ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በካሊፎርኒያ ግዛት በተከፈተ ተኩስ 6 ሰዎች ተገደሉ
በአሜሪካዋ ካሊፎርኒያ ግዛት ሳክራሜንቶ ከተማ በተከፈተ ተኩስ ቢያንስ ስድስት ሰዎች ሲገደሉ ተጨማሪ 12 ሰዎች ደግሞ ጉዳት ደርሶባቸዋል።
መጠጥ ቤቶች እና ምግብ ቤቶች በሚበዙበት አካባቢ የተከፈተውን ድንገተኛ ተኩስ ተከትሎ ሰዎች እራሳቸውን ለማዳን በየጎዳናዎቹ ሲሯሯጡ እና የድረሱልን ጥሪያቸውን ሲያሰሙ ነበር።
ፖሊስ ድንገተኛ ተኩሱን ተከትሎ በደረሰው ጥቆማ መሠረት በቦታው ሲደርስ በርካታ ሰዎች በአካባቢው ተሰብስበው እንደነበር የፖሊስ ኃላፊዋ ካትሪን ሌስተር ገልጸዋል። እስካሁን ድረስ ምንም አይነት ተጠርጣሪ በቁጥጥር ስር ያልዋለ ሲሆን የሟቾች ቁጥር ሊጨምር እንደሚችልም ተገምቷል።
''ይህ በጣም የሚያሳዝን ክስተት ነው" ያሉት ኃላፊዋ መርማሪዎች በቦታው ሲደርሱ በመጀመሪያ ስለ ጥቃት አድራሾቹ ማንነት መረጃ ያለው እንዲጠቁም ነው የጠየቁት ብለዋል ኃላፊዋ።
ጥቃቱ የተፈጸመው ከግዛቷ ካፒቶል ሂል ብዙም በማይርቅ ቦታ ሲሆን በአካባቢው ደግሞ ሳክራሜንቶ ኪንግስ በመባል የሚታወቀው የቅርጫት ኳስ ቡድን የሚጫወትበት ነው።
ፓሜላ ሃሪስ እንደምትለው ጥቃቱ ከመፈጸሙ ጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ሴት ልጇ ደውላ የ38 ዓመቱ ወንድ ልጇ ከአንድ የምሽት ቤት አካባቢ ተተኩሶበት መገደሉን ነግራታለች።
''እንደሞተ ስትነግረኝ እራሴን ስቼ ወደቅኩኝ'' ስትል በወቅቱ የነበረው ሁኔታ ምን እንደሚመስል ሮይተርስ የዜና ወኪል ገልጻለች።
አክላም "ምን እንደተፈጠረ መረጃ ሳላገኝ ከዚህ ቦታ አልንቀሳቀስም። የትም አልሄድም፤ አሁንም ድረስ ህልም ነው የሚመስለኝ" ብላለች።
የ32 ዓመቷ ኬይ ሀሪስ ደግሞ ጥቃቱን ተከትሎ ከአንዳንድ የቤተሰብ አባላት ድንገተኛ የስልክ ጥሪ እንደደረሳትና ምናልባት ወንድሟ ሳይገደል እንዳልቀረ እንደተነገራት ገልጻለች። ለአሶሺየትድ ፕሬስ ስትናገርም ወንድሟ በአካባቢው የሚገኘውን መሸት ቤት እንደሚያዘወትረውና እሷም ሄዳ እንደምታውቅ ገልጻለች።
የከተማዋ አስተዳዳሪ ዴረል ሰቲንበርክ በበኩላቸው በትዊተር ገጻቸው ላይ ባስተላለፉት መልዕክት በጥቃቱ ሕይወታቸው ያለፈና ጉዳት የደረሰባቸውን ሰዎች ቁጥር ማሰብ በጣም አስቸጋሪ እንደሆነ ገልጸዋል።
"በጦር መሳሪያ የሚፈጸሙ ጥቃቶች የከተማችን፣ የግዛታችን እንዲሁም የአገራችን ስጋት ነው። ይህንን ለመቀነስ የሚደረጉ ማንኛውም አይነት እርምጃዎችን እደግፋለው'' ሲሉም አክለዋል።
አሜሪካ ውስጥ ከጦር መሳሪያዎች ጋር በተያያዘ በየዓመቱ 40 ሺ ሰዎች የሚሞቱ ሲሆን ይህ ደግሞ በመሳሪያዎች እራሳቸውን የሚያጠፉ ሰዎችንም እንደሚያካትት መሰል ጥቃቶችና አደጋዎችን የሚመዘግበው የአሜሪካው ድረ ገጽ መረጃ ያሳያል።