ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በኔፓል የወር አበባ የሚያዩ ሴቶች ጽዩፍ ተደርገው ይታያሉ
በኔፓል ገጠራማ አካባቢዎች "የወር አበባ ጎጆ" የሚባል ነገር አለ። "የወር አበባ ጎጆ" ማለት ሴቶች ከወለዱ በኋላ ወይም ደግሞ የወር አበባ በሚያዩበት ሰዓት ከኅብረተሰቡ ተገለውና ራቅ ተደርገው የሚመቀመጡበት እልፍኝ ነው።
በቅርቡ የ21 ዓመቷ ወጣት ፓርባቲ ራዋት የወር አበባ ላይ ነሽ በሚል ራቅ ተደርጋ በዚህ "የወር አበባ ጎጆ" እንዲቆለፍባት ኾና ነበር። በዚያው ታፍና ሞታለች።
ከርሷ ሞት ጋር በተያያዘ አንድ የቤተሰብ አባል በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ውሏል።
ይህ ሴቶችን የማግለለ ተግባር በሕግ የተከለከለ ቢሆንም ፖሊስ ተጠርጣሪን ለመያዝ ሲሞክር ግን ይህ የመጀመርያ ነው።
በአገሬው ባሕል ሴቶች የወር አበባ ላይ ከሆኑ እንደቆሸሹ ተደርጎ ይታሰባል።
ሴቶችን ጽዩፍ አድርጎ የማየቱ ነገር በወር አበባ ጊዜ ብቻ አይደለም። ልጅ ከወለዱ በኋላም ለተወሰነ ጊዜ ተገለው ራቅ ባለች ጎጆ ይቆለፍባቸዋል።
ፖሊስ ያዝኩት ያለው የሟች ቤተሰብ ጥፋተኛ ሆኖ ከተገኘ የሚቀጣው 26 ዶላር ብቻ ነው።
ምዕተ ዓመት ባለፈው የሂንዱ ባሕል ሴቶች በወር አበባ ጊዜያቸው ከእንሰሳት ጋር ጋጣ ውስጥ እንዲያድሩ ይደረጋሉ። በወር አበባ ላይ ሳሉ የሚነኩት ነገርም እንደረከሰ ይታሰባል። ምግብንም ሆነ ወንድን እንዳይነኩ ጥብቅ መመሪያ አለ።
በዚህ ዘመንም ቢሆን በወር አበባ ጊዜ ራቅ ወዳለ ጎጆ ተወስደው እዚያው እንዲኖሩ ይደረጋል። የሚኖሩባቸው ጎጆዎች እጅግ ቅዝቃዜ ስለሚኖራቸው ሴቶቹ በወሊድ ጊዜ ለሞት ይዳረጋሉ። በቅርቡ በእባብ ተነድፋ የሞተች ሴትም እንዳለች ፖሊስ ገልጧል።
ኔፓል ይህን ኋላ ቀር አስተሳሰብና ድርጊት እንዲቆም ጥረት ማድረግ የጀመረችው እንደ ጎርጎሮሲያዊያኑ በ2005 ቢሆንም ወንጀል ሆኖ የተደነገገው ግን ከሁለት ዓመት በፊት ነው። ያም ሆኖ ይህ አጉል ባሕል ስር የሰደደ በመሆኑ ወንጀል መደረጉ እምብዛምም ለውጥ አላመጣም።
በዚህ ዓመት ብቻ ሦስት ሴቶች የወር አበባ ላይ ናችሁ ተብለው ራቅ ወዳሉ ጎጆዎች ተወስደው በመጣላቸው ሞተዋል። አንዲት ሴት በዚህ እጅግ ጠባብ በሆነ "የወር አበባ ጎጆ" ውስጥ ከሁለት ልጆቿ ጋር ለመታሰር በመገደዷ እርሷም ልጆቿም ታፍነው መሞታቸው ተዘግቧል።