የዶናልድ ትራምፕ አዲሱ ማሕበራዊ ሚድያ ምን ዋጠው?

ባለፈው ዓመት ጥቅምት ላይ ነበር የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ አብዮታዊ የቴክኖሎጂ ኩባንያ እከፍታለሁ ሲሉ ቃል የገቡት።

"ትሩዝ ሶሻልን ፈጥርያለሁ። ትላልቅ ኩባንያዎች በእውነት ስም ለመሞገት ስል" ብለው ነበር።

"እንግዲህ የምንኖርበት ዘመን ታሊባን ትዊተር ላይ ብዙ ተከታዮች ያፈራበት፤ እናንተ የምትወዱት ፕሬዝደንታችሁ ግን ድምፁ የታፈነበት ነው" ሲሉ ምሬታቸው ገልጠዋል በወቅቱ።

ትራምፕ እንደፎከሩ አልቀሩም።

ትሩዝ ሶሻል የተባለውን ማሕበራዊ ድር አምባ በፈረንጆቹ የካቲት 21 ይፋ አደረጉ።

ነገር ግን ከስድስት ሳምንታት በኋላ የዶናልድ ትራምፕ አዲሱ ድር አምባ በችግር ተተብትቧል።

ቢያንስ 1.5 ሚሊዮን ሰዎች ትራምፕን ብለው ይህን ድር አምባ ለመጠቀም ቢመዘገቡም በቀላሉ የቀድሞውን ፕሬዝደንት ማግኘት አልቻሉም።

ይህን ማበራዊ ሚዲያ ለመጠቀም የተመዝጋቢዎች ቁጥር 1.4 ሚሊዮን ደርሷል።

ትሩዝ ሶሻል በትዊተር አምሳል ነው የተሠራው። ትራምፕ ከዚህ በኋላ መተግበሪያዬን መጠቀም አይችሉም ብሎ እስከወዲያኛው ባሰናበተው ትዊተር አምሳል።

ትዊተር ትራምፕን ከአምባው ያገደው ምርጫው በግድ "ተጭበርብሯል" ብለው ሃሳዊ ንግግር አሰራጭተዋል፤ አመፅም ቀስቅሰዋል በሚል ነው።

ትራምፕ ከትዊተር በሞት ይፍታህ የተባረሩት በፈረንጆቹ ጥቅምት 8 ነበር።

'ትሩዝ ሶሻል' ትዊተርን ይምሰል እንጂ አንድሮይድ ስልክ ለሚጠቀሙ ሰዎች አልተሠራም፤ በድረ-ገፅም ማግኘት አይቻልም።

አልፎም ይህ ድር አምባ ከአሜሪካ ውጭ ላሉ ተጠቃሚዎች ክፍት አይደለም።

"ትልቅ ውድቀት ነው" ነው ይላሉ የኒው ዮርክ ዩኒቨርሲቲ የሶሻል ሚድያና ፓለቲክስ ማዕከል ኃላፊው ጆሽዋ ታከር።

ስማቸው እንዳይጠቀስ የሻቱ አንድ ሪፐብሊካን የዶናልድ ትራምፕ ደጋፊ ደግሞ "ምን እየሆነ እንዳለ የሚያውቅ ሰው የለም" ሲሉ ሹክ ብለዋል።

የካቲት 21 ትሩዝ ሶሻል አፕ ስቶር ከተሰኘው የአይኦኤስ መተግበሪያ ማውረዳጅ ላይ ብዙ ሰዎች ያወረዱት መተግበሪያ ሆኖ ነበር። ነገር ግን ያወረዱት ሰዎች ሊጠቀሙበት አልቻሉም።

ብዙዎች ችግሩ በጥቂት ቀናት ተቀርፎ ዶናልድ ትራምፕ እንደተለመደው አወዛጋቢ ፅሑፋቸውን ጣል ያደርጋሉ ተብሎ ቢጠበቅ ጠብ የሚል ነገር ጠፋ።

እነ ዩቲዩብ፣ ቲክቶክ፣ ፌስቡክና እና ኢንስታግራም ብዙ ሰዎች ያወረዷቸው 10 መተግበሪያዎች ሆነው ታሪክ ሲፅፉ የትራምፕ ትሩዝ ሶሻል ከቁንጮ 100 ተርታ ውጭ ነው።

አንደምንም ብለው ትሩዝ ሶሻልን መጠቀም የቻሉ ሰዎች ደግሞ ውስጥ ሲገባ ዝምታው ይጮኻል ይላሉ።

አብዛኛዎቹ ቀኝ ዘመም የአሜሪካ ፖለቲከኞች እስካሁን ትሩዝ ሶሻልን ለመቀላቀል እያመነቱ ነው።

አሁን ደግሞ መተግበሪያውን ከአፕ ስቶር የሚያወርዱት ሰዎች ቁጥርም እየቀነሰ ነው።

"ከሳምንታት በፊት ነበር ትሩዝ ሶሻልን ለመጠቀም የተመዘገብኩት። ነገር ግን እስካሁን ተጠባባቂ ወንበር ላይ ነኝ" ሲል አንድ ግለሰብ ትዊተር ላይ ለጥፎ ነበር።

የትሩዝ ሶሻል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ዴቪን ኑኔዝ ድር አምባው በመጋቢት ወር መጨረሻ "ሙሉ በመሉ ሥራ ይጀምራል" ብለዋል።

ነገር ግን መተግበሪያው ለምን እንደዚህ በችግር እንደተበተበ ለብዙዎች ግራ የገባ ሆኗል።

አንዳንዶች ትሩዝ፤ ራምብል ከተሰኘው በዩቲዩብ አምሳል ከተሠራው የተንቀሳቃሽ ምስል መጋሪያ ድር ጋር መጣመሩ ነው ያንቀራፈፈው ይላሉ።

በወግ አጥባዊ አሜሪካዊያን ዘንድ ታዋቂ የሆነው ራምብል የትሩዝ የጀርባ አጥንት ይሆናል ተብሎ ተጠብቆ ነበር።

ችግሩን በቀናት ልዩነት መፍታት አልተቻለም? የብዙዎች ጥያቄ ነው።

"በስድስት ሳምንታት ሳይሆን በጥቂት ቀናት ውስጥ ሊፈታ ይገባ ነበር" ይላሉ ሪፐብሊካኑ የትራምፕ የቅርብ ሰው።

"ሁሌም ሲጀመር ችግር አያጣውም። ነገር ግን አሁን ተፈቶ ልንጠቀመው በተገባ ነበር። ምን እየሆነ እንዳለ የገባው ሰው የለም።"

ትራምፕ በዚህ የትሩዝ ቀርፋፋ አጓጓዝ ደስተኛ አይደሉም።

ምንም እንኳ ከ750 ሺህ በላይ ተከታዮች ቢያፈሩም ከአንድ ወር በላይ ምንም ነገር አልጠፉም።

የሲሊከን ቫሊይ ግዙፍ ድር አምባዎችን ይፎካከራል የተባለው ትሩዝ ለጊዜው ቆሞ መራመድ የተሳነው ይመስላል።