ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኬንያ ምርጫ፡ የኬንያው ፕሬዚደንት ምክትላቸው ሥልጣን እንዲለቁ ጠየቁ
የኬንያ ፕሬዚደንት ኡሁሩ ኬንያታ ምክትላቸው ዊሊያም ሩቶ ከሥልጣናቸው እንዲለቁ ጠየቁ።
ፕሬዚደንቱ ይህንን የጠየቁት በነሐሴ ወር ከሚካሄደው አጠቃላይ ምርጫ በፊት በሁለቱ መካከል ያለው ውዝግብ እየከረረ በመምጣቱ ነው።
ፕሬዚደንት ኡሁሩ ምክትላቸው ሩቶ አገሪቷን እየተፈታተነ ያለውን የምጣኔ ሃብት ችግር ለመፍታት በቂ ጥረት አላደረጉም ሲሉ የከሰሷቸው ሲሆን መንግሥትን ከውስጥ ሆነው መተቸት እንደሌለባቸውም ፕሬዚደንቱ ተናግረዋል።
ይሁን እንጂ ምክትል ፕሬዚደንት ሩቶ በትዊተር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሁፍ ካቢኔው ከሁለት ዓመት በላይ ለሆነ ጊዜ ስብሰባ እንዳላደረገ እና ነገሮች ለፕሬዚደንቱ ስልክ በመደወል ብቻ እንደሚቀሩ ተናግረዋል።
በአገሪቷ ሕግ መሠረት ፕሬዚደንት ኡሁሩ ምክትላቸውን ለማባረር ሥልጣን የላቸውም።
በመሆኑም ምክትል ፕሬዚደንቱ ሩቶ ከሥልጣን ሊነሱ የሚችሉት ክስ ከቀረበባቸው አሊያም ሥራቸውን ለማከናወን የሚያስችል ብቃት ከሌላቸው ነው።
በፕሬዚደንት ኡሁሩ እና በምክትላቸው መካከል ያለው ልዩነት አገሪቱ በቀድሞው የአገሪቷ ፕሬዚደንት ምዋይ ኪባኪ ሞት ሀዘን ላይ ባለችበት ወቅት በግልጽ ተስተውሏል።
አርብ ዕለት በተካሄደው የቀድሞ ፕሬዚደንቱ የቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ ፕሬዚደንት ኡሁሩ የምክትላቸውን ሩቶን እጅ ለመጨበጥ ፈቃደኛ አልነበሩም።
በሁለቱ ባለሥልጣናት መካከል ያለው አለመግባባት የተፈጠረው ነሐሴ ላይ በሚካሄደው አጠቃላይ ምርጫ ምክንያት ነው።
ምክትል ፕሬዚደንት ሩቶ በመጪው ምርጫ ለፕሬዚደንትነት መወዳደር የሚፈልጉ ሲሆን ፕሬዚደንት ኡሁሩ የሚደግፉት ደግሞ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪውን ራይላ ኦዲንጋን ነው።
በዘንድሮው ምርጫ መዳረሻ ወቅቶች የአገሪቷ ምጣኔ ሃብት ጉዳይ ዋነኛ አጀንዳ ሆኖ ቆይቷል።
ኬንያ በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ የሆነ የዋጋ ንረት እያጋጠማት ሲሆን በተለይ እንደ የምግብ ዘይት እና ነዳጅ ያሉ መሠረታዊ ፍጆታዎች ዋጋ ጨምሯል።