣ አመድ ላይ ይቀመጣሉ"
ተፈጥሯዊው የወር አበባ እንደ 'እርግማን' እንደ 'አስጸያፊ ክስተት' የሚቆጠርበት ማኅበረሰብ ውስጥ ነው የምንኖረው።
አንዲት ተማሪ ድንገት የደንብ ልብሷ ደም ከነካ የክፍሏ ተማሪዎች ያሳቅቋታል፣ ያሸማቅቋታል። ዳግመኛ ወደ ትምህርት ቤት ላትመለስም ትችላለች።
ሴቶች የወር አበባቸው ሲመጣ ከቤት ወይም ከቤተ እምነትም እንዲርቁ ሲደረግም እናያለን።
'ከተማ ቀመስ' የሚባል አካባቢ የምሠራ ሴት እንኳን በቀላሉና በተመጣጠኝ ዋጋ ሞዴስ ለማግኘት ትቸገራለች።
ሚካል ያካፈለችን ታሪኮች ደግሞ ከላይ ከተጠቀሱትም በላይ ይከፋሉ።
"ለመስማት የሚከብዱ ብዙ ታሪኮች አሉ. . . ሴቶች የወር አበባቸው ሲመጣ አመድ ላይ ይቀመጣሉ። ኩበት ይጠቀማሉ። ጉድጓድ ላይ ይቀመጣሉ። ላስቲክ አንጥፈው ቤት ይቀመጣሉ።
ደሙ ልብሳቸውን እንዳይነካባቸው የብርድ ልብስ ቅዳጅ ይጠቀማሉ። የአንሶላ ቅዳጅ ወይም ሌላም ሰውነት ጎጂ ጨርቅ የሚጠቀሙ ሴቶች አሉ። ፈሳሽ መምጠጡን ብቻ አይተው ፖሊስተር ወይም ድብልቅ ጨርቅ የሚጠቀሙም አሉ። እነዚህ ለአካል አይስማሙም. . ."
በአማካይ ከ12 ዓመት ዕድሜ አንስቶ፣ በአማካይ በየ28 ቀኑ በዚህ ማለፍ ለምን? ያውም በተፈጥሯዊው የወር አበባ ምክንያት።
ችግሩን ከፖሊሲ ክፍተት፣ ከድህነት እና ከተዛባ ምልከታ አንጻር መመልከት ይቻላል።
ወደ አገር ቤት የሚገቡ ሞዴሶች እንደ ቅንጦት እቃ መቀረጣቸው የሞዴስ ዋጋ እንዲንር ምክንያት ሆኗል።
በእርግጥ ከዓመታት ጥያቄ በኋላ መንግሥት ከአንድ ዓመት በፊት የሞዴስ ቀረጥ ላይ ማሻሻያ እንዳደረገ አስታውቋል።
የወር አበባ ንጽሕና መጠበቂያ አገር ወስጥ የሚያመርቱ ፋብሪካዎች ከውጭ የሚያስገቡት ጥሬ እቃ ከቀረጥ ነጻ እንዲሆን፣ ሞዴስ ከውጭ ሲገባ ደግሞ ቀድሞ ከነበረው 30% የቀረጥ ምጣኔ ወደ 10% ዝቅ እንዲል ተወስኗል።
"አገር ውስጥ ሞዴስ የሚያመርቱ፣ ጥሬ እቃ ከቀረጥ ነጻ እንዲያስገቡና 10% ብቻ ግብር እንዲከፍሉ ተወስኗል ተብሎ ነበር። ነገር ግን [ማሻሻያው የሚተገበርበት] ቀን አልተወሰነም ዋጋም አልተተመነም" ትላለች ሚካል።
በአገሪቱ ባለው የዋጋ ግሽበት ሳቢያ ከ17 እስከ 20 ብር ይሸጥ የነበረው ጥቅል ሞዴስ እስከ 35 ብር እየተሸጠ ይገኛል።
35 ብር በወር፣ በዓመት ወደ 420 ብር ገደማ ይመጣል። የሚካል ጥያቄ ዋጋው የምን ያህል ሴቶችን ዐቅም ያማክላል? ነው።
ችግሩ ሞዴስ ባለማግኘት ብቻ አያቆምም። ማኅበረሰባዊ ማሸማቀቅም ይጨመርበታል።
ሚካል የአንዲትን ታዳጊ ታሪክ አትረሳውም።
