የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት በግራሚ ሽልማት ላይ ጠንከር ያለ መልዕክት አስተላለፉ

የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዘለንስኪ ትናት ምሽት በተከናወነው የግራሚ ሽልማት መርሃግብር ላይ ቀድሞ በተቀረጸ ቪዲዮ ጠንካራ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ሌዲ ጋጋን እና ጀስቲን ቢበርን ጨምሮ ሌሎች እውቅ የሙዚቃ ባለሙያዎች በተገኙበት መድረክ ላይ ፕሬዝዳንቱ "ሙዚቀኞቻችን ከቶክሲዶ ይልቅ የጥይት መከላከያን ታጥቀዋል" ሲሉ ተደምጠዋል።

"በየሆስፒታሉ ለተጎዱና እነሱን መስማት ለማይችሉት ሳይቀር ያዜማሉ። ያቢሆንም ሙዚቃቸው ያበረታታቸዋል" ያሉት ዜሌንስኪ በሩሲያ ቦምቦች ተመትተው በዝምታ የተዋጡትን የዩክሬን አከባቢዎች "በሙዚቃችሁ ቀስቅሱት" ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።

"ዝም አትብሉ በምትችሉት መንገድ ሁሉ ደግፉን። ዝምታውን በሙዚቃችሁ ስበሩት" ሲሉም አክለዋል።

ቀድሞ የተቀረጸው የዜሌንስኪ መልዕከት ከተላለፈ በኋላ ጆን ሌጀንድ ‘ፍሪ’ የተባለውን አዲሱን ሙዚቃ በመድረኩ ላይ አቅርቧል።

"ሁላችንም ነፃ እስክንወጣ ድረስ ነፃነት ይዘንብ" እያለ ሌጀንድ ያቀነቀነው ሙዚቃ ዩክሬናዊያኑ አቀንቃኞች ሚካና ሱዛና ያጀቡት ሲሆን ሙዚቃው ሲቀርብ በዩክሬን ባለው ጦርነት የደረሰውን ጉዳት የሚያስመለክቱ ምስሎች በስክሪኖች ላይ ቀርበዋል።

በመዝጊያው ላይም ታዳሚዎች የዩክሬን ስደተኞችን ሊረዱባቸው የሚችሉ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ዝርዝሮች ተሰጥቷቸዋል።

ይህ ሙዚቃ ከመቅረቡ በፊት ፕሬዝዳንት ዜሌንስኪ “ከሙዚቃ በጣም የተቃረነ ነገር ምንድን ነው?” የሚል ጥያቄ አንስተው “በጸጥታ የተሞሉ የፈረሱ ከተሞችና የተገደሉ ሰዎች ናቸው” ብለዋል።

“ጦርነቱ የሚተርፈውን እና በዘላለማዊ ጸጥታ ውስጥ የሚኖረውን እንድንመርጥ ባይፈቅድልንም የሀገራችንን ነጻነት ለማስጠበቅ የመኖር፣ ሀገራችንን የመውደድ፣ የመሰማት” አማራጭ አለን ብለዋል።

ፕሬዝዳንቱ የቪዲዮ መልዕክታቸውን ሲዘጉ የሀገሬ ሰዎች “የግራሚ መድረክ ላይ እንደታደሙ ሰዎች ነፃ ይሆናሉ” የሚል እምነት አለኝ ብለዋል።

የሩሲያና ዩክሬን ጦርነት ከተቀሰቀሰ ወዲህ የዩክሬን ሙዚቀኞች፣ ፕሮዲውሰሮች እና ዲጄዎች ከሩሲያ ጋር የሚደረገውን ትግል ለመቀላቀል ስራቸውን አቁመዋል።

የሙዚቃ ባለሙያዎቹ የጦርነት ሪፖርተር ሆነው እየሰሩ እና ለወታደሮች እርዳታ እያሰባሰቡ ይገኛሉ።