ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ጄዳ ፒንኬት ስሚዝ ዝምታዋን ሰበረች
ጄዳ ፒንኬት ስሚዝ ባሏ በሕዝብ ፊት ክሪስ ሮክ የተባለውን ኮማኪ በጥፊ ካጮለ በኋላ ዝምታዋን ሰበረች።
ተዋናይት ጄዳ ፒንኬት ስሚዝ ኢንስታግራም የተሰኘው ድር አምባ ላይ "አሁን ጊዜው የፈውስ ነው" የሚል ፅሑፍ አሥፍራለች።
ባሏ ዊል ስሚዝ ባለፈው እሑድ በታላቁ የተዋንያን ሽልማት መድረክ ብዙዎችን አጀብ ያስባለ ድርጊት መፈፀሙ አይዘነጋም።
ክሪስ ሮክ የተባለው ኮመዲያን ጄዳ ፒንኬትን የሚነካ ንግግር ከተናገረ በኋላ ደንበኛ ጥፊ ከዊል ስሚዝ አስተናግዷል።
ዊል ስሚዝ ለዚህ ድርጊቱ "ግጭት መርዛማና አጥፊ ነው" የሚል ርዕስ ያለው ይቅርታ ፅፎ ለጥፏል።
እሑድ ለሊት ይህ የሆነው ዊል ስሚዝ ምርጥ ተዋናይ ተብሎ የኦስካር ሽልማት ከማግኘቱ ከደቂቃዎች በፊት ነው።
ክሪስ ሮክ ጄዳ ፒንኬት ስሚዝ ፀጉሯን መላጨቷን ተንተርሶ ቀልድ ቢሰነዝርም ፀጉር የሚያሳሳ በሽታ እንዳለባት የሚያውቀው ዊል ስሚዝ ግን አልተዋጠለትም።
ጄዳ፤ ምንም እንኳ ስላ ባሏ ድርጊትም ይሁን ስለክሪስ ሮክ ቀልድ ምንም ባትተነፍስም "አሁን ጊዜው የፈውስ ነው፤ እኔም ዝግጁ ነኝ" ስትል የኢንስታግራም ገጿ ላይ አስፍራለች።
ክሪስ ሮክ የዊል ስሚዝን ቡጢ የሚያስንቅ ጥፊ ካስተናገደ በኋላ እስካሁን ምንም ትንፍሽ አላለም።
ነገር ግን ከእሑዱ ታሪካዊ ክስተት በኋላ በርካቶች የኮመዲ ሥራውን ለማየት ቲኬት ቆርጠዋል።
አንድ የክሪስ ሮክን ቲኬት የሚሸጥ ድረ-ገፅ እንደጠቆመው ኮመዲያኑን ባለፈው ከወር ከሸጠው የሚበልጥ ቲኬት በአንድ ለሊት ቸብችቧል።
አልፎም ኮመዲያኑን ለማየት ቀድሞ 46 ዶላር የነበረው የአንድ ቲኬት ዋጋ ወደ 411 ዶላር ተወንጭፏል።
ክሪስ ሮክ የአሜሪካ ከተሞችን እያዳረሰ የኮመዲ ሥራውን ለማሳየት ከአንድ ወር በፊት ሻንጣውን ጠቅልሎ ቢወጣም ከግማሽ በላዩን ቲኬት የቸበቸበው ከእሑዱ ክስተት በኋላ ነው።
ዊል ስሚዝ የሙያ አጋሩ ክሪስ ሮክን ጩኸቱ አድማስ በሚሻገር ጥፊ ካጮለ በኋላ ሪቻርድ ኪንግ ሪቻርድ በተሰኘው ፊልም ላይ ባሳየው ትወና የዓመቱ ምርጥ ተብሎ ተሸልሟል።
ይህ ፊልም የቴኒስ ከዋክብቱን ሰሪና እና ቬነስ ዊሊያምስ አባት ሪቻርድ ዊሊያምስን ታሪክ ይዘክራል።
ሰኞ ዕለት ሪቻርድ ዊሊያምስ፤ ዊል ስሚዝ ያደረገው ድርጊት ትክክል አይደለም ሲሉ ተዋናዩን ወቅሰዋል።
"የድርጊቱን ዝርዝር ባናውቅም ራስን ለመከላከል ካልሆነ በቀር ሰውን መማታትን አንደግፍም" ሲሉ በቃል አቀባያቸው በኩል ኤንቢሲ ለተሰኘው ጣቢያ ድምፃቸውን ሰጥተዋል።
ዊል ስሚዝ ከዓመታት የሆሊውድ ሥራዎች በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የኦስካር ሽልማት ያገኘው ዘንድሮ ነው።