አዲስ አበባ ውስጥ ነው። ሚካልና የሥራ ባልደረቦቿ ሞዴስ ለመለገስ ትምህርት ቤት አቀኑ።
አንዲት ታዳጊ "ታሪኬ ብዙዎችን ስለሚያስተምር ላካፍላችሁ" ብላ ወደ መድረክ ወጣች።
የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ናት። የወር አበባዋን ለመጀመሪያ ጊዜ ስታይ ለቤተሰቦቿ ነገረቻቸው።
ያገኘችው ምላሽ ግን ፍጹም ያልጠበቀቸው ነበር።
'ወሲብ ፈጽመሽ ነው!' ብለው ቤተሰቦቿ ተቆጧት።
ታዳጊዋ ታሪኳን ስትናገር እያለቀሰች ነበር።
ቤተሰብ ለልጆቹ ስለ ወር አበባ አይነግርም፣ አያዘጋጃቸውም። ትምህር ቤት ውስጥም ጤናማ የሆነ የወር አበባ ውይይት እምብዛም አይስተዋልም። ሞዴስም በቀላሉ አይገኝም።
የሚታጠብ ሞዴስ
ሚካል የኢንተርናሽናል ቢዝነስ ምሩቅ ናት። አደይ የሚታጠብ የንጽሕና መጠበቂያን የመሠረተችው ከ3 ዓመት በፊት ነበር።
"ፓድ ገዝቶ መጠቀምን እንደ ምንም ካልቆጠርነው ችግሩን አናውቀውም። እውነት ለመናገር እኔም እዚህ ሥራ ውስጥ ከገባሁ በኋላ እለት በእለት በማየው ነገር ነው ችግሩ ይሄን ያህል ጥልቅ ነው? ክፍተቱ ይሄን ያህል ነው? ያልኩት።"
ለገጣፎ የሕፃናት ልብስ ታመርት ነበር። በአካባቢዋ ያሉ ታዳጊዎች የወር አበባ ንጽሕና መጠበቂያ አጥተው ሲንገላቱ ስታይ የሥራ ዘርፏን ቀየረች።
"ችግሩ ተማሪዎቹ የንጽሕና መጠበቂያ ምን እንደሆነ አያውቁም በሚባልበት ደረጃ ነው" ስትል ታስታውሳለች።
ሴቶች በየወሩ ለሦስት ቀናት፣ ገፋ ሲልም እስከ ሰባት ቀናት በትምህርት ገበታቸው አይገኙም።
በድጋሚ ጥቅም ላይ የሚውል ሞዴስ (reusable sanitary pad) የሚያመርቱ ድርጅቶችን በመጎብኘት ጀመረች።
ከተማሪዎች እስከ ቀን ሠራተኞች አነጋገረች።
በድጋሚ ጥቅም ላይ የሚውሉ ሞዴሶች ለሰውነት ተስማሚ ሆነው እንደማይሠሩ፣ በብዛት እንደማይመረቱም ተገነዘበች።
አያት ቅድመ አያቶቻችን የነጠላ ወይ የጋቢ ቅዳጅ ይጠቀሙ ነበር።
"እንዲያውም እነሱ ለተፈጥሮ ቅርብ ስለነበሩ ብዙም ሰውነት የሚጎዳ ነገር አይጠቀሙም" የምትለው ሚካል፣ ለደረስንበት ዘመን የሚመጥን ምቹ ሞዴስ ለማምረት ተነሳች።
ለጤና ተስማሚ የጨርቅ ናሙናዎች አጥንታ አደይ ተጠነሰሰ።
አደይ፣ የሴቶች ኩራት
በድጋሚ ጥቅም ላይ የሚውል ሞዴስ ሲሠራ ለሰውነት ተስማሚነቱ፣ የሚይዘው የፈሳሽ መጠንና ዕድሜው ታሳቢ ይደረጋል።
በኢትዮጵያ ለሚታጠብ የወር አበባ ንጽሕና መጠበቂያ የወጣ የጥራት ደረጃ ወይም ልኬት የለም።
