በዘይት እጦት እየተንገፈገፉ ያሉት አልጄሪያውያን

ዘይት እየፈለገች ያለች ግለሰብ

የፎቶው ባለመብት, AFP

በሰሜናዊቷ አፍሪካ አገር አልጄሪያ የምግብ ዋጋ በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ ሲሆን ለዚህም የአንበሳ ድርሻውን የያዘው በአገሪቱ የተከሰተው የዘይት እጥረት ነው።

በገበያ ውስጥ ያለው ዘይትና እና ወተት ምርቶች በጣም አናሳ በመሆኑ ምክንያት ሸማቾች በመደብሮች ውስጥ በሚገበዩበት ወቅት ነጋዴዎችን መለማመጥ እንዲሁም ማሞካሸት ይጠበቅባቸዋል።

የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመግታት ተጥለው የነበሩ መመሪያዎች እንዲሁም በቅርቡ የተከሰተው የዩክሬን ጦርነት ተደማምሮ እጥረቱን ያባባሰው ሲሆን ለሸማቾችም ህይወትን ፈታኝ አድርጓታል።

"መድኃኒት የመግዛት አይነት ስሜት አለው" ትላለች የ31 አመቷ ሳሚሃ ሳመር በንዴትና በምጸት በተቀላቀለው ድምጸት።

ለቤተሰቦቿና ጓደኞቿ ኬክ መስራት ትወድ የነበረችው ሳሚሃ በዚህም ገቢም ታገኝ ነበር በአሁኑ ወቅት ግን ለኬክ የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን ማግኘት አልቻለችም።

"ከየትኛውም መደብር ዘይት ለመግዛት የሱቁ ባለቤት ጋር ወዳጅነት ወይም ትውውቅ መኖር አለበት" በማለት ሁኔታውን ታስረዳለች።

የግብይይት ሁኔታውም የሚከናወነው ሚስጥራዊ በሆነ ሁኔታ ነው። ዘይት እንደማንኛውም እቃ መደብሩ መደርደሪያ ፊት ለፊት ላይ አይታይም፤ ሻጮች መደብሮች ውስጥ ደብቀው ነው የሚያስቀምጡት።

እንደ በርካታ አልጄሪያውያን የኮሮናቫይረስ መመሪያዎች ከፍተኛ ጫና ሲያደርሱና በርካታ ነገሮችን ሲቀይሩ የተመለከተችው ባለፈው ዓመት ነበር።

የሙስሊሞች ረመዳን ፆም ሊጀምር በተቃረበበት በአሁኑ ወቅትና ቅዱስ ወር ተብሎ በሚጠራው በዚህ ወር ለሚሰሩ የተለያዩ ዓይነት ምግቦች ግብዓት የሚሆነውን ዘይት ለመሸመት ነዋሪዎች ፍለጋቸውን አጠናክረው ቀጥለዋል።

ሳሚሃ አንዳንድ ጊዜ ፍራፍሬ እና አትክልቶችን ለመግዛትም ከምትኖርበት ከተማ ቢልዳ ረከስ ወዳለባትና ወደ አቅራቢያዋ ወደምትገኘው ኮሊያ ሄዳ መሸመት ይኖርባታል።

ሳሚሃ ሳመር

የፎቶው ባለመብት, Samiha Sammer

ሌሎች የምግብ ሸቀጦችም እንዲሁ ዋጋቸው ንሯል። ለምሳሌ ድንችን ብንወስድ ከጥቂት ወራት በፊት ከነበረው ከ30 በመቶ በበለጠ አሻቅቧል። ወተት ለመግዛት ነዋሪዎች ጸሃይ ከመውጣቷ በፊት ወደ መደብሮች በማቅናት ረጅም ወረፋ መጠበቅ ይኖርባቸዋል።

"ወተት ለማግኘት የተሰለፉ ሰዎችን መግፋት አንዳንዴም መጣላት ስለሚያጋጥም አሁን አቁሜያለሁ" በማለት የአስተዳደሩ ጸሃፊ ይናገራሉ። "በጣም የሚያዋርድ ተግባር ነው " የሚሉት ጸሃፊዋ እነዚህን ሰልፎች መራቅ ግን ዋጋ አስከፍሏቸዋል።

