ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አንድ እግሯን በካንሰር ያጣችው ሯጭ የማራቶን ክብረ ወሰንን ሰበረች
ግራ እግሯን በካንሰር ካጣች በኋላ መሮጥ የጀመረችው ጃኪ ሃንት 104 ተከታታይ የማራቶን ውድድሮችን በ104 ቀናት በመሮጥ የጊነስ የአለም የተከታታይ ማራቶን ክብረ ወሰንን እንዳለፈች ተነግሯል።
የ46 አመቷ ጃኪ ሀንት ብሮርስማ ከአውሮፓውያኑ ጥር ወር አጋማሽ ጀምሮ በየቀኑ 42 ኪሎሜትር ርቀት ሮጣለች። ይህ በተለምዶ አምስት ሰዓት አካባቢ ይወስዳል።
ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ 104ኛ ተከታታይ የማራቶን ውድድሯን ያጠናቀቀችው ጃኪ፣ ይህ ስኬቷ በዓለም ድንቃ ድንቅ መዝገብ [ጊነስ ወርልድ] የክብረ ወሰን እንዲመዘገብላት ጠብቃለች።
የጊነስ ወርልድ የክብረ ወሰን ምዝገባ ሦስት ወር አካባቢ እንደሚወስድ ቃለ አቀባዩ ተናግረዋል።
ተከታታይ ሩጫዎችን አድርጋ ባጠናቀቀችበት ማግስት ባረፈችበት ወቅት ለጃኪ እንግዳ ነገር ነበር።
"ይሄ ነገር በማለቁ በተወሰነ መልኩ የደስተኝነት ስሜት ተሰማኝ" በማለት በአሪዞና ከሚገኘው ቤቷ ለቢቢሲ ተናግራለች።
"ነገር ግን አሁንም ቢሆን በሩጫው መቀጠል አለብኝ የሚል ሁኔታ ላይ ነኝ" ትላለች።
ሰውነቷም ቢሆን ይህንን ክብረ ወሰን ለማሻሻል ካደረገችው ተከታታይ ሩጫ ማገገም አለበት።
በደቡብ አፍሪካ ተወልዳ በእንግሊዝና ኔዘርላንድስ የኖረችው ጃኪ፣ አሁን ለደረሰችበት ደረጃ ምስጋናዋ የላቀ ነው። ምክንያቱም ሩጫ አጥታው የነበረውንና መቼም ይመለሳል ብላ ያላሰበችው በራስ መተማመኗን ስለሰጣት እንደሆነ ትናገራለች።
በአውሮፓውያኑ 2002 ነው በኔዘርላንድስ የሚገኙ ዶክተሮች ጃኪ ኤዊንግስ ሳርኮማ የተሰኘ የአጥንት ካንሰር እንዳለባት ያወቁት።
በተመረመረች በሁለት ሳምንት ውስጥም ሕይወቷን ለማትረፍ የግራ እግሯ መቆረጥ ነበረበት። በወቅቱ ጃኪ ገና 26 አመቷ ነበር።
"ሁሉም ነገር በፍጥነት ነው የተከናወነው" በማለት ታስረዳለች።
በመጀመሪያዎቹ ሁለት ዓመታት ጃኪ በሕይወቷ ከተከሰተው ለውጥ ጋር አብሮ ለመኖር ታግላለች። ካንሰሩ ከፍተኛ ንዴት ፈጠረባት እንዲሁም ከሰው የተለየ መሆኗ አሳፈራት። በቀዶ ጥገና የተተከለላትንም ሰው ሰራሽ እግር ሰዎች እንዳያስተውሉት ሱሪ በመልበስ ትሸፍነው ነበር።
ከዚያም በድንገት ነው በአውሮፓውያኑ 2016 መሮጥ የጀመረችው።
ባሏ ረጅም የርቀት ሩጫዎችን ሲያደርግ ብትደግፈውም እርሷ ግን እሮጣለሁ ብላ አስባም አልማም እንደማታውቅ ታስረዳለች።
ከዚያም ለረዥም ርቀት ሩጫ የሚሆናትን በሙሉ አዘጋጅታ ለመጀመሪያ ጊዜ 10 ሺህ ሜትር ለመሮጥ ተመዘገበች።
በሩጫው ዋዜማ ከአስር ሺህ ወደ ግማሽ ማራቶን የሩጫ ምድብ ቀየረች። ከዚያችን እለት ጀምሮ ወደኋላ አልተመለከተችም። ወደ ሩጫው አለም ገባች።
በዓመቱ መጀመሪያ ላይ ጃኪ ለራሷ ተከታታይ የማራቶን ውድድሮችን በማካሄድ ክብረ ወሰኑን መጨበጥ በሚል ሃሳቧን ለማሳካት ተነሳች።
ከዚህ ቀደም በጊነስ በሴቶች ዘርፍ የተመዘገበው ተከታታይ ውድድር በአሊሳ አሞሳ ክላርክ ሲሆን 95 ውድድሮችን በተከታታይ በማድረግ የተመዘገበ ነው። ከሁለት አመት በፊት የተመዘገበው ይህ ክብረ ወሰን ሁለት እግሮች ባሏት ሯጭ ነው።