አሜሪካ በምዕራብ ትግራይ ተፈጽመዋል የተባሉት የጭካኔ ድርጊቶች እንደሚያሳስባት ገለጸች

የፎቶው ባለመብት, Reuters
አሜሪካ በምዕራብ ትግራይ በትግራይ ተወላጆች ላይ ተፈፀመ የተባለው ብሔርን መሠረት ያደረገ የጭካኔ ድርጊት በእጅጉ እንደሚያሳስባት ገለጸች።
አሜሪካ ይህንን የገለጸችው ሁለቱ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች አምነስቲ ኢንተርናሽናልና ሂውማን ራይትስ ዎች በአካባቢው ተፈፅሟል ባሉት ግድያ እና ሌሎች የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ላይ በጥምረት ሪፖርት ካወጡ በኋላ ነው።
በተለይ ድርጊቶቹ " ዘር ማጽዳት" ተብለው የሚፈረጁ ሆነው መገኘታቸው አሜሪካን እጅጉን እንደሚያሳስባት የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ያወጣው መግለጫ አመልክቷል።
የመብት ተሟጋች ድርጅቶቹ በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ ባወጡት ሪፖርት ከአስራ ሰባት ወራት በፊት ከተቀሰቀሰው ጦርነት ጀምሮ የአማራ ኃይሎች በተቆጣጠራቸውና በሁለቱ ክልሎች ይገባኛል በሚነሳባቸው አካባቢዎች የአማራ ኃይሎች በትግራይ ተወላጆች ላይ " የዘር ማጽዳት ዘመቻ" ከፍተዋል ሲል ይከስሳሉ።
ክሶቹ ሕገ ወጥ ግድያ፣ የጅምላ እስር እና በኃይል ማፈናቀል ይገኙበታል።
የሰብዓዊ መብት ድርጅቶቹ የፌደራል መንግሥት ይህ ድርጊት አንዲፈፀም ፈቅዷል አሊያም በተባሉት ወንጀሎች ላይ ተሳትፏል ብለዋል።
የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት ሪፖርቱን ተከትሎ በማኅበራዊ ትስስር ገጹ ባወጣው መግለጫ ሪፖርቱ ፍጹም ተቀባይነት የሌለው ነው ብሏል።
የፌደራሉ መንግሥት ሁለቱ ድርጅቶች ጉዳዩን ለመመርመር የተጠቀሟቸውን ፖለቲካዊ ጉዳዮች ትክክለኛነት ላይ ጥያቄ አቅርቧል።
የውስጥ ወሰን ጉዳዮች ሊታዩ የሚገባቸዉ ሕገ መንግሥታዊ ሥልጣን ባላቸው አካላት ነው ያለው መንግሥት፤ "እንዲህ አይነቱ ሪፖርታቸው ለፖለቲካ ፍጆታ እንደሚውልም የታወቀ ነው። ይህ አመለካከት ምርመራው በተገቢው ጥንቃቄ አለመፈፀሙን ከማሳየቱም በላይ በፍፁም ተቀባይነት የሌለው ነው።" ብሏል።
ሪፖርቱ ብሄር ተኮር ይዘት አለው ያለው ይህ መግለጫ ይህም ሁኔታ መንግሥትን እንደሚያሳስበውም አስፍሯል። ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ ክሶቹን ለመመርመር ቃል ገብታለች።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት አርብ ዕለት ባወጣው መግለጫ በሺዎች የሚቆጠሩ የትግራይ ተወላጆች ምዕራብ ትግራይ ውስጥ ለሕይወት አስጊ በሆነ ሁኔታ ታስረው የሚገኙ መሆናቸው መገለጹ ትኩረታቸውን እንደሳበው የገለጹት የመሥሪያ ቤቱ ቃል አቀባይ ኔድ ፕራይስ የቀሩ እስረኞች እንዲፈቱ እና ዓለም አቀፍ ክትትል እንዲደረግ ባለሥልጣናቱ ፈቃድ እንዲሰጡ ጠይቀዋል።
ባለፈው ወር በመንግሥት እና በትግራይ ኃይሎች መካከል የተደረገውን የሰብዓዊ እርቅ ስምምነት መቀበሏል የገለጸችው አሜሪካ በጦርነቱ የሚሳተፉ አካላት ጦርነቱን እንዲያቆሙ እና ግጭቱ በድርድር እንዲፈታ አሳስባ ነበር።
እርቁን ተከትሎም የሚካሄደው ውጊያ በከፍተኛ ደረጃ እየቀነሰ ቢመጣም ሁለቱም ወገኖች በትግራይ አስቸኳይ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው በሚሊየኖች የሚቆጠሩ ሰዎች እርዳታ ለማድረስ የሚደረገውን ጉዞ በመገደብ እርስ በእርስ መወነጃጀላቸውን ቀጥለዋል።