ከህዝብ ጋር እየተገፋፉና ረጅም ወረፋ መጠበቅንም በመተው ከውጭ አገር ለሚገባ አንድ ኪሎ የዱቄት ወተት 2.90 ዶላር አካባቢ መክፈል ይጠበቅባቸዋል። በመንግሥት ድጎማ የሚደረግለት ወተት ዋጋ 17 ሳንቲም ዶላር ነው።

አልጄሪያ ወተት ብታመርትም ነገር ግን መጠኑ በጣም አናሳ ነው። ለዓመታትም ከፈረንሳይ፣ ከሌሎች የአውሮፓ ህብረት ሃገራት እንዲሁም በቅርብ ጊዜ ከተባበሩት አረብ ኤምሬቶች በሚመጣ ወተት ጥገኛ ናት። የሚገባው ወተት በዱቄት መልክ ሲሆን ለሸማቾች ከመድረሱ በፊት ፋብሪካዎች ወደ ፈሳሽነት ይቀይሩታል።

ወተት እጥረት ቢኖርም በርካታ አልጄሪያውያንን እያስጨነቀ ያለው የዘይት ዋጋ መናር ነው።

እንደ ወተት ዘይትም ቢሆን በመንግሥት ድጎማ ቢደረግለትም በቅርቡ ከተከሰተው ቀውስ በፊትም ቢሆን ውድ ነበር። በዚያን ጊዜም የአምስት ሊትር ዘይት ዋጋ 4.20 ዶላር ወይም 216 ብር ነበር።

የአልጄሪያ ጣፋጭ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የአልጄሪያውያን ወርሃዊ ደመወዝ በአማካይ በግሉ ዘርፍ 240 ዶላር እንዲሁም የመንግሥት ሰራተኞች ደግሞ 410 ዶላር ሲሆን ባለስልጣናቱም በናረው የሸቀጥ ዋጋ ላይ እርምጃ እንዲወስዱ ጫና ቢፈጠርባቸው ብዙም አያስገርምም።

በአገሪቷ ኢኮኖሚ ሳቢያ ምግብ ማከማቸት እንዲሁም ሙስና በከፍተኛ ሁኔታ ማንሰራራቱን የፓርላማው ኮሚቴ በሪፖርቱ ይፋ አድርጓል።

በፓርላማው የተመረጠው ኮሚቴ አባል የሆኑት ሂሻም ሳፋር ለቢቢሲ እንደተናገሩት የዘይት ነጋዴዎች ከመንግሥት ተጨማሪ ገንዘብን ለመጠየቅ በሚል ድጎማ የተደረገለት ዘይት ላይ ሰው ሰራሽ የሆነ የዋጋ ንረት እየፈጠሩ ይገኛሉ።

ባለፈው ዓመት ወደ 150 ሺህ የሚጠጉ ጥሰቶች ለባለስልጣናቱ ሪፖርት የተደረጉ ሲሆን አብዛኞች ፍርድ ቤት ቀርበዋል እንዲሁም በሺዎች የሚቆጠሩ የንግድ ፈቃዶች ተነጥቀዋል።

ከዚህም ጋር በተያያዘ በአገሪቷ ድጎማ የተደረገላቸው ሸቀጦች በደቡባዊ ድንበር አቋርጦ በጎረቤት ሃገራት በህገወጥ መንገዶች እየተሸጡ ይገኛሉ። ይህም መጠነ ሰፊ እንደሆነ የፓርላማ ኮሚሽኑ መጠነ ሰፊ እንደሆነም አመልክቷል።

ምንም እንኳን ይፋ የሆነ አሃዝ ባይኖርም ምንጮች ለቢቢሲ እንደተናገሩት 12 የሚሆን የጭነት መኪና ዘይት ወደ ማሊና ኒጀር በድብቅ ይወሰዳል።

ህገወጥ ነጋዴዎቹ በመንግሥት ድጎማ የተደረገለትን ዘይት በመቸብቸብ በአንድ ጭነት መኪና እስከ 17 ሺህ 800 ዶላር ትርፍ እንደሚያገኙም ምንጮቹ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ ፕሬዝዳንት አብደልማጂድ ቴቡኔ ከውጭ የመጡ ምርቶች ወይም ግብዓታቸው ከውጭ የመጣ እንደ ዘይት፣ ስኳር፣ ፓስታ፣ ሰሞሊና እና የስንዴ ምርቶች ወደ ውጭ እንዳይላኩ አግደዋል።