ሚካል ከጤና ባለሙያዎችና የሥነ ተዋልዶ ጤና አስተማሪዎች ጋር በመመካከር አደይን ሙሉ በሙሉ ከጥጥ ትሠራለች።
ሞዴሱ ታጥቦ ቶሎ በፀሐይ ብርሃን መድረቅ ከሚችል ግብአት ይሠራል። ምንም ዓይነት ማቅለሚያ ወይም ባዕድ ነገር አይገባበትም።
ሞዴስ በተገቢው ግብዓት ካልተሠራ ለማሕፀን ኢንፌክሽን፣ ለፈንገስና ለባክቴሪያ ያጋልጣል።
የአደይ ሽፋን የተለያየ ቀለም ያለው የጥጥ ጨርቅ ሲሆን ውስጡም ጥጥ ነው።
ብዙ የሚባለው የወር አበባ ፈሳሽ 10 ሚሊሜትር (ሁለት ወይም ሦስት የሾርባ ማንኪያ) ስለሆነ አደይምበዚህ ልኬት ተሠርቷል።
ከሞዴስ ውድነት እንዲሁም ውስን ተደራሽነት ጎን ለጎን መጸዳጃ ቤት ማጣት ሌላው ራስ ምታት ነው።
ሴቶች መጸዳጃ ቤት አያገኙም ወይም ደግሞ መጸዳጃ ቤት ለማግኘት ረዥም ርቀት መጓዝ ይጠበቅባቸዋል።
ይህንን ከግምት በማስገባት አደይ ፈሳሽ መምጠጥ እንዲችል ነው የተሠራው። ከ6 እስከ 8 ሰዓት መቆየት እንደሚችል ሚካል ትናገራለች።
ታጥበው በድጋሚ ጥቅም ላይ መዋል የሚችሉ ሞዴሶች በአማካይ ከ18 ወራት እስከ 3 ዓመት የሚቆዩ ናቸው።
ከ82 በላይ ሴት ሠራተኞች ያሉት አደይ፣ 100 ጊዜ የሚታጠብ ሞዴስ ነው።
አንዲት ሴት በወር ውስጥ ከሦስት እስከ ሰባት ቀናት የምትጠቀመው ሞዴስ እየታጠበ እስከ ሁለት ዓመታት ያገለግላል ትላለች ሚካል።
ትንሹ ጥቅል አራት ሞዴስ ይይዛል። 140 ብር ይሸጣል።
"አንድ ጥቅል እስከ 2 ዓመታት ጥቅም ላይ ስለሚውል የምንሸጥበት ዋጋ ተመጣጣኝ ነው። አንዴ ብቻ አገልግሎት የሚሰጥ ሞዴስ ለመግዛት እስከ 500 ብር ያስፈልጋል" ትላለች ሚካል።
አንዱ የወር አበባ ንጽሕና መጠበቂያ በአንድ የወር አበባ ዑደት ሁለት ጊዜ ጥቅም ላይ ሊውል ይችላል።
በአደይ ጥቅል ውስጥ ሦስት የቀን እና አንድ ተለቅ ያለ የሌሊት ሞዴስ ተካቷል።
ሌሊት ረዥም ሰዓት በእንቅልፍ ስለሚያልፍ ተለቅ ያለው ሞዴስ እስከ 12 ሰዓት ሊያቆይ ይችላል።
ከሞዴሱ ጋር ፈሳሽ የማያሳልፍ አነስተኛ ጥቁር ቦርሳ አለ። ሴቶች በሚመቻቸው ቦታ ሞዴስ ቀይረው በቦርሳው እንዲያስቀምጡት ታስቦ ነው የተዘጋጀው።
"ፈሳሽ የማያሳልፈው ጥቁሩ ቦርሳ ተማሪዎችም ይሁን ሠራተኞች ሳይሳቀቁ የተጠቀሙበትን ሞዴስ ቀይረው ወደ ትምህርት ወይም ሥራቸው እንዲመለሱ ለማስቻል ያለመ ነው" ትላለች ሚካል።
አደይ ለየተጠቃሚዎቹ ሴቶች ዕድሜ እንዲሆን በአነስተኛ፣ መካከለኛና ትልቅ መጠን ነው የሚዘጋጀው።
የወለዱ እናቶች፣ በእድሜ የገፉ ሴቶችና የቀን ሠራተኞች ትልቁን ሞዴስ ይመርጣሉ። በዐሥራዎቹ ዕድሜ ክልል ያሉ ደግሞ አነስተኛውና መካከለኛውን።
