በኢትዮጵያ የሽብር ጥቃት ለመፈጸም ሲዘጋጁ ነበር የተባሉ 34 የአልሸባብ አባላት በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተገለጸ

በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች የሽብር ጥቃት ለመፈጸም ሲዘጋጁ ነበር የተባሉ 34 የአልሸባብ አባላት በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት አስታውቋል።

እነዚህ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር የዋሉት ከሶማሌና ኦሮሚያ ክልሎች የጸጥታ አካላት ጋር በመተባባር በተከናወኑ ዘመቻዎች እንደሆነም የብሔራዊ መረጃና ደህንነት በትናንትናው ዕለት ሚያዝያ 15፣ 2014 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

የአልሻባብ ቡድን የሃይማኖታዊ በዓላት አከባበር የሚበዙባቸውን ወቅቶች ጠብቆ "የሽብር ተግባር ለመፈጸም ዝግጅት ሲያደርግ እንደነበር" ተቋሙ ባደረገው ክትትል መድረሱን መግለጫው አትቷል።

በአዲስ አበባ፣ ኦሮሚያና ሶማሌ ክልሎች ከፍተኛ ጥቃት ለመፈጸም በህቡዕ ሲያሴርና ሲዘጋጅም ቆይቷል ያለው ይህ መግለጫ የቡድኑን ሰንሰለት በመከታተልና መረጃ በማሰባሰብ ጥቃቱ እንዲፈጸም ሲያቀነባበሩና ሲዘጋጁ የነበሩ ያላቸውን 34 አባላት በቁጥጥር ስር በመዋላቸው የጥቃቱ ዕቅድ መክሸፉን ገልጿል።

መሃመድ ጉሃድ ሙርሰል እና ሼህ መሃመድ ሁሴን ዑስማን የተባሉ ግለሰቦች በኢትዮጵያ የአልሸባብ ህዋስ የምልመላና የሎጂስቲስክስ ጉዳዮችን የሚያስተባብሩ ተጠርጣሪዎች እንደነበሩም መግለጫው ጠቁሟል።

እነዚህ ግለሰቦች በሃገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ምልማላ በማካሄድ፣ የተመለመሉትን በማደራጀት፣ በቤት የሚሰሩ ፈንጂዎችን ዝግጅት ጨምሮ ተከታታይ ስልጠናዎችን በማካሄድ የአልሸባብ እንቅስቃሴ መሪ ተዋናይና አቀነባባሪ ነበሩም በማለት አትቷል።

በነዚህ ተጠርጣሪዎች ከተመለመሉትም መካከል ሚካል አብዱረህማን ኢብራሂም በተባለ ግለሰብ ስም የተለያዩ የባንክ አካውንቶች በመክፈት በአሜሪካ ሚኒሶታ፣ ሶማሌ ላንድ እና ኬኒያ ከሚገኙ የአልሻባብ ወኪሎች ከፍተኛ ገንዘብ ገቢ ሲያደርጉ እንደነበር የሰነድ ማስረጃዎች ማግኘቱን ተቋሙ ገልጿል። በ

ተለያዩ ሃገራት የሚገኙ የዚህ ጥቃት አካል የሆኑ ግለሰቦችም ተለይተው በቁጥጥር ስር እንዲውሉ በተለያየ ሃገራት ካሉ የመረጃ ተቋማት ጋርም በትብብር እየተሰራ ነው ብሏል።

ከሶማሌና ከኦሮሚያ ክልሎች ፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት በቁጥጥር ስር ከዋሉትም መካከል አስሩ በአሮሚያ ክልል ምዕራብ አርሲ፣ ምስራቅ አርሲ፣ ምዕራብ ባሌ፣ ምስራቅ ባሌ ፣ ምስራቅ ሸዋ፣ ምዕራብ እና በምስራቅ ሃረርጌ ዞኖች በሚገኙ በተለያዩ አካባቢዎች ነው።

ሃያ አራቱ ተጠርጣሪዎች ደግሞ በሶማሌ ክልል አፍዴር፣ ዶሎ፣ ጎዴ፣ ጅግጅጋና ሸበሌ መያዛቸው ተገልጿል።

ከተጠርጣሪዎቹም ጋር ክላሽ ጠመንጃዎች፣ የመትረየስ ሰንሰለቶች፣ የሞርታር ቅንቡላ መያዣ ሻንጣዎች፣ጥይቶች እና ሌሎችም የጦር መሳሪያዎች እንዲሁም ሰነዶችና የባንክ ደብተሮች መያዛቸው ተጠቁሟል።

መግለጫው ሙስሊሙ የረመዳን ፆም እንዲሁም ክርስቲያኑ የትንሳዔ በዓልን በሚያከብርበት ወቅት ኢትዮጵያን በሽብር ጥቃት በመናጥ በዜጎች ላይ የደህንነት ስጋት ለመፍጠር ቢንቀሳቀስም መክሸፉን አስታውቋል።