በሕዳሴ ግድብ ላይ ያነጣጠሩ የሳይበር ጥቃቶች መክሸፋቸው ተገለጸ

የኢትዮጵያ የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ በታላቁ የሕዳሴ ግድብ እና አገሪቱ የፋይናንስ ተቋማት ላይ ያነጣጠሩ የመረጃ መረብ (ሳይበር) ጥቃቶችን አከሸፍኩ አለ።

ተቋሙ በአገራት የሚደገፉ የሳይበር ጥቃቶች ማክሸፍ መቻሉን የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ሹመቴ ግዛውን (ዶ/ር) ጠቅሰው መንግሥታዊ የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

የሕዳሴ ግድብን ግንባታ ለማስተጓጎል 'ብላክ ፒራሚድ ዋር' የሚባል በአገር ደረጃ የሚደገፍ ድርጅት የሳይበር ጥቃት መሰንዘሩ እና ይህ ሙከራ ጉዳት ሳይደርስ መክሸፉን ባለሥልጣኑ ተናግረዋል።

ዋና ዳይሬክተሩ የፋይናንስ ተቋማት የሚጠቀሙባቸውና እርስ በእርሳቸው የተሳሰሩ 37 ሺህ ኮምፒውተሮች ላይ ጥቃት በመፈጸም እንዲሁም የሕዳሴው ግድብ ግንባታን ለማስተጓጎል ተሞክሯል ስለማለታቸው መገናኛ ብዙኃኑ ዘግበዋል።

የሕዳሴው ግድብ ኃይል ማመንጨት ከጀመረ በኋላም የሳይበር ጥቃቶች ሊቀጥሉ ስለሚችሉ የሳይበር ደኅንነትን ተግባራዊ በማድረግ ከሕዳሴው ግድብ ግንባታና ቁጥጥር ተቋማት ጋር በቅርበት እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ በፋይናንስ ተቋማት ላይ ያነጣጠሩ በርካታ የሳይበር ጥቃቶች እንዲከሽፉ መደረጉን ሹመቴ ግዛው (ዶ/ር) ተናግረዋል።

የተቃጡት የሳይበር ጥቃቶች ዒላማቸውን ቢያሳኩ ኖሮ በፋይናንስ ተቋማት ላይ ብቻ ሳይሆን በአገር ደረጃ ከፍተኛ ችግር ያስከትሉ እንደነበርም ዋና ዳይሬክተሩ አመልክተዋል።

ሹመቴ ግዛው (ዶ/ር) ከመስከረም እስከ የካቲት ባሉት የ2014 የመጀመሪያ ስድስት ወራት ውስጥ ከ3 ሺህ 400 በላይ ከፍተኛ እና አደገኛ የሆኑ የሳይበር ጥቃት ሙከራዎች እንደተደረጉ ገልጸዋል።

የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ በመንግሥት ተቋማት ላይ የሳይበር ጥቃት ሙከራ መካሄዳቸውን ሲገልጽ ይህ የመጀመሪያው አይደለም።

ኤጀንሲው ጥር 14/2014 ዓ.ም. በስድስት ወራት ውስጥ ብቻ ከ2 ሺህ በላይ የሳይበር ጥቃቶች መሞከራቸውን አስታውቆ ነበር።