አንድ ሞዴስ ለመሥራት 13 ዓይነት ግብዓት ይጠቀማሉ። 8 የውስጥ ርብራቦች (filler) እንዲሁም ከላይ እና ከታች ሁለት ክንፍ (wing) አለው። ከላይ በቁልፍ እና ክር ይታሰራል።
ቀረጥ ይወሰንልን፣ ዋጋ ይተመንልን
ሚካል፣ እንደ አይ ኬር ኢትዮጵያ እና ጀግኒት ኢትዮጵያ ካሉ የወር አበባ ድህነትን መቅረፍን ጨምሮ በሌሎችም የሥነ ጾታ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ጋር በቅርበት ትሠራለች።
እነዚህ ማኅበረሰብ አንቂ ድርጅቶች 'ቀረጥ ይወሰንልን፣ ዋጋ ይተመንልን' 'አበባ አየሽ ወይ ትምህርት ቤት ትሄጃለሽ ወይ?' በሚሉትና በሌሎችም ተመሳሳይ ንቅናቄዎች ይታወቃሉ።
ሚካል እንደምትለው፣ መንግሥት መቼ ነው የንጽሕና መጠበቂያን ከቀረጥ ነጻ የሚያደርገው? የሚለው ጥያቄ እስካሁን ምላሽ አላገኘም።
"የሞዴስ መሥሪያ ጥሬ እቃ ቀረጥ እንዲሁም አንድ ጊዜ ጥቅም ላይ የሚውል ሞዴስም ቀረጥ መነሳት አለበት።"
ታጥቦ በድጋሚ ጥቅም ላይ የሚውል የወር አበባ ንጽሕና መጠበቂያ አገር አቀፍ ልኬት እንዲወጣለትም ትጠይቃለች።
ለሰውነት ተስማሚ ከሆነ ግብዓት የሚሠራ፣ ምቹ የሆነ፣ ፈሳሽ የሚችል፣ ምንም የጎንዮሽ ጉዳት የሌለው እንዲሆን ነው ልኬት የሚያስፈልገው።
አደይ በአንድ ሳምንት ውስጥ ለ5 ሺህ ሴቶች የሚደርስ ሞዴስ እንደሚያመርት ሚካል ትናገራለች።
አብዛኛውን ግብዓት ከውጭ ማስመጣታቸው አንዱ የሥራው መሰናክል ነው። የኮንቴነር እጥረት በተደጋጋሚ ይገጥማቸዋል።
"ዋናው ችግራችን የቀረጥና ግብር ጉዳይ መፍትሄ አለማግኘቱ ነው። እኛ ሞዴስ ለተፈናቃዮችና ለተማሪዎች በማድረስ ማኅበራዊ ኃላፊነታችንን ለመወጣት እንሞክራለን። ከዐቅማችን በላይ ሲሆን እናስተባብራለን። አደይ በሴቶች የሚመራ፣ በሴቶች ተሠርቶ ለሴቶች የሚደርስ ነው። ከመንግሥት ግን ብዙም ድጋፍ እያገኘን አይደለም።"
መንግሥት የወር አበባ ድህነትን ለመቀነስ መሥራት እንዳለበት በአጽንኦት ትናገራለች። 'ሴቶችን እናብቃ' ሲባል የመጀመሪያው ነጥብ የወር አበባ ንጽሕና መጠበቂያ ማቅረብ እንደሆነም ታሰምርበታለች።
'አበባ አየሽ ወይ ትምህርት ቤት ትሄጃለሽ ወይ?'
የእነ ሚካል ዋነኛ ትኩረት ሴት ተማሪዎች ናቸው።
"መንግሥት ተማሪዎችን ምግብ ያበላል፣ ዩኒፎርም ያለብሳል። አልፎ አልፎም ጫማ መስጠት ጀምሯል። በዚህም ብዙ እናቶች እፎይታ አግኝተዋል። ታዲያ መቼ ነው የንጽሕና መጠበቂያም በነጻ የሚሰጠው? ወይም በተመጣጣኝ ዋጋ የሚቀርበው?"