ሪፖርቶች እንደሚጠቁሙት ፕሬዚዳንቱ መሰል ድርጊቶች ሆን ብሎ የአገሪቱ ምጣኔን ሆን ብሎ ለማደናቀፍ የተሸረበ ሴራ ስለሆነ ከፍተኛ ቅጣት እንዲጣልባቸው ይፈልጋሉ።

ነገር ግን በአልጄሪያ ለተነሳው ቀውስ ጥልቅ መንስኤዎችን ለማወቅ ወደ ኋላ መለስ ብሎ መመልከት እንደሚያስፈልግ ባለሙያዎች ይናገራሉ።

"አገሪቷ በማፍያ ተዘርፋለች"

የአገሪቷ ምጣኔ ኃብት መሰረቱ ጋዝ እና ድፍድፍ ነዳጅ መሆኑ እንዲሁም የመንግሥት ገቢ ምንጭም በነዚህ ምርቶች ላይ ጥገኛ መሆኑ በርካታ ችግሮችን ፈጥሯል ይላሉ የምጣኔ ሀብት ባለሙያው አብዳል ራህማን ሀዴፍ።

በዘርፉ ላይ የሚደረጉ ስምምነቶች መልካም አስተዳደር ጉድለት የሚታዩበትና ከፍተኛ ገንዘብ የሚወጣባቸው መሆናቸውንም አብዳል ይናገራሉ።

የኢኮኖሚው ችግር ወደ ከፋ ፖለቲካዊ አለመረጋጋት ሊያመራ ይችላል የሚል ስጋትም ፈጥሯል።

የዋጋ ንረቱ "በህዝቡ እና በአስተደዳሩ መካከከል መካከል ያለው ደካማ ግንኙነት ሊፈርስ የሚችልበት ደረጃ ላይ ሊያደርሰው ይችላል፣ ይህም በህዝቡ ላይ ከፍተኛ ቅሬታን ይፈጥራል" ሲሉ የሶሺዮሎጂ ባለሙያ ፕሮፌሰር ራቺድ ሃማዶቼ ያስጠነቅቃሉ።

የቀድሞው ፕሬዝዳንት አብደላዚዝ ቡተፍሊካ በአውሮፓውያኑ 2019 የተነሳውን ሰፊ ህዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ ስልጣናቸውን ለመልቀቅ ተገደዋል።

ተተኪው ፕሬዚዳንት በአንድ ወቅት የቀድሞው ፕሬዚዳንት ቅርብ አጋር የነበሩ ሲሆን በቡተፍሊካ መሪነት "የሀገሪቱን ካዝና የዘረፈውን ማፍያ" ደጋግመው ሲያወግዙም ተዘሰምቷል።

የፕሬዝዳንቱ ለውጥ ቢኖርም በርካታ ወጣቶች ለውጥ ባለመኖሩ ቅር እንደተሰኙ ነው ከዚህም ጋር ተያይዞ የኮሮናቫይረስ ወረረርሽኝ እስከተከሰተበት ድረስ በርካታ የአደባባይ ተቃውሞዎች አድርገዋል።

የአገሪቱ ሶስት አራተኛ ህዝብ ከ37 አመት በታች ነው፣ ስራ አጥነት 11 በመቶ ደርሷል፤ ይባስ ብሎ በርካታ ስራ አጦች የዩኒቨርስቲ ምሩቃን ናቸው።

መንግሥት የህዝቡን እሮሮ በጊዜያዊነት ለማስታገስ በሚመስል መልኩ በንቃት ስራ እየፈለጉ መሆናቸውን ማረጋገጥ የሚችሉ ስራ አጥ ዜጎች 90 ዶላር የሚጠጋ ወርሃዊ አበል እንደሚሰጣቸው ተናግሯል።

በዩክሬን ጦርነት ምክንያት በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚታየው የነዳጅ ዋጋ መጨመር ሁኔታውን ቀለል የሚያደርግላቸው ሲሆን ለባለሥልጣናቱ ይህንን ገንዘብ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለመክፈል ያስችላቸዋል ተብሏል።

ነገር ግን አልጄሪያ በዚህ አጋጣሚ የተገኘው የነዳጅ ገቢን ማባከን እንደማትችል የምጣኔ ኃብት ባለሙያዎች አጥብቀው ይከራከራሉ ።

አሁን ግን እንደ ሳመር ያሉ ሸማቾች በአሁኑ ወቅት ወዳጅ የሚሆናቸውም ባለመደብርና የተደበቀ ዘይት ላይ ተስፋቸውን ጥለዋል።