ሚካል እንደምትለው፣ 'አበባ አየሽ ወይ ትምህርት ቤት ትሄጃለሽ ወይ?' የተባለው ንቅናቄ፣ በ10 ክልሎች ቢያንስ 50 ሺህ ሴት ተማሪዎችን ለመድረስ ያለመ ነበር።
የአገሪቱ አለመረጋጋት ቢያስተጓጉለውም ከያዝነው ዓመት ጥቅምት ጀምሮ 12 ሺህ ተማሪዎችን ደርሰዋል።
ከጦርነቱ በፊት መቀለ፣ ከዚያም በአፋር ክልል እንዲሁም በወሎ፣ በደብረ ብርሃን፣ በባሌ እና በአዲስ አበባ ከተሞች ሞዴስ አከፋፍለዋል። በአጣዬ፣ በደብረ ብርሃን እና በወልዲያ መጠለያ ጣቢያዎች ለሚገኙ ተፈናቃዮችም አድርሰዋል።
የሞዴስ መኖርና አለመኖር. . .ብርሃን እና ጨለማ
በሚካል አገላለጽ፣ ልዩነቱ የብርሃን አና የጨለማ ያህል ነው። ሞዴስ ሲኖር እና ሳይኖር።
ልብሳቸውን ደም ነክቶት ከትምህርት ቤት የቀሩ ሴቶች ሚካል ገጥመዋታል። የወር አበባቸው በመጣ ቁጥር ትምህርት ቤት የማይሄዱትንም ቤቱ ይቁጠራቸው።
ሚካል ብርታት የሚሰጣት ሴት ተማሪዎች ሞዴስ ሲሰጣቸው ፊታቸው ላይ የሚታየው እፎይታ ነው።
". . .ፊታቸው ላይ የሚታየው ደስታ፣ እረፍቱ፣ ለ2 ዓመት ሳይሳቀቁ ወደ ትምህርተ ገበታቸው ሲመለሱ ማየት ያበረታታናል። ተማሪዎቹ ሞዴስ ሲሰጣቸው እንባ ነው የሚቀድማቸው። አሁን በትምህርቴ እጎብዛለሁ፣የሚያቆመኝ ነገር የለም ይላሉ። ይህንን ማየት ሥራችን ለውጥ አለው እንድንል ያደርገናል።"
ለሚካል በስልክ መልዕክት የሚልኩላት፣ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጾች የውስጥ መስመር የሚጽፉላት በርካታ ናቸው።
"ደስታቸውን ለመግለጽ ከባድ ነው። አንዳንዶቹ ምርቃት ያስቀምጡልሻል። የሚሰጡን ምላሽ ችግሩ ምን ያህል ጥልቅ እንደሆነ ነው የሚያሳይሽ" ትላለች።
እነ ሚካል ሞዴስ ሲለግሱ፣ በጎ ፈቃደኛ የሆኑ የሕግ እና የሥነ ተዋልዶ ጤና ባለሙያዎች ትምህርት እንዲሰጡ መድረክ ይመቻችላቸዋል።
ሴቶቹ መጠየቅ የሚፈልጉትን ሁሉ በነጻነት እንዲጠይቁ ይደረጋል።
የሥርዓተ ጾታ መምህራን ወይም ነርሶች ለተማሪዎች በምን መንገድ እርዳታ መስጠት አለባቸው የሚለውም ይነሳል።
ተማሪዎችም ይሁን ተፈናቃዮች ሞዴስ ሲሰጣቸው የተረጂነት ስሜት አንዲፈጠርባቸው አይፈለግም።
የወር አበባ ድህነትን ለመቅረፍ የሚደረገው ንቅናቄ አካል የሆነችው ድምጻዊት ፀደንያ ገብረማርቆስ "ሞዴስ ለመስጠት በምንሄድበት ለሴቶቹ፣ የሷን የሚወዱትን ዘፈን ትዘፍንላቸዋለች፣ ታስቃቸዋለች. . . ሞዴስ በማጣት ራዕያቸው መጨንገፍ እንደሌለበትም እናስታውሳቸዋለን" ትላለች ሚካል።